Saturday, 11 March 2017 12:17

ሔኒከን ቢራ በ176 ሚ. ብር የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ አቋቋመ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 በ5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተቋቋመው ሔኒከን ቢራ ፋብሪካ፣ ተረፈ ምርቱን በማጣራት ለማስወገድ የሚያስችል የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመገንባት ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉ ተገለፀ፡፡
በፋብሪካው የተገነባው የፍሳሽ ማጣሪያና ማስወገጃ ጣቢያ ሰሞኑን በጋዜጠኞች በተጎበኘበት ወቅት የሔኒከን ቢራ ፋብሪካ የቂሊንጦ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ምትኩ እንደተናገሩት፤ ሔኒከን ቢራ በአዲስ አበባ ከተማ ቂሊንጦ አካባቢ ላስገነባው የቢራ ፋብሪካ ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ባስገነባው የፍሣሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት ዓለም እየተጠቀመበት የሚገኘውን ዘመናዊ ማጣሪያ በመጠቀም በህብረተሰቡ ላይ ምንም ዓይነት የጤና ጉዳት የማያስከትል ንፁህ ውሃ ይለቃል፡፡
በዘመናዊው የፍሳሽ ማጣሪያ እየተጣራ የሚለቀቀው ተረፈ ምርት ወደ አቃቂ ወንዝ እስከሚገባ ድረስ በክፍት ቱቦ የሚተላለፍ በመሆኑ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የክፍለ ከተማውና የወረዳው መስተዳድር አመራሮች ከፋብሪካው አስተዳደር ጋር ባደረጉት ሰፊ ውይይት ችግሩን ከሥሩ ለመቅረፍና ከተጣራው ተረፈ ምርት የሚመጣው ቆሻሻ ያለምንም ሽታ ወደ ወንዙ የሚገባበትን መንገድ ለማመቻቸት ሰፊ ጥናት መደረጉን አቶ አንተነህ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ጥናት መሰረትም ፍሳሹ በዝግ ቱቦ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት መነደፉንም ጠቁመዋል፡፡  በሔኒከንና በዋሊያ የንግድ ስያሜ በዓመት 3 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው፤ የሐረርና በደሌ ቢራ ፋብሪካዎችንም ከመንግስት በመግዛት ዓመታዊ ምርቱን ወደ 4 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር አድርሷል፡፡

Read 1342 times