Monday, 13 March 2017 00:00

የጉራጌ ዞን፤ ባለሃብቶች እንዲያለሙ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ባለፈው ቅዳሜ ከጉራጌ ዞን ተወላጆች ጋር በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ ላይ በአካባቢው ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ውይይት ያደረገው የዞኑ አስተዳደር፤ ከ340 ሺህ ሄክታር በላይ ቦታ አዘጋጅቼ ባለሀብቶችን እየተጠባበቅኩ ነው ብሏል፡፡ የአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶች ይሄን እድል በቅድሚያ እንዲጠቀሙበትም የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኮርንማን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለአንድ ቀን በተደረገው በዚህ ውይይት ላይ ከ200 በላይ የዞኑ ተወላጅ ባለሀብቶች የተሳተፉ ሲሆን አካባቢው ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ሶስት ጥናቶች ቀርበው ገለፃ ተደርጓል። ዞኑ በተለይ ለግብርና እና ለግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ልማት የተመቻቸ ሁኔታ እንዳለው በመድረኩ የቀረቡ ጥናቶች ያመለከቱ ሲሆን በእነዚህ ዘርፎች በጣት የሚቆጠሩ ባለሀብቶች ብቻ ኢንቨስት በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ለአበባ፣ ለመድኃኒት ተክሎች፣ ለተለያዩ አትክልቶች፣ ለሰሊጥ፣ ለበርበሬ፣ ለድንች ልማት የተመቻቸ የአየር ንብረትና መሬት እንዲሁም ለመስኖ የሚሆኑ አምስት ወንዞች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ዞኑ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ እንደ መገኘቱ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሊሆን ይገባው ነበር፤ ሆኖም እስከ ዛሬ ሲቀርቡ ለነበሩ የኢንቨስትመንት ግብዣዎች ምላሽ የሰጡት ጥቂቶች ናቸው ሲሉ የዞኑ አስተዳዳሪ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡  
ለእንስሳት እርባታና ለእንስሳት ውጤቶች ማቀነባበሪያ የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶች በተገቢው መጠን መሟላታቸውንም አስተዳዳሪው አስታውቀዋል። እነዚህን ሁሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መሰረተ ልማት አሟልቼ ኢንቨስተሮችን ብጋብዝም ውጤታማ አልሆንኩም ብሏል፤ አስተዳደሩ፡፡
በአካባቢው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በየዓመቱ አስር የሚደርሱ ባለሀብቶች ወደ ዞኑ ይመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም በአመት በአማካይ አንድ ባለሀብት ብቻ የኢንቨስትመንት ጥያቄ እያቀረበ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ የዞኑን የኢንቨስትመንት ግብዣ ተቀብለው፣ መሬት ወስደው ውጤታማ ተግባር ካከናወኑ ኢንቨስተሮች መካከል ቲናው የአበባ ልማት፣ ዘቢደር ቢራ፣ ኤደን ውሃ እና ሌሎች በወተት ማቀነባበር ላይ የተሠማሩ ኩባንያዎች ተጠቅሰዋል፡፡  
‹‹የጉራጌ ዞን በመላ ሃገሪቱ ካሉት ተወላጅ ባለሃብቶቹ አንፃር በእድገትና ልማት መድረስ የነበረበት ደረጃ ላይ አለመገኘቱ እንደሚያስቆጣቸው የገለፁት አንዳንድ የመድረኩ ተሳታፊ ባለሃብቶች፤ ዞኑ እንድናለማ ቢጋብዘንም ከክልሉ መንግስት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለማግኘት ውጣ ወረዱ አታካች ነው ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸል፡፡  
አንድ የዞኑ ተወላጅ ምሁር በበኩላቸው፤”የጉራጌ ባለሃብት አኩርፏል፤ ለምን እንዳኮረፈ ልትጠይቁት ይገባል” ብለዋል። ታታሪው የጉራጌ ባለሃብት የዞኑን ጥያቄ በሚፈለገው መጠን ለምን እንዳልተቀበለ ሊጠና እንደሚገባውም እኚሁ ምሁር አስገንዝበዋል።
የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ፤ “በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ ያዘጋጀሁትን 103 ሄክታር የከተማ ቦታ ጨምሮ በ14 የተለያዩ ከተሞች 340 ሺህ 926 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት አዘጋጅቻለሁ፤ አቅሙ ያላችሁ ባለሃብቶች ወስዳችሁ ስሩበት” የሚል ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 748 times