Monday, 13 March 2017 00:00

ሙቨንፒክ ዮቤክ የሚያስገነባውን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ሊያስተዳድር ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገውና በአውሮፓ፣ በኤስያና በአፍሪካ ከ300 በላይ ሆቴሎችን የሚያስተዳረው ሙቨንፒክ አለም አቀፍ ሆቴልና ሪዞርት፤ ዮቤክ የንግድ ስራ ድርጅት ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ የሚያስገነባውን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለማስተዳደር ስምምነት ፈፀመ፡፡
 ከትላንት በስቲያ አመሻሽ ላይ በሸራተን ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የሙቨንፒክ ዓለም አቀፍ ሆቴልና ሪዞርት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዮቤክ ንግድ ስራ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኔ ግደይ ገ/እግዚአብሔር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የሆቴል ባለሀብቶችና በርካታ እንግዶች ተገኝተው ነበር፡፡
ሙቨንፒክ ሊያስተዳድረው የተስማማውና ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ያለው ሆቴሉ ግንባታው 60 በመቶ መጠናቀቁ በዕለቱ የተገለፀ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ ሁሉ ነገር አልቆ አገልግሎት እንደሚጀምር የድርጅቱ ባለቤት ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል፡፡ ሆቴሉ 252 የተለያየ ደረጃ ያላቸው የመኝታ ክፍሎች፣ 3 የምግብ አዳራሾች፣ (1 የሙሉ ሰዓት፣ 1 የጣሊያንና 1 የኤስያ ምግብ ቤት) ሶስት ባሮች (ሎቢ ባር፣ ስፖርት ባርና የመዋኛ ገንዳ አጠገብ የሚገኝ ባር)፣ 1600 ሰው ከሚይዘው ጀምሮ የተለያየ መጠን ያላቸው 6 የስብሰባ አዳራሾች፣ 1,350 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸውና በወር 3 ሺህ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ የሚችል የስፓ አገልግሎት፣ ከ400 በላይ ተሸከርካሪዎች የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያና እና ሌሎችም በርካታ አለም አቀፍ አገልግሎት እንደሚሰጥ በዕለቱ ተገልጿል፡ ሆቴሉ በ2011 ተከፍቶ ስራ ሲጀምር ለ700 ቋሚና ለ450 ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ባለቤቶቹ ተናግረዋል፡፡
የሙቨንፒክ ኃላፊዎች በስምምነቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሆቴል እንድናስተዳድር ጥያቄ ሲቀርብልንና ወደ ኢትዮጵያ መጥተን አገሪቱን ስንመለከት እስከዛሬ ባለመምጣታችን ይቆጨናል›› ያሉ ሲሆን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎቶችን ለማስፋት እንደሚጥሩ ገልፀው በአፍሪካ፣ በኤስያና በአውሮፓ እያስተዳደሯቸው የሚገኙትን ሆቴሎች በዘጋቢ ፊልም ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡
ይህ ስምምነት እውን እንዲሆን የማደራደሩን  እና የማስተባበሩን ሂደት ያለ ድካም ያካሄደውን የኦዚ የሆቴልና የሆስፒታሊቲ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቁምነገር ተከተልን ሁለቱም ወገኖች አመስግነዋል፡፡
ዮቤክ የንግድ ድርጅት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ውጤታማ የንግድ ስራዎች ተሰማርቶ ሲሰራ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን ከስራዎቹም ውስጥ የፒፒ ከተጢት፣ ኮንድዊት፣ ፒቪሲ ቧንቧ፣ የኤሌክትሪክ ኬብሎች ማምረቻና የISO የምስክር ወረቀት ያላቸው የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች አስመጪና አከፋፋይ፣ … ይገኙበታል፡፡ ድርጅቱ በ2004 ዓ.ም ወደ ሪል እስቴት ግንባታ በመግባትም ውጤታማ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡ የሆቴል አስተዳደሩን ስምምነት በዮቤክ በኩል የአቶ ብርሃኔ ልጅ የ26 ዓመቱ  ዮናስ ብርሀኔ ከሙቨንፒክ ጋር ተፈራርሟል።  

Read 1591 times