Monday, 13 March 2017 00:00

ግዙፉ ራስ ወዳድ

Written by  ድርሰት- ኦስካር ዋይልድ ትርጉም - ተፈራ ተክሉ
Rate this item
(9 votes)

ሁልጊዜ ከሰዐት በኋላ ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ፣ በግዙፉ ሰው የአትክልት ቦታ ውስጥ እየሄዱ መጫወት ያዘወትሩ ነበር፡፡ ሰፊና ደስ የሚል የአትክልት ቦታ ነው፤ በለስላሳ አረንጓዴ ሳር የተሸፈነ፡፡ አልፎ አልፎ በሳሩ ላይ እንደ ኮከብ የሚያማምሩ አበቦች በቅለዋል፤ በፀደይ ወራት ፈንድተው ለስልሰው የሚፈኩ፣ በበልግ ወራት ደግሞ በደንብ የሚያፈሩ አስራ ሁለት የኮክ ዛፎች አሉ፡፡ ወፎቹ በዛፎቹ ላይ አርፈው ጣፋጭ ዜማቸውን ሲያዜሙ፣ ልጆቹ ጨዋታቸውን እየገቱ ያዳምጧቸው ነበር፡፡  “እዚህ እንዴት ደስተኛ ነን!” ይባባላሉ፤ እርስ በርሳቸው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ግዙፉ ሰውዬ ከሄደበት  ተመለሰ፡፡ አስፈሪውን ጓደኛውን ለመጎብኘት ሄዶ ለሰባት ዓመታት አብሮት ቆይቶ ነበር የመጣው። ከሰባት ዓመታት በኋላ ማለት የሚፈልገውን ሁሉ ብሎ (ንግግሮቹ ውስን ነበሩ) ወደ ግንቡ ለመመለስ ወሰነ፡፡ እንደደረሰም ልጆቹ በአትክልት ቦታው ላይ ሲጫወቱ አያቸው፡፡
“እዚህ ምን እየሰራችሁ ነው?” ሲል አምባረቀ በሻካራ ድምጹ፤ ልጆቹም ከመቅጽበት ተፈተለኩ።
“የእኔ የአትክልት ቦታ፣ የእኔ የአትክልት ቦታ ነው” አለ ግዙፉ፤ “ያንን ማንም ይረዳል፤ እናም ከእኔ ውጭ ማንም እንዲጫወትበት አልፈቅድም።”
ስለዚህም ዙሪያውን ትልቅ ግድግዳ ገነባበትና የማስታወቂያ ሰሌዳ ሰቀለበት፡፡
አጥሩን ጥሰው የሚገቡ በሕግ ይዳኛሉ!
ሰውየው በጣም ራስ ወዳድ ግዙፍ ነበር፡፡
አሁን አሳዛኞቹ ሕጻናት የሚጫወቱበት ሥፍራ  የላቸውም፡፡ መንገድ ላይ ሊጫወቱ ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን መንገዱ አቧራማና ድንጋያማ ስለነበር አልወደዱትም፡፡ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ትልቁን ግድግዳ እየዞሩ፣ በውስጡ ስለሚገኘው የሚያምር የአትክልት ቦታ ያወሩ ነበር፡፡ “እዚያ ውስጥ እንዴት ደስተኞች ነበርን!” ይባባላሉ፡፡
ፀደይ ሲመጣም አገሩ በሙሉ በፈኩ አበቦችና በወፎች ይሞላል፡፡ በራስ ወዳዱ ግዙፍ የአትክልት ቦታ ብቻ እስካሁን ክረምት ነበር፡፡ ምንም ልጆች ስላልነበሩበት ወፎቹ ሊዘምሩበት ግድ አልነበራቸውም፤ ዛፎቹም መፍካቱን ረስተውት ነበር፡፡ አንድ ቀን አንዲት የምታምር አበባ ከሳሩ መሀል ራሷን ብቅ አደረገች፤ ነገር ግን የማስታወቂያ ሰሌዳውን ስትመለከት ለልጆቹ በጣሙን አዝና ወደ መሬቱ ተመልሳ በመግባት ተኛች፡፡ የተደሰቱት በረዶና ውርጭ ብቻ ነበሩ። “ይህንን የአትክልት ቦታ ፀደይ ረስቶታል” አሉ ጮክ ብለው፤ “ስለዚህ ዓመቱን በሙሉ እዚህ እንኖራለን፡፡” በረዶ ሳሩን በታላቁ ነጭ ካባዋ አለበሰችው፤ ውርጭም ሁሉንም ዛፎች ብርማ ቀለም ቀባቻቸው፡፡ ከዚያም የሰሜኑን ነፋስ ከእነርሱ ጋር እንዲቆይ ጋብዘውት ስለነበር በግብዣቸው መሠረት መጣ፡፡ በለምድ ተሸፋፍኖ ነበር፤ ቀኑን ሙሉም በአትክልት ቦታው ውስጥ ሲያጓራ ዋለ፤ የጭስ መውጫ ቱቦዎችንም ወዝውዞ ጣላቸው፡፡ “ይህ ደስ የሚል ቦታ ነው” አለ፤ “በረዶ የቀላቀለ ዝናብን እንዲጎበኘን መጠየቅ አለብን፡፡” ስለዚህ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ መጣ። በየቀኑ ለሦስት ሰዐታት የጣራውን ልባስ ጥቁር ድንጋዮች ሲቆፈቁፋቸው ብዙዎቹ ተሰባበሩ፤ ከዚያም የአትክልት ቦታውን በቻለው ፍጥነት ተሽከረከረበት፡፡ ግራጫ ለብሶ ነበር፤ ትንፋሹም በረዶ በረዶ ይል ነበር፡፡
“ፀደይ ለምን እንደዘገየ ሊገባኝ አልቻለም” አለ ግዙፉ ራስ ወዳድ፡፡ መስኮቱ አካባቢ ተቀምጦ ቀዝቃዛውንና ነጩን የአትክልት ቦታውን እየተመለከተ፤ “የአየር ንብረቱ ይለወጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡” ሲል ለራሱ ተናገረ፡፡
ነገር ግን ፀደዩም ሆነ በጋዉ በፍጹም አልመጡም፡፡ በልግ ለሁሉም የአትክልት ቦታዎች ወርቃማ ፍሬ ሰጠች፤ ነገር ግን ለግዙፉ የአትክልት ቦታ ምንም አልሰጠችም፡፡ “በጣም ራስ ወዳድ ነው” አለች፡፡ ስለዚህ እዚያ ሁሌ ክረምት ነበር፤ እናም የሰሜኑ ነፋስ፣ በረዶ የቀላቀለው ዝናብ፣ ውርጭና በረዶ በዛፎቹ ውስጥ በዳንስ ተሽከረከሩ።
ከዕለታት አንድ ጥዋት ግዙፉ ዐይኑ እንደፈጠጠ አልጋ ላይ ተጋድሞ እያለ ደስ የሚል የሙዚቃ ድምጽ ሰማ፡፡ ለጆሮዎቹ በጣም ጣፋጭ ድምጸት ስለነበረ የንጉሡ ሙዚቀኞች እያለፉ መሆን አለበት ሲል አሰበ፡፡ በእውነቱ አንድ ትንሽ ወፍ ብቻ ነበር ከመስኮቱ ውጭ ሆኖ የሚዘምረው፡፡ ነገር ግን ወፍ በአትክልት ቦታው ውስጥ ሲዘምር ከሰማ ረዘም ያለ ጊዜ ስለሆነው ለሱ በአለም እጅግ የሚያምረው ሙዚቃ መስሎ ነበር የተሰማው። ከዚያም በረዶ የቀላቀለው ዝናብ በጭንቅላቱ ላይ መደነሱን አቆመ፣ የሰሜኑ ነፋስም ማጓራቱን አቆመ፣ የሚያምር ሽቶም በመስኮቱ ጠርዝ ክፍተት በኩል አድርጎ ወደሱ መጣ፡፡ “በመጨረሻ ፀደይ እንደመጣ አምናለሁ” አለ ግዙፉ፤ ከአልጋው ላይ ዘሎ ወርዶም ወደ ውጭ ተመለከተ፡፡
ምን ዐይቶ ነበር?
እጅግ የሚደንቅ ነገር ነበር ያየው፡፡ ልጆቹ ግድግዳው ላይ ባለው ትንሽ ቀዳዳ ሾልከው ገብተው በዛፎቹ ቅርንጫፎች ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ ማየት በሚችለው ዛፍ ላይ ሁሉ ትንሽ ልጅ አለ፡፡ ዛፎቹም ልጆቹ በመመለሳቸው እጅግ ከመደሰታቸው የተነሳ ራሳቸውን ፍካት አልብሰውና ክንዶቻቸውን በቀስታ ከልጆቹ ጭንቅላቶች በላይ እያወዛወዙ ነበር፡፡ ወፎቹም በደስታ ወደዚህና ወደዚያ እየበረሩና እየተንጫጩ ነበር፡፡ አበባዎቹ ደግሞ ከሳሩ ውስጥ ወደ ላይ ቀና ብለው እያዩና እየሳቁ ነበር። ደስ የሚል ትዕይንት ነበር፣ በአንድ ጥግ ብቻ ክረምት እንደቀጠለ ነበር፡፡ የአትክልት ቦታው የመጨረሻ ጥግ ነበር፤ በአካባቢውም አንድ ትንሽ ልጅ ቆሟል፡፡ በጣም ትንሽ ስለነበረ የዛፉ ቅርንጫፎች ላይ መድረስ አልቻለም፤ እናም አምርሮ እያለቀሰ ዛፉን ይዞረው ነበር፡፡ አሳዛኙ ዛፍ እስካሁን በከፍተኛ ውርጭና በረዶ እንደተሸፈነ ነበር፤ የሰሜኑ ነፋስም በላዩ ላይ እየነፈሰና እያጓራ ነበር፡፡ “ትንሹ ልጅ፤ እኔ ላይ ውጣ!” አለ ዛፉ፡፡ ዝቅ ማለት እስከሚችለውም ድረስ ቅርንጫፎቹን ወደ ታች ዘንበል አደረገለት፤ ነገር ግን ልጁ በጣም ትንሽ ነበር፡፡
ይህንን ሲመለከት የግዙፉ ልብ ቀለጠች። “እንዴት አይነት ራስ ወዳድ ነበርኩ!” አለ፤ “ፀደይ እዚህ ለምን እንደማይመጣ አሁን አወቅኩ፡፡ ያንን አሳዛኝ ትንሽ ልጅ የዛፉ ጫፍ ላይ አስቀምጠዋለሁ፣ ከዚያም ግድግዳውን አፈርሰዋለሁ፣ የአትክልት ቦታዬም ሁልጊዜና እስከዘላለም የልጆቹ መጫወቻ ሥፍራ ይሆናል።”
ከዚህ በፊት ላደረገው ነገር ከምር አዘነ፡፡
ቀስ ብሎ ወደ ምድር ቤቱ ወርዶም የፊተኛውን በር በቀስታ ከፍቶ ወደ አትክልት ቦታው ሄደ፡፡ ነገር ግን ልጆቹ እንዳዩት በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ ሁሉም ሮጠው አመለጡ፡፡ በአትክልት ቦታውም እንደገና ክረምት ሆነ፡፡ ትንሹ ልጅ ብቻ ሳይሮጥ ቀረ፤ ዐይኖቹ በዕንባ ስለተሞሉ ግዙፉ ሲመጣ ማየት አልቻለም ነበር፡፡ እናም ግዙፉ ከኋላ አፈፍ አድርጎ አንስቶት በእጆቹ ቀስ አድርጎ ይዞት ዛፉ ላይ አስቀመጠው፡፡ ዛፉም በአንዴ ፍክት አለ፣ ወፎችም እላዩ ላይ አርፈው መዘመር ጀመሩ፡፡ ትንሹ ልጅም ሁለቱን ክንዶቹን ዘርግቶ፣ በግዙፉ አንገት ላይ ጠመጠማቸውና ሳም አደረገው። ሌሎቹ ልጆችም ግዙፉ እንደቀድሞው ክፉ እንዳልሆነ ሲያዩ እየሮጡ ተመለሱ፤ ከእነርሱ ጋርም ፀደዩ ተመለሰ፡፡ “ትንንሾቹ ልጆች፤ አሁን የእናንተ የአትክልት ቦታ ነው” አለ ግዙፉ፤ በትልቅ መጥረቢያም ግድግዳውን አፈረሰው። ሰዎች ወደ ገበያ ሲሄዱም ከዚህ በፊት ካዩት ሁሉ በላቀ የሚያምር የአትክልት ቦታው ውስጥ ግዙፉ ከልጆቹ ጋር ሲጫወት አገኙት፡፡
ቀኑን ሙሉ ሲጫወቱ ዋሉ፡፡ ሲመሽም ሊሰናበቱት ወደ ግዙፉ መጡ፡፡
“ታዲያ ትንሹ ጓደኛችሁ የት አለ?” አለ፤ “ዛፉ ላይ ያስቀመጥኩት ልጅ፡፡” ስለሳመው ግዙፉ ከሌሎቹ አስበልጦ ወዶት ነበር፡፡
“አላወቅንም” ልጆቹ መለሱ፤ “ሄዷል፡፡”
“እርግጠኛ እንዲሆንና ነገ እንዲመጣ መንገር አለባችሁ” አለ ግዙፉ፡፡
ነገር ግን ልጆቹ የት እንደሚኖርና ከዚህ በፊትም አይተውት እንደማያውቁ ነገሩት፤ ግዙፉም በጣም ሐዘን ተሰማው፡፡
ሁሌ ከሰዐት፣ ከትምህርት ቤት መልስ፣ ልጆቹ እየመጡ ከግዙፉ ጋር ይጫወቱ ነበር፡፡ ነገር ግን ግዙፉ የሚወደው ትንሽ ልጅ በፍጹም እንደገና ታይቶ አያውቅም፡፡ ግዙፉ ለሁሉም ልጆች ደግ ነበር፤ ሆኖም የመጀመሪያ ጓደኛውን ናፈቀ፤ ስለሱም በተደጋጋሚ ያወራ ነበር፡፡ “ባየው እንዴት ደስ ይለኝ ነበር!” ይል ነበር፡፡
ዓመታት አለፉ፤ ግዙፉም እያረጀና እየደከመ ሄደ፡፡ እንደ ቀድሞው መጫወት አልቻለም፤ ስለዚህ በትልቅ ባለመደገፊያ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚጫወቱትን  ልጆች ይመለከታል፤ የአትክልት ቦታውንም ያደንቃል፡፡
“ብዙ የሚያማምሩ አበባዎች አሉኝ” አለ፤ “ነገር ግን ልጆቹ ከሁሉም የላቀ የሚያምሩ አበባዎች ናቸው፡፡”
በአንድ የክረምት ጠዋት ልብሱን እየለባበሰ እያለ በመስኮቱ ወደ ውጭ ተመለከተ፡፡ አሁን ክረምቱን አይጠላውም፤ ምክንቱም ፀደዩ ሌላ ነገር ሆኖ ሳይሆን እንቅልፍ እንደወሰደው፣ አበባዎቹ ደግሞ እረፍት ላይ እንደነበሩ ያውቃል።
በድንገት በግርምት ተውጦ ዐይኖቹን አሻሻቸው፤ ወደ ውጭም መመልከቱን ቀጠለ። በእርግጥም ድንቅ ትዕይንት ነበር፡፡ በአትክልት ቦታው የመጨረሻው ጥግ ጋ የሚገኝ አንድ ዛፍ በሚያምሩ ነጭ አበቦች በእጅጉ ተሸፍኖ ነበር። ቅርንጫፎቹ በሙሉ ወርቃማ ሆነው ነበር፤ ብርማ ፍሬዎችም ተንጠልጥለውባቸዋል፤ ከበታቹም የሚወደው ሕጻን ቆሟል፡፡
በከፍተኛ ደስታ ተውጦ ግዙፉ ወደ ታችኛው ክፍል ሮጠ፣ ከዚያም ወደ አትክልት ቦታው ወጣ። ሳሩን በፍጥነት አቋርጦ ሄዶ ወደ ሕጻኑ ቀረብ አለ። በጣም ቀረብ ሲል ፊቱ በንዴት ቀላ። “ማን ነው ሊያቆስልህ የደፈረው?” ምክንያቱም በልጁ እጆች መዳፎች ላይ የሁለት ምስማር ምልክቶች፣ በትንንሾቹ እግሮቹ ላይም የሁለት ምስማር ምልክቶች ነበሩ፡፡  
“ማን ነው ሊያቆስልህ የደፈረው?” ግዙፉ ጮኸ፤ “ንገረኝ፡ ትልቁን ጎራዴዬን ልወስድና ልገድለው እችላለሁ፡፡”
“አይደለም!” ልጁ መለሰ፤ “እነዚህ የፍቅር ቁስሎች ናቸው፡፡”
“አንተ ማን ነህ?” አለ ግዙፉ፡፡
እንግዳ የሆነ ትልቅ የማክበር ስሜት ተሰማው። በትንሹ ልጅ ፊትም ተንበረከከ፡፡
ልጁም ለግዙፉ ሰውዬ ፈገግ አለለት። እንዲህም አለው፡- “አንዴ በአትክልት ቦታህ እንድጫወት ፈቅደሃል፤ ዛሬ ወደ እኔ የአትክልት ቦታ አብረኸኝ መምጣት አለብህ - ገነት ነው፡፡”
ልጆቹም ከሰዐት በኋላ እየሮጡ ወደ አትክልት ሥፍራው ሲሄዱ፣ ግዙፉ ሰውዬ፤ በነጭ አበባዎች ተሸፋፍኖ ከዛፉ ሥር ሞቶ አገኙት፡፡  

Read 2856 times