Monday, 13 March 2017 00:00

አዝማሪና ሙያው ሲፈተሽ

Written by  ታደለ ገድሌ (ዶ/ር
Rate this item
(2 votes)

 የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ዓባይ የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ በባህላዊው የአዝማሪ ጥበብ ዙሪያ ሦስተኛ አገር አቀፍ ጉባኤ የካቲት 16 እና 17 2009 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የስብሰባ አዳራሽ አካሂዷል። “አዝማሪና ሙያው የጥበብ መድረክ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ጉባኤ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክብር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሴ ያዕቆብና አቶ አያልነህ ሙላቱ፤ የጥናት ወረቀት አቅራቢዎች፣ በባሕር ዳር ከተማ ከተቋቋሙ ዕዝራ የአዝማሪዎች ማኅበርና ከሌሎች ቦታዎች የተጋበዙ አዝማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡ የኅትመት ብርሃን ያረፈበትና የሁለተኛውን ዓመት ጉባኤ ፍሬ ሐሳብ የያዘ ጆርናልም በዕለቱ ለእንግዶች ተበርክቷል፡፡
በጉባኤው ላይ ዶ/ር ዋልታንጉሥ መኮንን ባቀረቡት አጭር ማስታወሻ፡- ፈጣሪ ዓለምን ሲፈጥርና ፍጥረታትን በየመልኩ ሲደለድል ሙዚቀኞች፣ ብረት ሰሪዎች፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ተብለው የተከፋፈሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ብርሃናትን የለበሱ መላእክትም ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ፈጣሪን በማመስገን የተወሰኑ ሲሆን ሙዚቃም ከፈጣሪ ለሰው ልጅ መገልገያ እንድትሆን የተሰጠች ናት፤ብለዋል፡፡
የማዕከሉ ዲሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አንዱዓለም ባደረጉት የመግቢያ ንግግርም፡- “ሀገራችን የልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች፣ ለቱሪዝም መስህብነት የሚያገለግሉና ታሪካዊነት ያላቸው ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ቤተ መንግስቶችና ልዩ ልዩ የቱሪስት መስህቦች፣የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃብቶች ባለቤት ስለሆነች እነዚህ ሃብቶቿ በአግባቡ ተይዘውና በጥናትና ምርምር ዳብረው ልማቷንና እድገቷን ማፋጠን አለባቸው፡፡” ብለዋል፡፡ አዝማሪዎች በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት፤በዕረፍትና በጥናት ወረቀቶች ፍጻሜ ወቅት ጣልቃ እየገቡ በአሰሙት ሙዚቃ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶና ፉከራ ተሰብሳቢውን በእጅጉ አስፈንድቀውታል፡፡ ጉባኤው የተጀመረው ድምጽ፣ የሙዚቃ መሳሪያና ቃለ ግጥም ኅብር ፈጥረው፣ በአዝማሪ ማሲንቆ በተቀነቀነ መንፈሳዊ የ”ክበር ተመስገን ጌታችን” ዜማ ነው፡፡
“ክበር ተመስገን ጌታችን፣
ለዚህ ላደረስከን፡፡
ውለታው ብዙ ለእግዚአብሔር፣
አመስጋኝማ ቢኖር፡፡ …
ድንገት ገብቼ ከጭስ ቤት፣
ቋንጣ ጠብሸ ለመብላት፤
ወድቄ ነበር ከእሳት ላይ
ሥጋ ሥጋየን ሳይ፡፡
    እመቤታችን የዓለም ቤዛ፣
    ተሰድዳ ነበር ልጇን ይዛ፤
    ምን አሳሰባት ለእኛ ሰው፣
     ዓለም በቃኝ ላለው፡፡ …
የዛሬ ዘመን ገበሬ፤
መሬት አያውቅም እስከዛሬ፤
ጭቃ ነው ብለህ አትተወው፤
ኧረ ሰው ዐፈር ነው፡፡ … ”
የቃለ ግጥሙና የዜማው ስልት ከዚህ ዘመን ላይ ያደረሰን ፈጣሪ አምላካችን ምስጋና እንደሚገባው፤ ግን የእርሱ ውለታ ብዙ ቢሆንም ሥራዬ ብሎ የሚያመሰግን ሰው እንደሌለ ያስረዳናል፡፡ ሰው ከነፍሱ ይልቅ ለሥጋው ስለሚያደላ ወደ ሲዖል እንደሚገባ፤ እመቤታችን ማርያምም ፍጥረቱን ለማዳን ልጇን ይዛ ወደ ምድረ ግብጽ እንደተሰደደች ከቃለ ግጥሙ እንረዳለን፡፡ ሰው ሁሉ ዐፈር ትቢያ ከመሆን እንደማያመልጥም እንገነዘባለን፡፡
ከዚያም አዝማሪዎች ወደ ዘመናዊ የሙዚቃ ስልት ዞረው በአማረ፤ በሚስብ፣ ላህይና ቃና በዓለመው ድምጻቸውና የማሲንቆ ግርፋቸው፡-
“የፈረንጅ መሳሪያ ቢመጣ አሸብርቆ፤
ያገር ባህላችን እንዴት ነሽ ማሲንቆ፡፡
ጌጡም አበባውም እዚያው ይቀመጥ፤
ማሲንቆ ይበቃል ለአዝማሪዎች ጌጥ፡፡
አዝማሪና ዶሮ የለውም አዝመራ፤
ታበላዋለች እናቲቱ ጭራ፡፡
ቆንጆ ሚስት አግብቶ ጎረቤትን ማመን፣
ሽምብራ መዝራት ነው ትል በሆነ ዘመን፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራችን፤
ዘለዓለም ኑሪልን ኢትዮጵያ አገራችን፡፡
ሳሉ መጠያየቅ ሳሉ መተባበር ይተውና ዘመድ፤
ሲሞት ወየ ወየ ይመስለኛል ማበድ፡፡
አምባሰል ተንዶ ማሽን ደግፎታል፣
የቆመውን አውሬ የተኛው መግደሉ፣
ስፍራ በመያዝ ነው በመደላደሉ፡፡
አምባሰል መናዱ ያንቺ ቃል ማፍረስ ነው፤
ግሸን መደገፉ የእኔ ቃል ማክበር ነው፤
ይብላኝ እንጂ ለአንቺ ቃልሽን ለአፈረስሽው፤
መች የእጁን ያጣዋል ቆሞ ከሔደ ሰው፡፡
---- እያሉ በማዜም ጉባኤተኛውን አዝናንተውታል፤ በተለይም አንድ ወንድና አንዲት ሴት አዝማሪ የዐድዋንና የማይጨውን ጦርነት፤ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ተጋድሎ በማነሳሳት፣ በአሰሙት ቀረርቶና ሽለላ የታዳሚውን ቀልብ ለመሳብ ችለዋል፡፡
“ኧረ መገን ኧረ ወንዱ ኧረ ያ ሰው ጅል ነው፤
ሲሰድቡት ዝም  ሲመቱትም ያው ነው፡፡
ኧረ ጎራው ኧረ ጀግናው
በመሳሪያ ብዛት እነርሱ ቢያይሉ
በደቦል ድንጋይ ነው ጀግኖች የሚገድሉ፡፡
ኧረ ተው አንተ ሰው ስሮጥ አታባርረኝ፤
    አንተም አበዛኸው እኔንም መረረኝ፡፡
አባቴ ትልቅ ነው ይላል የሰው ሞኝ፤
ትንሹም ትልቅ ነው እንጀራ ሲያገኝ፡፡
ጭልጥ ነው እልም ነው ውኃ አይላመጥም፤
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም፡፡
አሜሪካ ሔጄ ሳላውቀው ልኖር፤
ኢትዮጵያ አገሬ አንች የብር አምባር፡፡
ሙያውን ሳያውቁት እንዲህ ተናንቆ፤
ዓለም አስደናቂ እንዴት ነሽ ማሲንቆ፡፡
አዝማሪ ይሉናል ፍቺው ያልገባቸው፤
የተበላሸ አንጎል ስላደስንላቸው፡፡
አሞኝ ውሎ አሞኝ ሊያድር ነወይ፤
ይኽ ሠርቶ መብላት ጤና ላይሆን ነው ወይ፡፡
ገፋ ገፋ አድርገህ ውጣው አቀበቱን፤
ልብ ያሰበው ነገር አይገኝ ዕለቱን፡፡
አፍርሷት ጎጆየን ቁንጮዋን ይዛችሁ፤
መቼም ቤት አልሠራ እናንተ እያላችሁ፡፡››
‹‹አዝማሪና ሙያው የጥበብ መድረክ›› በሚል ለሁለት ቀናት በተካሔደው የአዝማሪ ጉባኤ፤ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ዜማና ማሕሌት ገምቦ ለባህላዊውና ለዘመናዊው የሀገራችን ሙዚቃ መሰረት መሆኑን የሚያስረዳ ጥናት በሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ቀርቧል፡፡ እንደዚሁም የክብር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ ባህላዊውን ሙዚቃ ከዘመናዊ የጃዝ ሙዚቃ ጋር አዋሕዶ ለሀገራችን የሙዚቃ እድገት ታላቅ አስዋጽኦ ማድረጉንና በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ ሙዚቃ አምባሳደር መሆኑን የሚያስረዳ ጥናት ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ በመጡት ፕሮፌሰር ዶክተር አበበ ዘገየ ቀርቧል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ጥናት አቅራቢ ዶክተር አበባ አማረ፤”ሽምብሩት” በተባለው ልቦለድ ውስጥ አዝማሪ ገጸ ባህርያት እንዴት በአሉታዊና በአወንታዊ መልክ እንደተሣሉ ተንትነዋል፡፡ በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙት ዶክተር ፍሬሕይወት ባዩ፤ የመንዙማ ባህል በአላባ ብሔረሰብ፣ በቋንቋው በሀላቢኛ ሲቀርብ ምን እንደሚመስል፤ በአቶ መስፍን መሰለ ደግሞ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩ የአዝማሪ ቃል ግጥሞችን በማውሳት፣ መዲና አጫጭር ግጥም ሆኖ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደሚውልና ዘለሰኛ የወል ቤት አገጣጠምን ተከትሎ ለፍቅር፤ ለኅዘን፣ ሰንጎ መገን ደግሞ ጀግንነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የሚያስረዳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ እንደዚሁም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሃይማኖታዊ፤ ፖለቲካዊና ልማታዊ የሆነው የአዝማሪ ሙዚቃ ለሀገር ታሪክ ያደረገውን አስተዋፅኦ የሚያስቃኝ ጥናት፤ አቶ እንዳለ ጌታ ከበደ በበኩሉ፤በአንድ ሰው ተዋኝነት በውዳሴ ላይ ስለ ተመሰረተው የጉራጌና የጌዲኦ ብሔረሰብ ሙዚቃ የሚያስረዳ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የክብር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ እንደገለጹት፡- “ሙዚቃ ሳይንስ፤ ሙዚቀኛው፣ አዝማሪ ደግሞ ሳይንቲስት ስለሆነ ሳይንሳዊነቱን ተቀብሎ ማጥናት ይገባል፡፡ ሙዚቃ ሲደረስና ሲጻፍ፤ የሙዚቃ መሳሪያዎች ተቀላቅለው ሲሰሩ ጥሩ ውጤት ሊመጣ  ይችላል፡፡ ሰው ራሱን ፈልጎ ማግኘት አለበት፡፡ የነፍስ ጥሪን ተቀብሎ የአንድ ሙያ ባለቤት መሆን ውጤታማ ያደርጋል፡፡ አንድን ሙያ ሳይፈልጉት ለእንጀራ መቁረሻና ለመከበሪያ ብሎ ማጥናት ተገቢ አይደለም፡፡”
በጉባኤው ላይ ጸሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚና ደራሲ አያልነህ ሙላቱ፤ አነጋጋሪና አመራማሪ የሆኑ አስተያየቶችን በመስጠትና ተገቢ ጥያቄዎችን በማቅረብ፣ የሞቀና የደመቀ ውይይት እንዲካሄድ ምክንያት ሆነዋል፡፡
ስለ አዝማሪ ሙዚቃ ጥንታዊ አመጣጥ፤ ስለአባ ውዴታዎችና ሐሚናዎች፤ አዝማሪዎች ሙዚቃቸው እንደ ማንኛውም ሙያ ታይቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ መከበር ሲገባው መናቁን፣ ልጆቻቸውም በትምህርት ቤት ሳይቀር “አንተ/አንቺ የአዝማሪ ልጅ” እየተባሉ ስለሚሰደቡና ስለሚያፍሩ አባቴ አስተማሪ፤ አናጺ፤ ሾፌር… ነው እያሉ እንደሚናገሩ ተወስቷል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዚህ መልኩ የተናቀው አዝማሪነት ትንሳኤ እንዲያገኝና ሙያውና ባለሙያዎቹ እንዲከበሩ ትኩረት ሰጥቶ፣በየዓመቱ በዘርፉ ጥናታዊ ጉባኤ ማካሄዱ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችንም የሚያበረታታና በአርአያነትም እንዲታይ ስለሚያደርግ በበለጠ እንዲጠናከር እግዜር ይርዳው፡፡

Read 985 times