Monday, 13 March 2017 00:00

የጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ ህይወት በጨረፍታ!

Written by  ደረጄ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 አርስጣጣሊስ በኋላም አፍላጦን፣ … የሰው ልጅ፣ በተለይ ከፍ ያለ ግብር ያለው፣ ቁንጮ ተብሎ የተወደሰ፣ የታላቅነት አበባ የተነሰነሰለት ጀግና … ስሙ መቃብር ውስጥ እንዳይቀር ያደረጉት እንዲሁ አይደለም፣ አንገብግቧቸው ነው፡፡ … የሰዎች የህይወት ታሪክ መፃፍ አለበት ብሎ ትልሙን ያስቀመጠ አርስጣጣሊስ ነው፡፡ ታዲያ እርሱ በጊዜው ቦታ ይሰጠው ለነበረው የጦር ጀግንነት ነበር ያንን ያመጣው፡፡ አፍላጦን ደግሞ … የጥበብ ሰዎችንም ጨመረ፡፡ አሁን አሁን፣ ጋዜጠኛውም፣ ሳይንቲስቱም የተሻለ ሥራ ከሰራ መጽሐፍት ይጠረዙለታል፣ ትውልድ ያነብብለታል!
እኛም ሀገር የግለ - ታሪክና የህይወት ታሪክ ጥራዞች ከቅርብ አመታት ወዲህ ወርቃማ ዘመን የሆነላቸው ይመስላል፡፡ በተለይ ደግሞ የቀድሞው ሰራዊት አባላት፣ ያለፈውን ታሪካዊ ሁነትና የራሳቸውንና የባልደረቦቻቸውን ተሳትፎ፣ ለትውልድ ለማሳወቅ የየአቅማቸውን መፃፍ ቀጥለዋል፡፡ እኛም ሁሉንም ባይሆንም እጃችን የገቡትንና የተሻሉ ናቸው ብለን ያመንባቸውን አንብበናል፡፡
በቅርቡ ያነበብኩትና “የዘመናዊ ውትድርና አባት” በሚል ርዕስ ስለ ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ በዓለምነህ ረጋሳ የተፃፈውም መጽሐፍ ከእነዚሁ ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ በ148 ገፆች የተጠረዘው መጽሐፉ፤ የገፅ ሽፋኑ ሙሉ በሙሉ በጀኔራሉ ፎቶግራፍ የተሞላ ነው፡፡ የመፅሐፉ የውጭ ሽፋን ላይ እንደሚታየው፣ የጄነራሉ የህይወት ዘመን ከ1906 – 1953 ዓ.ም ነው፡፡
ስለመጽሐፉ አስተያየት የሰጡት ኮሎኔል መለስ ተሰማ፤ ገና መግቢያው ላይ ካሰፈሩት ሀሳብ ስለ ጄነራሉ የምናገኘው ቁም ነገር አለ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“… ሰውየው በጦር ግንባር እንደ ወታደር የተዋጋ፣ እንደ ወታደር መሪ ያዋጋና ጀግና፣ ስለ አገሩ ፍቅር ልቡ የነደደ፣ ተጋድሞ የተገረፈ፣ በስቃይ ልቡ ያልተሸበረ፣ ቆራጥ፣ በዓላማው የጸና፣ የአገሩን ክብር በድል ያስገኘ፣ ለአገሩ መከታ የሚሆን አዲስ የጦር ኃይል የመሰረተ፣ ያሰለጠነ፣ ያስታጠቀ፣ ከሰለጠኑ የዓለም መንግስታት የጦር ኃይል ጎን ለመሰለፍ የሚችል ኃይል የገነባ፣ የተመሰከረለት፣ የሚከበር የሚደነቅ፣ በኢትዮጵያ የጦር ኃይሎችም ተቋም በወቅቱ መተኪያ ያልተገኘለት ጀኔራል፡፡ …”
… እያለ ፅሁፉ ይቀጥላል፡፡ በርግጥም በኢትዮጵያ የዘመናዊ ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ጀነራሎች ውስጥ እኒህ ሰው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌተናል ጀኔራል ከበደ ገብሬን ጨምሮ በጊዜው የነበሩ ወጣት መኮንኖች፣ ሀገሪቱ በወራሪ ጠላት በተጠቃችበት ጊዜ የሰለጠኑ በመሆኑ በእሳት ተፈትነዋል፡፡ ይህ ፈተና እነ ጄነራል መንግስቱ ነዋይንም ይጨምራል፡፡ ከዚህ ባሻገር በጊዜው የነበረው የክብር ዘበኛ ጦር፣ በደቡብ ኮሪያ በነበረው ተሳትፎ፣ በታሪክ ውስጥ እጅግ የሚያኮራ ጀብድ መፈፀሙን በርካታ መፅሀፍት አውስተዋል፡፡
ዓለምነህ ረጋሳ የፃፈውም የእኒህ ጄነራል ታሪክ ይህንን ዘመቻ ያካተተ ነው፡፡ ይሁንና የዚህ ዘውግ ምሁራን እንደሚሉት፤ የህይወት ታሪኩ የሚፃፍለት ሰው ቢቻል በህይወት ቢኖር፣ ባይቻል ከህልፈቱ በኋላ ብዙ ባይቆይ እንደሚመረጥ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ህይወቱ ካለፈ በኋላ ታሪኩ እየተረሳ፣ እማኝነት የሚሰጡ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ስለሚሄድ፣ የሚፃፈው የህይወት ታሪክ፣ በቂና የሚያመረቃ መረጃ ላይኖረው ይችላልና ነው፡፡
ታዲያ ይህንን የጄነራሉን ታሪክ ስናስብ የሚከነክነን ይህ ነው፡፡ ዘመኑ እጅግ የራቀ በመሆኑ ለፀሐፊው በእጅጉ ፈታኝና አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ የመጀመሪያ (first hand information) ማግኘቱ ከባድ ነው፡፡ ጓደኞች የትዳር አጋር፣ የቢሮና መሰል ባልደረቦች በሌሉበትና በድምፅ የተቀረፁ፣ በፊልም የተዘጋጁ መረጃዎች በሌሉበት ዘመን የተከወነን ነገር መተረክ ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ፀሐፊው አቶ አለምነህ ረጋሳ፤ አሁን የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የፕሮቶኮልና የኮሚኑኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር መሆናቸው ከሌላው ሰው የተሻለ መረጃ ለማግኘት የሚቀልላቸው ይመስላል፡፡ የጋዜጠኝነት የሥራ ልምድና ትውውቅም ለዚህ ጥሩ ግብዓት ነው፡፡ ብቻ መጽሐፉ ምን ያህል የተዋጣለትና በቂ መረጃዎችን ያካተተ ነው ወደሚለው ሳንገባ፣ የእኒህን ውድና ብርቅ የሀገር መኩሪያ ታሪክ ፅፈው ስላቀረቡልን አክብሮቴ ታላቅ ነው፡፡ ምክንያቱም እኒህን የሚያህሉ ሙሉ ጀግና ታሪካቸው በሌሎች ሰዎች ታሪክ ውስጥ እግረ መንገድ ሲጠቀስ መሰማቱ፣ ሀገሩንና ታሪኩን ለሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የቁስል ያህል የሚጠዘጥዝ ነው፡፡
ፀሐፊው እንዳስቀመጡት፤ ሙሉጌታ ቡሊ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ሮቢ ወረዳ ምሽጊ (ምሽግ) እየተባለ ይጠራ በነበረ የገጠር አካባቢ በ1906 ዓ.ም ነው ከእናታቸው ከወ/ሮ አየለች ቸሬና ከአባታቸው ቡሊ ሁንዬ ነው የተወለዱት፡፡ እኒህ ጀግና ለእናታቸውና ለአባታቸው አንድ ነበሩ፡፡ አባታቸው የራስ ብሩ ወታደር ሲሆኑ በተለያየ ስፍራ እየተዘዋወሩ ነው የኖሩት፡፡ ደምቢዶሎ (ወለጋ)፣ ሀገረ ሰላም (ሲዳሞ) ኖረዋል፡፡ በአባታቸውና በእናታቸው መካከል ሰፋ ያለ የዕድሜ ልዩነትም ነበረ፡፡ 19 ዓመታት ያህል! … ስለዚህም በጋብቻ አልቀጠሉም። … ከዚያ እናትየው ልጃቸውን ሙሉጌታን ይዘው ወደ ትውልድ ሀገራቸው በቾ ሄዱ፡፡ ቡሊም ወደ ቀድሞው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ተዛወሩ፡፡ ይሁንና ልጃቸውን ሙሉጌታን እግረመንገዳቸውን ሊጎበኙ ጎራ ሲሉ፣ ልጃቸው የአጎቱን ከብቶች የሚያሰማራ እረኛ ሆኖ አገኙት፡፡ ይሄኔ ትምህርት ቤት ያለመግባቱ ቆጫቸውና ልጃቸውን ጌጡን ከወለጋ አስጠርተው፣ ወንድሟን እንድታሳድግ አደረጉ፡፡
ከዚያም ሙሉጌታ ሀገረ ሰላም (ሲዳሞ) አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በኋላም ራስ ብሩና ንጉሠ ነገሥቱ ልጃቸውን የተሻለ ትምህርት ቤት እንዲያስገቡላቸው ባደረጉት ተማፅኖ፣ የንጉሱን አዎንታ አግኝተው፣ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት መማር ጀመረ፡፡ ወጣት ሙሉጌታም በጊዜው ሌትና ቀን በርትቶ በማጥናት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማዕረግ አጠናቀቀ፡፡
ከዚህ በኋላ ያለው ታሪክ የጦር አካዳሚና የሹመት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ ባለታሪኩ በህይወት የነበሩበት ጊዜ 51 ዓመታት ያህል በመራቁ፣ ስለ ልጅነታቸው ማወቅ የሚገባንን ብዙ ነገር አጥተናል፡፡ የዚህ ዓይነት ታላላቅ ሰዎችን ልጅነታቸውን መፈተሽ ደግሞ ብዙ ልምድና ትምህርት ያስገኛል፡፡ ለምሳሌ ናፖሊዮን ቦናፖርትን የመሰለ ጀግና በልጅነቱ የነበረውን የጦር ዝንባሌና የተለየ የቤት ውስጥ ባህርይ ስናይ፣ የቀጣይ ዘመኑ ምልክት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ … ታላቁ እንግሊዛዊ ዊንስተን ቸርችልም በልጅነቱ ያሳይ የነበረው አዝማሚያና የአሻንጉሊቶቹ ምርጫ፣ የቀጣይ ዘመኑን አድማስ ቀድሞ የሚያሳይ መነፅር ነበር፡፡ እነ ቶልስቶይን፣ እነ ቤንጃሚን ፍራንክሊንንም ማየት እንችላለን፡፡ ለዚህ ነው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ብቅ ያለው ዘመናዊ የህይወት ታሪክ አፃፃፍ ልጅነት ላይ ትኩረት ይደረግ የሚለው፡፡
የሜጀር ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ የጦር ትምህርት ቤት መልክ አልታየም፡፡ ትምህርቱ ምን ይመስል እንደነበር፣ አያሳይም፡፡ ይህ ምናልባት በወቅቱ ከነበረው የሀገሪቱ አጣዳፊ ችግር፣ ማለትም በፋሽስት ኢጣሊያ ጦር የሀገሪቱ መወረር የፈጠረው ጭጋግ ሸፍኖት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ምክንያቱም የሌተና ጄነራል ከበደ ገብሬን የህይወት ታሪክ የፃፉት ሺበሺ ሊሳም፣ ይህን ጉዳይ አልፈው ዋና ዋና የሆኑት ጉዳዮች ላይ ነው ያተኮሩት፡፡ እዬዬም ሲዳላ ነው ይመስላል፡፡
ከወታደራዊ (የክብር ዘበኛ) መኮንንነት ማግስት የነበረው ፈተና (ስደት)፣ ከዚያም በኋላ ከንጉሰ ነገሥቱ ጋር ተመልሶ፣ ክብር ዘበኛን እንደገና በማቋቋም ውስጥ የጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ሚና ታላቅ መሆኑ በሚገባ ተፅፏል፡፡
በኋላም፡-
ኮሪያ ነው ቤቴ፣ ኮሪያ ነው ቤቴ፣
ይብላኝ ለወለዱኝ እናትና አባቴ
አንበሳና ዝሆን ሆኗል ጎረቤቴ፡፡
… ተብሎ ነበር ወደሚባልበት የኮሪያ ልሳነ ምድር ዘመቻ ትኩረቱን አድርጓል፣ መጽሐፉ፡፡ ይህ ዘመቻ “ቃኘው” በሚል ርዕስ በጋሻው ድረሴ ወደ አማርኛ በተመለሰው የግሪካዊው ኮሞን ስኮርዲለስ መጽሐፍ ላይ በሚገባ ተተርኳል፡፡ ሺበሺ ለማ እንደፃፈው፤ ሶቪየት ሕብረትና ቻይና የኮሚኒዝምን የአገዛዝ ሥርዓት በሩቅ ምስራቅ ለማስፋፋት በነበራቸው ጥማት ነው ጦርነቱ የተቀሰቀሰው፡፡ … እናም ጦርነቱ በጊዜው የሰሜን ኮርያ መሪ በነበሩት ኪም ኤል ሱንግ የተቀነባበረና የሶቪየትና ቻይና እገዛ የነበረው ነው፡፡
በዚህ ዘመቻ ተሳታፊ የነበሩት የክቡር ዘበኛ አባላትን የመመልመል ኃላፊነት በሙሉጌታ ቡሊ ላይ ተጥሎ ነበር፡፡ መጽሐፉ እንዲህ ይተርካል (ገፅ 41)፡-
“… በወቅቱ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ሀገር ጦርነት ላይ የሚሳተፍ ሰራዊትን ወደ ውጭ ለመላክ የተዘጋጀችበት በመሆኑና የኢትዮጵያም ክብርና ዝና በዓለም የሚታወቀው በዘማቹ ሰራዊት ወታደራዊ ብቃት ስለነበር ዘመቻው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከዘመናዊ የዓለም ሰራዊት እንደ አንዱ የሚቆጠርበት፣ ነፃ ሀገሮች ሰላም ለማስከበር በጋራ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የራሱን ድርሻ ለወጣት ስለመቻሉም የሚወሰንበት ነበር፡፡ ንጉስ ኃይለሥላሴ ይህ ዘማች ጦር እንዲመሰረት ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት ከጣሉባቸው ጊዜ ጀምሮ የዘመቻው ዓላማ በብርጋዲየር ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሊ አእምሮ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ነበረው፡፡ … ዘመቻውም ኢትዮጵያዊያን እጅግ በጣም ውጤታማና የዓለምን ህዝብ ያስደነቀ ውጤት ያስመዘገቡበት ሆኗል፡፡
የቢቢሲ ጋዜጠኛ አሌክስ ላስት ከፃፈው ሻምበል ማሞ ሀብተወልድን ጠቅሶ፤ “እኛ እኮ ምርኮ ተዋጊዎች ነበርን፡፡ ሶስቱ የኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቆች በ253 ግንባሮች ተዋግተናል፡፡ እናም አንድም ኢትዮጵያዊ ወታደር በኮሪያ አልተማረከብንም … በጦር ሜዳ በፍፁም እንዳትማረክ የሚል ደንብ አለን፡፡ ይህ ብዙ ፈተና ቢያስከትልብንም ተግባራዊ አድርገነዋል፡፡” ሲል ፅፏል፡፡
“… አሜሪካዊውን አስር አለቃ ጨምሮ በዚያ ጦርነት 4 የቡድኔ አባላት ተገደሉ፤ ሁላችንም ቆሰልን። የሬዲዮ ኦፕሬተሬን ሊማርኩብኝ ሞከሩ፤ አነጣጥሬ ሊማርከው የነበረውን ወታደር ገድዬ ኦፕሬተሬን አዳንኩት፣ በዚያ ሁላችንም በቆሰልንበት አጋጣሚ ሁላችንንም በአንዴ ሊማርኩን መጡ ግን በያዝኩት ጠመንጃ ፈጀኋቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁኔታው እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡
ጦርነቱ ቀጠለ፣ ሌሊቱን በሙሉ ስንዋጋ አደርን - በመጨረሻም ጦሬ ተቆረጠ፡፡ … (ገፅ 78) ታሪኩ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
ይሁንና በዚህ ዐውደ ውጊያ የዋሉት አስራ አምስት ወታደሮች በዚህ በኩል (አንድ አሜሪካዊ የአሥር አለቃን ጨምሮ) ሲሆን፣ በዚያ በኩል ሦስት መቶ ወታደሮች ናቸው፡፡ ቁጥራቸው የቱን ያህል እንደሚራራቅ ልብ በሉ!?
መጽሐፉ የጀነራሉን የጋብቻ ህይወት አካትቷል። ባለቤታቸው ወ/ሮ አፀደ ሀ/ማርያምን እንዴት እንዳገቡና በመካከላቸው በነበረው ሰፊ የዕድሜ ልዩነትና በሌሎችም ምክንያቶች ጋብቻቸው እንዳልፀና ይነግረናል፡፡ ይህ ታሪክ ግን ከሌሎቹ ታሪኮች ቀድሞ መምጣት ነበረበት፡፡ አንዱ የሰዎችን የህይወት ቁመና፣ ጥንካሬና ድካም የምንለካበት ስፍራ ትዳር ስለሆነ ከቀጣይ ህይወታቸው ጋር እያዛመድንና እያመሳከርን ማንበብ ነበረብን፡፡
ወደ ማጠቃለያ ስንመጣ፣ የአፃፃፉ ውበትና ፍሰት ያን ያህል የተሳካ አይደለም፡፡ ቋንቋው ሙሉ ለሙሉ ወደ ጋዜጣ ዘገባ ያደላል ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ “ለመረዳት ተችሏል” … “መሆናቸውን ይገልፃል” … “ለማወቅ ተችሏል” … “መረጃዎች ይናገራሉ” .. ወዘተ የሚሉት ሀረጎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ መጽሐፉን ወደ ጋዜጣ ዘገባነት ያወርደዋል፡፡
ለምሳሌ ገፅ 8 ላይ “ለማወቅ ተችሏል፡፡” በሚል የተዘጋው ዐረፍተ ነገር፣ … “ወ/ሮ አፀደ ሀ/ማርያም በህይወት ሳሉ ተናግረው ነበር፡፡” … ቢባል የተሻለ ጣዕም ይኖረው ነበር፡፡
ሌላው እጅጉን ያዘንኩበት ጉዳይ ኮሎኔል መለሰ ተሰማ፤ የታሪክ መድልዎ መፈፀሙ ነው፡፡ ስለ ኮሪያ ዘማቾች አንስተው የተናገሩበት መንገድ አላማረኝም፡፡ ኃይለ ሥላሴን ከፍ፣ ደርግን አረመኔ አድርገው፣ ኢሕአዴግን ወላንሳ ብለውታል፡፡ “ለኢህአዴግ ምስጋና ይግባውና … እንድንደራጅ ፈቀደልን” ብለዋል፡፡ የዚህ ዓይነት የታሪክ መዛባት ለአሁንም ለሚቀጥለውም ዘመንም ደግ አይደለም፡፡ ትናንት አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ስለ ምኒልክ በፃፉት መፅሀፍ እያዘንን፣ በአሁን ዘመን የዚህ ዓይነት ሥራ መስራት ነውር ይመስለኛል፡፡ ለምን? … የትኛውንም የማንቀበለውን መንግስት  ጥሩ ስራ ማድበስበስ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንንስ በሽታ ዛሬውኑ ልናስወግደው ይገባል፡፡
ፀሐፊው እኒህን ታላቅ ጄነራል ስላስተዋወቁን ምስጋናዬ ታላቅ ነው፡፡ ምናልባትም መግቢያው ላይ ኮሎኔል መሰለ ተሰማ እንዳሉት፤ ዕድሜ ጨምሮላቸው እንደገና ጠለቅና ጠበቅ አድርገው ቢፅፉት ምኞቴ ነው! …

Read 617 times