Monday, 13 March 2017 00:00

“በእኔ አልተጀመረ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ ከርሞ፣ ከርሞ ለአቤቱታ ሄዷል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…እንዴት ከረምክ ብልህ ደግሞ ትቆጣኛለህ…
አንድዬ፡— አይ፣ በለኝ እንጂ…ለጤናህ እንደምን ከረምክ በለኝ! ስንት ነገር ትሉኝ የለ!… ዘዴው ጠፍቷችሁ እንጂ እንደ ዘንድሮ ሁኔታችሁ ለዙፋኔም አትመለሱም…
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ ጡር ይሆን… ይቅርታ አንድዬ፣ አምልጦኝ ነው...ይኸውልህ የኑሮው መላው ጠፍቶኝ እንዲህ ያዘባርቀኛል…
አንድዬ፡— ጡር ይሆንብሀል ነው ያልከኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አታካብድ…ይቅርታ አትቆጣ ማለቴ ነው! ምን ላድርግ፣ አንዳንዴ የምናገረው ለራሴም አይገባኝ…
አንድዬ፡— ጎሽ፣ አሁን ችግራችሁን አወቅህልኝ፣ ብዙዎቻችሁ የምትሉትን እንኳን እኔ ሊገባኝ እናንተም እንደማታውቁት ጠርጥሬ ነበር…አሁን ደግሞ ምን አቤት ልትለኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን አቤት የማልለው ነገር አለ!…የቱን አስቀድሜ የቱን እንደማስከትል ግራ ገብቶኝ ነው እንጂ ዘንድሮ ምን አቤት የማያስብል ነገር አለ!
አንድዬ፡— አሁን ምን ልትለኝ ነው የፈለግኸው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደው ሰው የሚባል ፍጥረት ዝር ወደማይልበት መኖሪያ ውሰደኝ…ለምን ሌላ ፕላኔት አይሆንም…ብቻ ሰው የሌለበት መኖሪያ አብጅልኝ…
አንድዬ፡— አሁን ደግሞ ምን አደረጉኝ ልትል ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ላስለፍልፈው ብለህ እንጂ አንተስ ሳታውቀው ቀርተህ ነው…
አንድዬ፡— ደግሞ ምኑን ነው የማውቀው…ጭራሽ እኔ የማውቀውንና የማላውቀውን ትነግረኝ ጀመር!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደ እሱ ሳይሆን… ያው ተሸፋፍነን ብንተኛ ገልጠህ ታየን የለ!
አንድዬ፡— እና የእንዳንዳችሁን ውሎና አዳር የምከታተለው ሥራ ፈት አደረጋችሁኝ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ በሌላ አትተርጉምብኝ!
አንድዬ፡— ደግሞ ተሸፋፍነን ብንተኛ ያልከው መሸፋፈን ትታችሁ የለም እንዴ! እኮ ንገረኛ… አሁን፣ አሁን ሁሉ ነገራችሁ በአደባባይ እየሆነ አይደለም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም አንድዬ፣ ቢሆንም የእኔ የተለየ ነው፡፡
አንድዬ፡— ልጠይቅህ እስቲ፣ ለመሆኑ እኔ ዘንድ ለመጨረሻ ጊዜ የመጣኸው መቼ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— በእርግጥ ምን አስዋሸኝ ትንሽ ከርሜያለሁ…ጧትና ማታ ቤትህ ብቅ ማለት የቀነስኩት ኑሮ እያሯሯጠኝ ነው፡፡
አንድዬ፡— ተመችቶኝ ነበር አትለኝም.
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ መች ተመቸኝ…መቼ ተመችቶኝ ያውቃል!
አንድዬ፡— ተው እንጂ… ገንዘብ በገንዘብ ሆነህ አልነበረም እንዴ፣ እኔን ትተህ ብርህን ማምለክ ጀምረህ አልነበር እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ኧረ እንደ እሱ አትበለኝ…
አንድዬ፡— በአንድ ጊዜ ባለቪላ ቤት፣ ባለመኪና ሆነህ አልነበረም እንዴ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይኸውልህ እሱ ነው ምቀኛ የሰበሰበብኝ፣ ብታይ ሁሉም ሰው በእኔ ላይ ተነስቷል…
አንድዬ፡— ገንዘብ አገኘህ ብለው ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ገንዘብ አገኘ ብለው፣ አለፈለት ብለው! ነው ኑሮዬን የማውቀው ግን እኔ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— ግን እንዴት ነው በአጭር ጊዜ ይሄን ሁሉ ሀብት ያገኘኸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ለፍቼ ነዋ አንድዬ፣ ለፍቼ ነዋ!…
አንድዬ፡— እኮ ንገረኛ …ሁሉም እኮ በአንድ ጊዜ እንዳንተ ብዙ ሀብት ማግኘት ይፈልጋል። ጧት ማታ የሚለምኑኝ ‘ሀብት ስጠኝ፣’ ‘ገንዘብ ስጠኝ፣’ ‘ሲነጋ ሀብታም አድርገኝ’ እያሉ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኔ እኮ ያቺን ታህል ለማግኘት የለፋሁትን፣ የደከምኩትን…መቼም ሳታውቀው አትቀርም፡፡
አንድዬ፡— ጭራሽ እኔኑ ልታታልለኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ አንድዬ እንደ እሱ አትበል…ደግሞ በእኔ አልተጀመረ!
አንድዬ፡— ለፋሁ፣ ደከምኩ የምትለው እኔን አያውቅም ብለህ ነው!…ምን እንዳሻሻጥክ፣ የትኛውን ሰነድ እንደሰረዝክ፣ እንደደለዝክ፣ ባልተገዛ እቃ ስንትና ስንት ሚሊዮን እንዳሳጣህ አያውቅም ብለህ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አ…አ…አንድዬ…እኔ…እኔ…
አንድዬ፡— ተሸፋፍነን ብንተኛ ገልጠህ ታየናለህ ብለህ አልነበረም…ደግሞ ለፋሁ ትላለህ! አንተ እኮ ገንዘብ ያገኘኸው የራስህን ላብ ሳይሆን ሌላው የለፋበትን ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደ እሱ እኮ አይደለም…
አንድዬ፡— እኮ በላ፣ በሀቅ ነው ያገኘሁት በለኛ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ያው…ምን መሰለህ፣ ጊዜው እኮ ነው፡፡ በእኔ አልተጀመረ! እኔ በዋናው መንገድ ስሄድ ሁሉም በአቋራጭ እያለፈኝ ላይ ሲደርስ ሆድ ባሰኝ…አንድዬ! የታክሲ ሙላልኝ ሲለኝ የነበረው ሁሉ በመኪና ውሀ እየረጨኝ ሲያልፍ ሆድ ባሰኝ! እኔ የኰንዶሚኒየም እጣ ስጠብቅ፣ በተከራየሁዋት የቀበሌ ቤት አዳብዬው የነበረው ጂ ፕላስ ስሪ ቤት ሲገዛ ሆድ ባሰኝ…አንድዬ! በጣም፣ በጣም ነው ሆድ የባሰኝ!…እኔስ ፍጡርህ አይደለሁም!  ጥሩ ኑሮ ቢኖረኝ አንተስ ደስ አይልህም…
አንድዬ፡— ጭራሽ! የማይገባህን ገንዘብ ስለሰበሰብክ ነው ደስ የሚለኝ! አትስረቅ፣ የሰው ገንዘብ አትመኝ ያልኩትን ስላፈረስክ ነው እኔን ደስ የሚለኝ! አንደኛውን አባሪ፣ ተባባሪህ ልታደርገኝ ነው እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደ እሱ ሳይሆን…በቃ ሰዉ የሚጠቀመውን ዘዴ ተጠቀምኩና ትንሽ አገኘሁ…ጓጓኋ አንድዬ፡ ጓጓኋ!
አንድዬ፡— እና ሰዉ ሁሉ እንደዛ ነው ማለትህ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይሄ በየመንገዱ የሚታየው መኪና ሁሉ በሀቅ የተገዛ መሰለህ! ይሄ ምን የመሳሰለ ቪላ ሁሉም በሀቅ የተሠራ መሰለህ!…ሁሏም ከጀርባዋ የሆነ ነገር አላት… በእኔ አልተጀመረ!
አንድዬ፡— ይቺን፣ ይቺን እንኳን የምትሉት ለራሳችሁ እንዲጠቅማችሁ ነው፡፡ የራሳችሁን ስርቆት  ለመሸፋፈን ሁሉንም አጭበርባሪ፣ ሁሉንም ከሀዲ፣ ሁሉንም ዘራፊ ታደርጉታላችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እመነኝ… ሁሉም ባይሆን አብዛኛው እንዲህ የሚንፈላሰሰው በላቡ ባመጣው ገንዘብ አይደለም…
አንድዬ፡— ከአንተ ጋር ማውራት ዋጋ የለውም፣ እሱን ተወውና ዛሬ ምን ልትለኝ ነው የመጣኸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አላስቀምጥ አሉኝ አንድዬ፣ አላስቀምጥ አሉኝ…
አንድዬ፡— የማይገባህን ወስደህ ሰላም ልታገኝ ታስባለህ?…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ… ያበደርኩህን ገንዘብ ካልከፈልከኝ እከስሃለሁ እያለ የሚዝትብኝን ሰው ብዛት አልነግርህም…
አንድዬ፡— ሳትበደራቸው ነው እንደዛ የሚሉህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— በእርግጥ ተበድሬያለሁ…ደግሞ መበደር በእኔ አልተጀመረ! ግን እኔ ገንዘብ ሳገኝ ነው እንዴ ማበደራቸው ትዝ የሚላቸው!…
አንድዬ፡— ብድርህን ካመንክ ክፈላ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ከየት አምጥቼ አንድዬ፣ ከየት አምጥቼ ልክፈላቸው…
አንድዬ፡— ያገኘኸው ያ ሁሉ ገንዘብ…ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያ ገዝተህ የለ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…የባሰ ደሞ አለ
አንድዬ፡— ምኑ ነው የባሰው?…
ምስኪን ሀበሻ፡— ቪላውን የሸጠለኝ ሰው በሀሰት ሰነድ ነው፣ ለካስ ባለቤቱ ሌላ ነው…
አንድዬ፡— ታዲያ አንተም በተራህ አትከሰውም….
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ … አገር ጥሎ ጠፋ! አንድዬ … ሦስት ሚሊዮን ብር አስከፍሎኝ አገር ጥሎ ጠፋ…
አንድዬ፡— ቤቱስ ምን ሆነ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ቤቱንማ ከእነዕቃው አሸጉብኝ…
አንድዬ፡— ለዚህ ነዋ እኔ ዘንድ የመጣኸው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሜዳ ላይ ቀረሁ እኮ!  እኔ ዜጋህ አጨብጭቤ ቀረሁልህ እኮ! ደግሞ እኮ አንድዬ … ቤቱን አትርፌ አምስት ሚሊዮን ልሸጠው አስማምቼ ስለነበር ሰባራ ሳንቲም አልተረፈኝም…
ምስኪን ሀበሻ፡— በል እንግዲህ ደህና ሁን… በሚያወጣው ያውጣሀ…
አንድዬ፡— አንድዬ ልትተወኝ! እንዲሁ ሜዳ ላይ ልትተወኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— በዘዴ ነው ገንዘብ ያገኘሁት ብለኸኝ የለ…አሁን ደግሞ በዘዴ ከችግርህ ውጣ…ይህንንም “በእኔ አልተጀመረ!” እንዳትለኝ! ዘንድሮ ሁልህንም እያጠፋህ ያለው ይሄ… “በእኔ አልተጀመረ!” የምትሉት ነገር ነው፡፡ ደህና ሁን፡፡
አንድዬ፡— አንድዬ! ኧረ…
ምስኪን ሀበሻ ጩኸቱን ቀጥሏል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1228 times