Monday, 13 March 2017 00:00

የክብደት መንበርና የሥልጣን ልዕልና!

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

 “Mass” የሚለውን ቃል ከዌብስተር ዲክሽነሪ ላይ ፍቺውን ስፈልግ እንደሚከተለው ይላል፡- “A quantity of matter or the form of matter, cohering together in one body or quantity, usually of considerable size … a general body of mankind, a nation etc”  
መዝገበ ቃላት ማለት ራሱ የቃላትን ክብደት በትርጉማቸው አማካኝነት የሚለካ የቃላት ፔሬዲክ ቴብል ነው፡፡ መዝገበ ቃላቱ “Mass” የሚለውን ቃል፤ “የድድር ክምችት፣ ቅንጣቶች፣ በስምምነት በአንድ አካል ቅርፅ የሚጠራቀሙበት፣ የሰው ልጆች ጥርቅምና፣ ሀገር ወዘተ” ብሎ ነው የፈታው፡፡
ልክ እንደ ፔሬዲክ ቴብሉ …ቃላትም በአይዘቶፕ (isotopes) መልክ ይገኛሉ፡፡ አንድ ቃል በድምፅና በፊደል ተመሳሳይ ሆኖ እንደ አገባቡ ትርጉሙና ክብደቱ የሚለያይበት ማለቴ ነው፡፡ “Isotopes” ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደ ቃል ነው፤ ትርጉሙም “አንድ አይነት ቦታ” (same place) እንደማለት ነው። ቃሉን ለአቶም የምርምር አለም እንዲሆን አምጥቶ ያጠመቀው ሰው “Soddy” ይባላል፡፡
“Mass” የሚለውም ቃል በመዝገበ ቃላት ማውጫው ላይ አይዞቶፕ አለው፡፡ በቤተ እግዜር በአንድ እምነት ተሰብስበው የቄሱን ስብከት የሚያደምጡ ምዕመናን “Mass” ተብለው ነው የሚጠሩት፡፡
ተመሳሳይ የኤሌክትሮን መጠን ያላቸውን ግን በክብደት የሚለያዩ አተሞችን ለመለየት የሚያገለግል “Mass spectrograph” የሚል ማሽን በአስራ ዘጠኝ ሀያዎቹ መጀመሪያ ግድም የፈለሰፈው የሀርቫርድ ምሩቁ ሳይንቲስት “Aston” ይባላል፡፡
እንደ መንደርደሪያ ይኼንን ይዘን በሌላ የእይታ አንፃር ነገር አለሙን እየመዘንን እስቲ እንቀጥል፡፡ ከተፈቃቀድን ማለቴ ነው፡፡
የምንመዝነው ክብደትን (Mass) መሰረት አድርገን እንዲሆን ነው ፍላጎቴ፡፡ ለምሳሌ፤ አይንሽታይን የሚባል ጀርመናዊ ይሁዲ … “ክብደት ማለት ሀይል ነው” የሚል ሐልዮ አፍልቆ ለሀያኛው ክፍለ ዘመን ቀዳሚ የሳይንስ እመርታ አስተዋፅኦ አደረገ፡፡
እርግጥ አይንሽታይን በንጥረ ነገር አለም ላይ ነው ግኝቱ ያነጣጠረው፡፡ ግኝቱ በጣም ቀላል ትመስላለች-በፎርሙላ መልክ ስትቀመጥ፡፡
E = MC2 ነው ፎርሙላው፡፡
“E” የሚወክለው ሀይልን ነው፡፡ “M” የሚወክለው ክብደትን (Mass) ነው፡፡
“C” … የብርሐን ፍጥነት ማለት ናት (velocity of light)
የብርሐን ፍጥነት (velocity) በእነ አንሽታይን ጊዜ በሰከንድ ስንት ሴንቲ ሜትር ይሄዳል በሚል ቀመር ነበር የሚለካው (centimeters per second) ክብደት ደግሞ የሚመዘነው በ “ግራም” ነበር፡፡ ዛሬ ክብደት በኪሎ ግራም፣ የብርሃን ፍጥነት ደግሞ በሰከንድ ስንት ሜትር (meters per second)       በሚል ነው የሚቀመረው፡፡
ለማንኛውም፤ ብርሃን በአንድ ሰከንድ ጊዜ ውስጥ 300 ሚሊዮን ሜትሮች ይጓዛል፡፡ ስለዚህ፤ አንድ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ክብደት ያለው ቀኒጥ (አተም) እንኳን በውስጡ የክብደቱን እጅግ እጥፍ የሆነ ኃይል (energy) ይዟል የሚል ነው፡፡ … የኒውክሊየር ቦንብ ፍንዳታ የዚህ ሀይል መገለጫ ነው፡፡ ከፍንዳታው በመጠን ያነሰ የኑራኒየም አተም ሲጨፈለቅ ከውስጡ የሚመነጨው ሀይልን በሚሊዮን እጅ ያጥፈዋል፡፡   
ጥሩ፤ ሳይንሱን እዚህ ደረጃ ያህል ነው የምናውቀው፡፡ ወደ ጥልቅ ቴክኒካዊ ጉዳይ ለመግባት የሚያስችል የእውቀት ስልጣን የለንም፡፡ ግን የመጠየቅ ስልጣን አለን፡፡ በምናስታውሰው የራሳችን መጠን የሚጠየቁ ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን፡፡
ዝም ብዬ ከተራ አስተውሎት ልነሳ፡፡ በአካል ክብደቱ ከፍ ያለ ሰውን ብዙ ጊዜ እናከብራለን። ክብደትና ክብርም በፔሬዲክ ቴብሉ ላይ በአንድ ፈርጅ የተቀመጡ ቃላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ቀትረ ቀላል›› የሚለው ሀረግ የክብደት መለኪያ ነው። ሁላችንም መሰሎቻችንን የምንመዝንና ደረጃ የምናወጣ ነን፡፡ ደረጃ ምደባ ደግሞ ከክብደት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
አንሽታይን የደረሰበት ግኝት ቅድም እንዳልኩት፤ ‹‹ክብደትና ሃይል ተጓዳኝ ነገሮች ናቸው›› የሚል ነው፡፡ የተሻለ ክብደት ያለው ውስጥ የበለጠ ሀይል ይኖራል እንደ ማለት ግን አንሽታይን (ምናልባት) ሳይደርስበት የቀረው ቁልፍ ጉዳይ ‹‹ክብደትና ሀይሉን የሚያዘው ማነው?›› የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡
አንሽታይን በክብደትና በሀይሉ መሀል ያለውን የተፈጥሮ ግንኙነት በማግኘቱ ብቻ የተፈጥሮ ህግ ለእውቀት ይታዘዝለታል፡፡… በሰዎች ዘንድ ሳይንቲስትነቱ ክብደት ያገኛል፡፡… ተራ የሆኑ ክብደት ያላቸው ብዙሀኑን ህዝብ (mass) ማዘዝ ይችላል፡፡
‹‹Mass›› ክብደት ነው፡፡ ልክ በአቶም አለም እንዳሉ አይዘቶፖች የቃላት አይዘቶፖችም፣ አሉ። ‹‹ክብደት›› የሚለውም ቃል ሁለት የትርጉም ፍቺ አለው፡፡ አንደኛው እንደ ግዑዝ በሚዛን አለም… በኪሎ የሚለካው ክብደት ነው፡፡ የንጥረ ነገሮች ጥርቅሙ ስጋ…የአተምና የሞሎኪውል ትስስሩ። ሁለተኛው ግን ይህንን የስጋና የንጥረ ነገር አለም የሚያዘው ነው፡፡ ሁለተኛው ክብደት የመጀመሪያውን ይነዳዋል፡፡
የሀሳብ ወይንም የእውቀት ክብደት… የአካልን ክብደት አስተሳስሮ ወደ አሻው አቅጣጫ ይመራዋል። እና በአንሽታይን ቲዎሪ ሁሉም አይነት ክብደት ከሚዛን ጋር ቢያያዝ ኖሮማ… የሃገር መሪ የሚሆነው ሰው ከሁሉም በኪሎ የገዘፈው ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ወፍራም ሰዎች ከቀጫጫ ጋር ተወዳድረው (የጉልበት ውድድር ያውም) ሲሸነፍ አይቻለሁኝ፡፡
ቀጫጫዋ ሰውዬ ወፍራሙን መሬት ላይ አንደባልላ ስትደስቀው ብታዩ አይንሽታይን ተሳስቷል ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ የተሳሳታችሁት ግን እናንተው ራሳችሁ ናቸው፡፡ ቀጫጫዋ ሰውዬ ውስጥ ያለው ‹‹ወኔ…በራስ መተማመን… ወይንም…ጀግንነት›› ከወፍራሙ ከበለጠ አዎን ታሸንፈዋለች። ፉክክሩም፤ የክብደት፤ ሀይል በሚል ፎርሙላ ሳይሆን ወኔ፤ ሀይል ወደሚል መንፈሳዊ ፔሬዲክ ቴብል ይገባል፡፡…ተመጣጣኝ ያልሆኑ ክብደቶችን የሚያመጣጥን… ወይንም ዝቅ ያለውን ክብደት ከፍ ወዳለ ልዕልና የሚያወጣ ሌላ የሳይኮሎጂ አለም ፎርሙላ አለ ማለት ይሆን? ብለን እንጠረጥራለን፡፡
E= MC2 በሳይኮሎጂ ወይንም በመንፈስ አለም ምንም ትርጉም የሚያዋልድ ፎርሙላ አይደለም። ለሚለካውና በክብደት ሊመዘን ለሚችለው ተጨባጭ አለም ብቻ የሚያገለግል ፎርሙላን ነው አንሽታይን ያዋለደው፡፡
በአካል አለም ደቃቃ የሚባለው ሳይንቲስት (አይንሽታይን) … ለኢነርጂ አለም የሚሰራ ፎርሙላ ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ እሱ የመንፈስ ልዕልና በተለዋጭ ተቀዳጀ፡፡ ስለ አካል ገልፆ በመንፈስ ገዘፈ፡፡
“Mass” የቤተ ክርስቲያን ምዕመን፣ ህዝብ ማለት ነው ብያለሁኝ … በቃሉ አይዞቶፓዊ ሁለተኛ ትርጉም፡፡
የቤተ ክርስቲያኑን ምዕመን የሚመራ አንዳች ግኝት አለ፡፡ ልክ አንስታይን የሀያኛውን ክፍለ ዘመን ሳይንስ እንደመራበት ግኝት የመሰለ፡፡ ያንን ያህል የአካል ክብደት ያለውን ህዝብ በአንድ (Bind) አድርጎ አድራሻ የሚመራ የሀሳብ ክብደት ምን ያህል ሀያል “energy” ያለው እንደሆነ ገምቱት፡፡ የብርሀን ፍጥነት በኃይል ቁጥር ሲበዛ የሚሰጠው ኃይል ለዚህ አይነቱ የሀሳብ ክብደት መለኪያ አያገለግልም፡፡
እና ብቻ ክብደት ቁሳዊና መንፈሳዊም አቅጣጫ አለው፡፡ የመንፈሳዊ ክብደትን አመንጭቶ (በእውቀትም ይሁን በዕምነት) አካላዊ ክብደትን (ተፈጥሮንና የሰው ልጅን) መቆጣጠር የቻለ የበለጠ ልዕልና ይኖረዋል፡፡
የቅኔው ፍቺ ይሄ ይመስለኛል፡፡ ህብረ ቃሉ “ክብደት” የሚል ነው፡፡ ሰሙ፣ የአካል ክብደት … የቁስ የተፈጥሮ ማንነት በክብደት ሀሊዮ ሲፈተሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ወርቁ ግን መንፈሳዊ ነው፡፡ መንፈሳዊ መሆን ሲያቅተው ደግሞ ሰምና ወርቁን በአንድ ላይ የሙጥኝ ብሎ የሳይኮሎጂ ትንተና አቅራቢ ይሆናል፡- እንደ ሲግመንድ ፍሮይድ .. ፡፡ ፍሮይድ፤ “Mass” የሚለውን ቁሳዊ ፍቺ እንስሳዊ ያደርገውና … መንፈሳዊ ፍቺውን ደግሞ ማህበራዊ እንስሳዊነት ያደርገዋል፡፡
… ብቻ ዋናው ጉዳይ ክብደትን ማዘዝና መቆጣጠር ነው፤ “በየትም በየትም ብለህ፤ ተፈጥሮን ደብቀህም ይሁን ገልጠህ … ብቻ ቅኔ የሆነውን የክብደት መንበር … እና የስልጣን ልዕልና ተቆጣጠር” … መርሁ ይሄው መሰለኝ፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ ነው!

Read 490 times