Monday, 13 March 2017 00:00

የሴቶች ጭቆና በየቤታችን!

Written by  በሲቲና ኑሪ
Rate this item
(0 votes)

  “አርበኛው ኔልሰን ማንዴላ፤ “ሴቶች ከየትኛውም አይነት ጭቆና ነፃ እስካልወጡ ድረስ የትኛውም አይነት
       የነፃነት ትግል አይሳካም” እንዳሉት፤ እንደዚህ ያሉ በየቤታችን የሚፈጸሙ የየዕለት የጭቆና ጥሪዎችን ችላ
      ብለን ታላቁ ሩጫ ለሴቶች ብንሮጥ፤ ከሩጫው መልስ ቤታችን የሚጠብቀን ያው ጭቆናው አይደለምን?”
                 
      በ”ሕይወት ኢትዮጵያ” እና በ”ዎክ ፋውንዴሽን” አጋርነት በተለያዩ ራዲዮ ጣቢያዎች ከሚተላለፉ ትምህርታዊ ማስታወቂያዎች መካከል “ዘመናዊ ወንዶች ኃላፊነት ይሰማቸዋል” የሚለው ማስታወቂያ ቀልብ ሳቢ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ዘመናዊ ማን ነው? ዘመናዊነትስ ምንድን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎችም ያጭርብኛል፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ዘመናዊነት የተሰኘው አገላለፅ በጣም ብዙ ትርጉሞችን አንድ ላይ አጭቆ የያዘ መሆኑ ነው የጥያቄዎቹ መጀመሪያ። ዘመናዊነት ስልጣኔን (Modernity)፣ ዘመኔ-ዊነት (Modernism)፣ እንዲሁም መዘመንን (Modernization) አንድ ላይ አዳብሎ የያዘ እምቅ ቃል መሆኑ ላይ ነው መረዳታችን ተግዳሮት የሚገጥመው፡፡ ይህ የቃላት ትርምስ (semantic chaos) በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ስልጣኔ ለመረዳት በምናደርገው ጥረት ላይ ማነቆ እንደሆነ ሊቋ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ “The Beginning of Ethiopian Modernism: A Brief Synopsis on the Inception of Ethiopian Visual Modernism (1957-1974)” ባሉት ጽሑፋቸው ላይ ይሞግታሉ። ከዚህ እሰጣ ገባ በመለስ ከላይ የጠቀስኩትን ማስታወቂያ ሐሳብ ለመረዳት እንደቻልኩት፤ ‹ዘመናዊ ወንዶች› የተባሉት ‹‹የዘመኑን መንፈስ (zeitgeist) ተረድተው የሚኖሩ ስልጡኖች›› ለማለት የተፈለገ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አግባብ ሴቶችን በእኩል ሚዛን የሚመዝኑና የሚያከብሩትን እንደማለት፡፡
ድንበር የለሹ ጾታዊነት (Sexism)
ከዚህ የሐገራችን እውነታ ራቅ ብለን በስካንዲኒቪያዊቷ ስዊዲን እ.ኤ.አ በ2013 የተቋቋመውን ‹Reklamera› የተባለ የሴቶች አግባቢ (lobbyist) ቡድን እናገኛለን፡፡ የቡድኑ ስያሜ በግርድፉ ማስታወቂያ ተቆጣጠሪ የሚል ሲሆን ዋነኛ አላማውም ለሕብረተሰቡ ፆታዊና (sexist) አድሎአዊ (discriminatory) ማስታወቂያዎች ምን እንደሆኑ ማሳወቅ፣ ሕብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ማስታወቂያዎች በሚዲያ ሲሰራጩ ሲያይ፣ ማስታወቂያውን በሚለቁ ሚዲያዎች፣ አሰሪ ድርጅቶችና የፖለቲካ ሰዎች ላይ የራሱን ምላሽ እንዲሰጥ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡ በተለያዩ የሕይወት መስመሮች፣ ሕብረተሰቡ አድሎአዊ አልያም ፆታዊ ማስታወቂያዎች ናቸው ብሎ ያሰባቸውን ነገሮች ፎቶ በማንሳት #Reklamera የሚል አፅንኦተ-ቃል (hashtag) በመጠቀም በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ እያወጣ፣ ጉዳዩን ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግንም እንደ ዋነኛ የመታገያ መንገድ ይገለገልበታል፡፡    
ለቡድኑ መቋቋም ዋነኛ መነሻ የሆነውም የስዊዲን መንግስት እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2008 ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ያደረገውን ጥናትና ምርመራ ውጤት መሰረት በማድረግ፣ የሴቶችንና የወንዶችን እኩልነት ለማሻሻል ማስታወቂያዎች ያላቸውን አሉታዊ አስተዋፅኦ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ማስታወቂያዎችን የሚቆጣጠር ህግ ለማውጣት በ2008 ረቂቅ ሕግ ቢያዘጋጅም፤ ሕጉ ገና ከጅምሩ የተቃውሞ ሰለባ ሆኖ፣ ‹የመናገር ነፃነትን ይገድባል› በሚል የአገሪቱ ላዕላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጉ ነበር፡፡ በሕግ አግባብ ፆተኝነት (sexism) ያጠቃቸውን ማስታወቂያዎች ማገድ የማይቻል ከሆነ ኢ-መደበኛ (informal) በሆነና ከመንግስት መዋቅር ውጭ በሆነ መንገድ ዘመቻ ማድረጉ የሚያዋጣ ነው ብሎ መወሰኑም ነው ለቡድኑ መመስረት ዋነኛው ምክንያት፡፡ ከዚህም ባለፈ ቡድኑ በመንግስት ላይ የበረታ ግፊት ማድረጉን ገፍቶ ቀጥሎበታል፡፡
በተለያዩ የዓለማችን አገራት (በአደጉትም ሆነ ባላደጉት አገራት) ማስታወቂያዎች ሴቶችን እንደ እቃ (objectify) የመሳልና ዝቅ አድርገው የመገመት (condescendingly) ባህሪ አላቸው የሚለው ድምዳሜ የብዙ ጥናቶች ውጤት ነው፡፡ ብሬትል እና ካንቶር የተባሉ አሜሪካዊያን ሊቃውንት “The Portrayal of Men and Women in U.S. Television Commercials: A Recent Content Analysis and Trends over 15 Years” ባሉትና ረጅም የጥናት ጊዜን በሸፈነ ጥናታቸው፤ በአሜሪካን አገር የሚሰሩ አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ላይ ሴቶች ቤት ተቀማጭ፤ ወንድ አቻዎቻቸው ደግሞ ከቤታቸው ውጭ ወጣ ብለው ተመላሾች ተደርጎ እንደሚሳሉ ገልፀዋል። ይሄም ሕብረተሰቡ ላይ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተፅዕኖ በማሳደር፣ ሴትን ከወንድ ነጥሎና ዝቅ አድርጎ የመሳል አባዜን የሚያስተጋባ ተግባር እንደሆነ ምሁራኑ አፅንኦት ሰጥተው ይገልፃሉ፡፡
. . . ሴት ወደ ማጀት
ባሳለፍነው ዓመት 2008 “የኢትዮጵያ የሴቶች ማህበራት ጥምረት” የዓለምአቀፉን ፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻን  በማስመልከት ባዘጋጀው አንድ ዝግጅት ላይ ዶክተር በላይ ሀጎስ፤«ፍትሀዊ ሥርዓተ ጾታን ለማሳካት የወንዶች ሚና» በሚል ርዕስ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው የነበረ ሲሆን፤ በጥናታዊ ፅሁፉ ላይ የወንዶች አጋርነት ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ዋነኛ መሳሪያው መሆኑን አፅንኦት በመስጠት፣ እዚህ ላይ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀው ነበር፡፡ እንዲሁ ሲታይ ይህ ቀላል ነገር ቢመስልም ወደ መሬት ወርዶ ለመተግበር ግን እጅግ ብዙ ተግዳሮቶች ሲገጥሙት ይታያል፡፡ ጎልተው ከሚታዩት ተግዳሮቶች መካከልም በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት እንደሚተላለፉት ማስታወቂያዎች ገዝፈው በየሰዓቱ በየቤታችን የሚደርሱ ተግዳሮቶች አሉ ለማለት አይቻልም፡፡
የቴክኖሎጂው ርካሽነትና በቀላሉ ተደራሽ መሆን ጋር ተዳምሮ በአሁኑ ወቅት (መንግስታዊዎቹን የሚዲያ ተቋማት ሳንዘነጋ) በአገራችን “ፖለቲካ አይነኬ” ራዲዮኖችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እዚህም እዛም አለን አለን እያሉ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጣቢያዎች ሕልውናቸውን የመሰረቱት በሚያስተላልፉት የንግድና ትምህርታዊ ማስታወቂያዎች በሚገኝ ገቢ ላይ እንደመሆኑ ማስታወቂያዎች ገነው መሰማታቸው ብዙም የሚገርም ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የሚተላለፉትን ማስታወቂያዎች እንዲሁ የተመለከተ ሰው፣ ይዘታቸውና የሚያስተላልፉት መልዕክት ላይ ብዙ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ ለማለት የሚችል አይመስልም፡፡
አብዛኛዎቹ ማስታወቂያዎች (እንደ ሌላው ዓለም በእኛ አገር በዚህ ረገድ የተሰራ ጥናት ላገኝ አልቻልኩም) ሴቶችን የሚመስሉት ማሕበረሰቡ የሰጣቸውን ጨቋኝ ሰብእና አፅዳቂ (conformist) በመሆን በልብስ አጣቢነት፣ በምግብ አብሳይነት፣ መንገድ ላይ ተለካፊ፣ ልጅ ማሳደግ የእነሱ ብቻ ሸክም እንደሆነ፣ በቤት እመቤትነትና መሰል የቤት ውስጥ ጉዳዮች ነው፡፡  
የዓለም የሴቶች ቀንን ለ40ኛ ጊዜ ያከበረችው ኢትዮጵያ እንደነ Reklamera ያሉ በማስታወቂያዎቻችን ላይ ስለሚሳሉ የሴቶች ሚና ተከራካሪ ቡድን አለማፍራቷ እንዳለ ሆኖ፤ በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  ዝምታን መምረጣቸውን ስንመለከት፣ የኢትዮጵያ ሴቶችን መብት ለማስጠበቅ አንድ ቀንን በዓመት ከማክበር ያለፈ መሰረታዊ ችግሮች ላይ ለመነጋገር ቁርጠኝነቱም ሆነ ፍላጎቱ ያላቸው አይመስልም፡፡
በ2004 ስለ ማስታወቂያ የወጣው አዋጅ ቁጥር 759/2004 እጅግ ብዙ ጥበቃ የሚደረግላቸው ነገሮች እንዳሉ በመዘርዘር በተለይም “…ነፃነትን፣ እኩልነትን የሚፃረር ምስልንና  አነጋገርን” የያዙ መልካም ስነ ምግባርን የሚፃረሩ አቀራረብ ያላቸውን ማስታወቂያዎች እንደሚከለክል በግልፅ የተቀመጠ ቢሆንም፤ አዋጁን አስፈፃሚ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ግን እስከአሁን እርምጃ ሲወስድ አልታየም፡፡  እነዚህ ሴቶችን የወንድ የበታችና አጋዥ አድርገው የሚያቀርቡ ማስታወቂያዎችም ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ ሲሄዱ አይታዩም፡፡
የጉዳዩ አሳሳቢነትስ?
እውነታው ከላይ እንደቀረበው ቢሆንም ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሴቶች ካለባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንጻር “ትንሹ ነው” የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ ይታያል፡፡ ይህ ግን ቢያንስ በሶስት ምክንያቶች የተሳሳተ ሐሳብ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የመጀመሪያው መብትን አሳንሶ ማየት የሚያመጣው ችግር ነው፡፡ ማንኛውም መብት (ትንሽ የመሰለንም ቢሆን) በተጣሰ ቁጥር ለትልቁ የመብት ጥሰት በር እየከፈተ መሄዱ እውነት ነው፡፡ ጉዳዩን አሳንሶ የማየት ችግር ሁለተኛው ስህተት፣የሚዲያንና የቋንቋን/ምስልን ኃይል ካለመረዳት ጋር ተያይዞ የመጣ ሐሳብ ነው ባይ ነኝ፡፡ የ60ዎቹ ዓለማቀፍ የመብት እንቅስቃሴ ትውልድ (Civil Rights Movement Generation) በመላው ዓለም ከተቀዳጃቸው መሰረታዊ ድሎች አንዱና ዋነኛው ቋንቋን ማረቅ (language consciousness) ነው። ይሄውም በየዕለቱ በየቤታችን የምንናገረው ሴትን ዝቅ አድራጊ (misogynistic) ንግግር፣ የትልቁ ጭቆና ዋነኛ ምንጭ መሆኑን በመረዳት የቋንቋ አጠቃቀምን በዚሁ አግባብ ማስተካከል ነው፡፡ በየአደባባዩና በየማስተዋወቂያው ‹ሴቷ ቦታዋ ማጀት ውስጥ ነው›፣ ‹ልብስ አጣቢነት ነው› … እያልን ውለን፣ ‹የሴቶች መብት ይከበር› ብለን ቢልቦርድ ብንሰቅል፣ ‹ሴት ናት፣ እህትህ ሴት ናት…› ብለን ብንዘፍን… ውጤት አልባ ከመሆን አናልፍም፡፡ ጉዳዩን የማሳነሱ አካሔድ ሶስተኛው ስህተት ሲሆን ሚዲያው ይሄን ነገር በደጋገመው ቁጥር ማህበረሰባዊ ቅቡልነቱ እያደገ ሔዶ የማይነቀልበት ደረጃ እንደሚደርስ አለመገንዘብ ነው ባይ ነኝ፡፡
ከቤተሰብ ጋር ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን የሚመለከቱ፣ ራዲዮ የሚሰሙ ልጆቻችንስ ከዚህ የዕለት ተዕለት  የጭቆና መዝሙር ምን ይማራሉ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ አርበኛው ኔልሰን ማንዴላ፤ “ሴቶች ከየትኛውም አይነት ጭቆና ነፃ እስካልወጡ ድረስ የትኛውም አይነት የነፃነት ትግል አይሳካም” እንዳሉት፤ እንደዚህ ያሉ በየቤታችን የሚፈጸሙ የየዕለት የጭቆና ጥሪዎችን ችላ ብለን ታላቁ ሩጫ ለሴቶች ብንሮጥ፤ ከሩጫው መልስ ቤታችን የሚጠብቀን ያው ጭቆናው አይደለምን?

Read 2385 times