Monday, 13 March 2017 00:00

መውለድ፤ አለመውለድ TO BE OR NOT TO BE

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

 የሄዋን እንጉርጉሮ
የያኔዋ የጥንቴ
የማንነት አጥንቴ
የጥርቡ ህልውና ምሣሬ
የአናሳ መነሾ ቅብጥሬ
የሄዋንነት ቅድመ ስፍሬ
አንቺ ዕፀ በለስ ፍሬ
ምነው ጉማሽ አዲስ አጣ
ወልድንም ላለም በደሜ አኑሬ?
                     /ብርሃን እና ጥላ - 1996 ዓ.ም/
ከላይ መግቢያ ያደረግነውና በኃይማኖታዊው አውድ ላይ ተመርኩዞ የተቋጠረው እንጉርጉሮ፣ ለጾታዊ ኢ- ፍትሀዊነት መታሰቢያ ተጽፎ የታተመው ከአስራ አምስት አመታት በፊት ነበር። ዛሬ እምብዛም እንዲያ አይመስልም፤ የጾታዊ ነጻነት አጀንዳ ከአጽናፍ አጽናፍ ተንሰራፍቷል። በማህበራዊ መስተጋብሩም ቢሆን፤ቁጥራቸው ቀላል የማይባል፤  ‹‹ባል/ሚስት ሳይሆን ልጅ መውለድ ስለፈለግኩ ብቻ ነው›› የሚል አቋም የያዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፤ ልጆቻቸውን ራሳቸው ለማሳደግ ዘመቻ የጀመሩ የሚመስልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የፍቺን መበራከት ጨምሮ፤ በነጠላ ወላጅ ማደግ በልጆች ላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ሀተታ እናቆየው፡፡ ባንጻሩ መውለድ ናፍቀው በጉጉት እሚጠባበቁ ወንድሞችና እህቶችንም ያስታውሷል፡፡ አመታዊው አለማቀፍ የሴቶች ቀን በተከበረበት በዚህ ሳምንት፤ እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም ባርባራ ቶነር፣ “A Mother’s Guide to Husbands” በሚል አርእስት ባሳተመችው መጽሐፍ ውስጥ “GOING NUCLEAR (OR NOT)” ብላ ከሰየመችው ምዕራፍ ጥቂቶቹን ቆንጥረንና ቀንብበን እናነብ ዘንድ እነሆ . . .
መሆን ወይም አለመሆን
ፈጥነሽም ይሁን ዘግይተሽ፤ ልጆች እንዲኖሩሽ ወሰንሽ እንበል፡፡ ወይም እንዳይኖሩሽ፡፡ በየትኛውም አንቺ ባሰብሽው ውሳኔ ደስተኛ ልትሆኚ ትችይ ይሆናል፡፡ ባንቺ አይነቱ ውሳኔም እሚደሰቱ ይኖራሉ ወይም እማይደሰቱ። አንዳንዶች ‹‹የመጣው ይምጣ እንጂ ዛሬ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ›› ሲሉ፤ ሌሎችም ደሞ ‹‹ምድሪቱን በህዝብ ብዛት ማጨናነቅ ምንድነው !›› የሚሉ አጋጥመውኛል፡፡ ቁም ነገሩ፤ ከወለድን፤ ለወለድናቸው ልጆች እንደምናስፈልጋቸው ማመኑ ላይ ነው፡፡ ብቻ የትኛውም ውሳኔ ቆይቶ ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ ከባልሽ ጋር ከወለዳችሁ ወይም ካልወለዳችሁ በኋላ የምትገፉት የኑሮ መልኩና ስሜቱ እንደጠበቃችሁት የመሆን አለመሆኑ ነገር ትልቁን ቦታ ሲይዝ ይገኛል። በዚህ አቢይ የህይወት ምእራፍ የሚያጋጥም ዱብ እዳ ቢኖርም ይኸው ነው፤ በጉዳዩ ላይ የአንቺና የባልሽ የአስተሳሰብ ጥምረት፤ የምትጋሩት የጋራ አመለካከት፡፡ ገና ‹በተጠባበሳችሁበት› ቅጽበት፤ ከሁለት አንዳችሁ ‹‹ልጅ እሚባል አልፈልግም›› ብትሉም፤ ምናልባት አንቺ በገነት በመሰልሽው የፍቅር ግንኙነትሽ ውስጥ የህይወትን ልምላሜና ፍሬ የማፍራትን ውበት ብርሀን ሀሴት እያደረግሽ፤ ስትወልጂ ጠያቂዎች ‹ስንቅ ቋጥረው ብቅ ሲሉ›፤ አበባ ሲላክልሽ ቢታይሽም፤ ‹‹ልጆች በረከት ናቸው፡ ግና ጊዜው አሁን አይደለም” ብለሽ ታልፊው ይሆናል፡፡(ማምሻም እድሜ ነው፡፡)
ልጅ የወለድን’ለት
የኔኑ ታሪክ ላውጋችሁ... በመጨረሻ ወንዶች ልጆችን የወለድኩ ቢሆንም፤ ግን በጣም ቆይቼ ነው፡፡ ትዳር ለመመስረት ከገመትኩት በላይ ዘግይቼ ነበርና፡፡ ካገባሁ በኋላም ቢሆን ለመውለድ በእጅጉ ተረጋግቻለሁ፡፡ ባል ሆዬ ልጁን ለማቀፍ ተጣድፎ ቀላል ይነጫነጫል። እኔ ደግሞ ገና ቤተሰብ ለመመስረት ዝግጁ አልነበርኩም፡፡ ድመት ገዝቼ አመጣሁለት። ዘላቂ መፍትኄ አልሆነም፤ ድመቶች የሰውን አባትነት በቅጡ አያስተናግዱ፡፡ የልጅ ድምጽ በቤቱ ካልጮኸ መቼም ደስተኛ እንደማይሆን ገባኝ። በዚያ ላይ የሚሰራው ‹ሴቶች ለዘር ናቸው› ብሎ ሽንጡን ገትሮ ከሚያምን ሰው ጋር ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ስንነታረክ ከርመን፤ እንደማይቀርልኝ ሳውቅና የግዴን ለመጸነስ ስወስን እምቢ አይልላችሁም፡፡ ተፈጥሮ ‹ገገመች›፡፡ ከዚያስ? ቀን በቀን ሀኪም እምጎበኝ ቋሚ ደንበኛ ሆኜ ቁጭ! የእድገት ንጥር hormone የተባለው እክል ሲስተካከልስ? ሀኪሜ ጋ ስከንፍ ሄጄ፤ የምግብ መመረዝ አጋጥሞኛል፤ ደጋግሞ ያስመልሰኛል ብዬ ተንጫጫሁበት፡፡ ‹‹በቃ ሆነ ማለት ነው›› አለኝ፡፡ ይህን የማጫውታችሁ፤ መውለድ ሲቻል አለመውለድን መወሰን ምን ያህል ከባድ መሆኑንና ወልዶ ለመሳም ለሚጓጉ ምስኪን ባሎች ያለውንም አሉታዊ ተጽዕኖ ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ (ማወቁን እናውቃለን፤ብንናገር እናልቃለን!)
ባልሽ ለምን ልጅ ይፈልጋል?
የአለሙ ሁሉ ስልጣን ቁንጮው ማእረግ በእጁ የገባ ያህል ሊሰማው ይችል ይሆናል፡፡ እናቱ የልጅ ልጇን ‹ከች› እንዲያደርግላት ነጋ ጠባ ትነዘንዘው ይሆናል፡፡ ልጅ የወለደችና ማንኛውንም ጉዳይ ‹አስተካክላ› የምትጠብቀው ሴት ያለችበት ዞሮ መግቢያ ጎጆ እንዲኖረው ይሻ ይሆናል፡፡ በነዚህ ሀሳቦች ዙሪያ የየግልሽን አስተያየት ለመሰንዘር ትችያለሽ፡፡ በበኩሌ እውነቱን ለመናገር ጎጆ በመቀለሱ ጉዳይ ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ በመጨረሻም እንዲኖረኝ የፈለግኩት እሱኑ ሆኖ አግኝቼዋለሁና፡፡ (ዞሮ ዞሮ ...)
ባልሽ ለምን ልጅ አይፈልግም?  
በሌላ መልኩ ደግሞ፤ ባልሽ ምናልባት አሁን ባላችሁበት ሁኔታ በቃ አንቺን ብቻ ይፈልግ ይሆናል፡፡ በመካከላችሁ ሌላ ሦስተኛ አካል እንዳይኖር ሊፈልግ ይችላል፡፡ ልጅ ሲመጣ የቤቱና የማንኛውንም ነገር ቅድሚያ ይወስድና ቀሪው ሁሉ በሁለተኛነት ይታይ ይጀምራል፡፡ በተለይ በእናቶች ህይወት ውስጥ፡፡ አንቺም ለባልሽ ሁለተኛ ረድፍ ላይ ትሰለፊያለሽ፡፡ እርሱም እንዲሁ፡፡ ላንቺ ምንም ባይመስልሽ እርሱ ግን መቼም ቢሆን ባንቺ ዘንድ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ መቆምን ይፈልግ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከወለድሽ በኋላ ትኩረትሽን ነፍገሽው ‹‹ልጅኮ ሊርበው፣ሊያለቅስ አይገባም፤ አብሬው መሆን አለብኝ››... መባልን በፍጹም አይፈልገውም ይሆናል፡፡ (ካንቺ ውጪ ወደ ..)
አንቺ ፈልገሽ ፤ እሱ ሲግደረደር
ባልሽ ካንጀቱ ወይም ካንገቱ ልጅ ባይፈልግና ልጅ ማሳደግ ይዞት የሚመጣውን ግሳንግስ ፈርቶ ሲንገዳገድ ብታገኚው፤ ወደሚፈለገው መንገድ እጁን ይዘሽ የምትመሪው አንቺው ነሽ። አለመቀበልን ያስተናገደ አእምሮ መቀበልን እንዲመርጥ ለማድረግ መልካም መሆን ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ የቀድሞ ውሳኔውን እንዲሽርና መውለድን እንዲያበረታታ በማገዝ። ይሄ ባለመውለድ ሊመጣ የሚችልን የፍቺ ችግርም ይቀርፋል፡፡ በነገራችን ላይ ማርገዛችንን የምናውጅበት ቃል በራሱ ለምናገኘው ምላሽ ተጽእኖ አለው፡፡ እንጂ ባመዛኙ አንቺ መውለድ እንደምትፈልጊ በሚታወቅበት ግንኙነት ውስጥ፤ ጽንስ መምጣቱን ሲያውቅ በኃይል ሊቃወም ሊገፈትር የሚነሳ አይመስለኝም፡፡ በርግጥ ነባር አቋሙን ማሳየቱ አይቀርም ይሆናል። ለማንኛውም መቼ፣ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደምትነግሪው ማወቁ በራሱ ‹‹ይወለድ ወይም አይወለድ›› ለሚለው ምላሽ ድርሻ አለው ልልሽ ነው፡፡ (‹‹በገባን መጠን እንመላለሳለን››)
“እንቁልልጩ” ባል
እናም እህቴ፤ አንድ ጊዜ ከወሰንሽና ከጸነስሽ በኋላ፤ ቀሪውን ዘጠኝ የእርግዝና ወራትሽን ማጣጣም/መጋፈጥ መጀመርሽ የማይቀር መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቅድም እንዳልነው፤ ያለመውለድ ችግሩ በተፈጥሮ የመጣ ካልሆነ በቀር፤ ባል ሆዬ ከሁለተኛው ጎራ ቆሞ፤ እርግዝናውም ሆነ ልጅ መውለዱ የሚያመጣውን ጣጣ ‹እያካበደ› ከውሳኔሽ ሊያንገጫግጭሽ ይችል ይሆናል፡፡ ሌላው ቀርቶ መጸነስ እምትችዪበትን ቀን ቆጥረሽ ዝግጁ በምትሆኚ ጊዜም እንኳ፤ እንደው ምኑም ምንም ሳይጎድለው፤ ቋት አይሞሉ የምክንያት መአት እየደረደረ ሲዋልል  ያጋጥምሻል። ያኔ ታዲያ፤ እውነት ነው፤ ሲደጋገም በትእግስት ቆይተሸ፤ አንድ ቀን ግን ድንገት ቱግ ብለሽ ‹‹እግዜሩ ሰጥቶህ የታቀፍከው መስሎኝ!›› ብትዪው በበኩሌ ምንም አይደንቀኝም፡፡ ምን ታረጊ፤ ፈርዶብሽ፡፡ (አልጋው ሲገኝ እንትኑ አይገኝ!) በዚህ ሁኔታ ሳላችሁም ደግሞ፤ የሆነ ቀን ማለዳ ላይ ባልሽ ሽክ ብሎ ለብሶ ክራቫቱን አስሮ መስተዋት ፊት ቆሞ እየዘነጠ፤ ‹‹እኔኮ ‹ቀሽት›! ነኝ፤ የወጣልኝ ወንዳወንድ !›› ሲል ብትሰሚውና፤ በምላሽሽ ‹‹ራስህን እያጃጃልክ ነው ልበል?!›› ብለሽ ብትጠይቂውም አልፈርድብሽም፡፡ (ጥያቄውም ይኸው አይደል? መሆን ወይም አለመሆን፡፡)

Read 626 times