Monday, 13 March 2017 00:00

ዶ/ር መረራ ጉዲና ዋስትና ተከለከሉ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ለፍ/ቤቱ ተናግረዋል
                                      
       ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ አድርገዋል እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች ተላልፈዋል በሚልና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ክስ የተመሰረተባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ለፍ/ቤት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም በነበራቸው ቀጠሮ፣ የተከሰሱት በወንጀል ህጉ ስለሆነና ተከሳሹ ከዚህ ቀደም የነበራቸው የፖለቲካ ታሪክ፣ ከቤልጂየም ሲመለሱ እንደሚታሰሩ እየተነገራቸው እንደመጡና ከሀገር የመኮብለል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ታይቶ እንዲሁም የስኳር ህመምተኛ በመሆናቸው በዋስትና ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አቃቤ ህግም የተጠረጠሩበት ወንጀል ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል የመናድ ሙከራ በመሆኑ በዋስትና ቢወጡ መረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
የግራ ቀኙን አስተያየት የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ተጠርጣሪው በተከሰሱበት የህግ አንቀፅ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ15 ዓመት በላይ ወይም በእድሜ ልክ አሊያም በሞት ሊያስቀጣ የሚችል በመሆኑ ዋስትናውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
በችሎቱ ማጠናቀቂያ ላይ ዶ/ር መረራ የምናገረው አለኝ ብለው ሲፈቀድላቸው፡-
“ከእነ ጀነራል መንግስቱ ነዋይና ጀነራል ታደሰ ብሩ ዘመን ጀምሮ ከአንድ ትውልድ በላይ ገዳዮችና ሟቾች፣ ታሳሪዎችና አሳሪዎች በበዙበት የሀገራችን የፖለቲካ ድራማ ውስጥ በመቆየት አንድ ከሆዱ በላይ ለሀገሩ የሚያስብ ምሁር ማድረግ እንዳለበት ሁሉ፣ ከአርባ አምስት አመታት በላይ ለሀገሩ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ በታማኝነት መታገሌ እየታወቀ ወደ ጎን መገፋቴን፤ ለሁላችንም የምትሆንና በእኩልነት የምታስተናግደን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠርና ነፃ የፍትህ ስርአት በሀገራችን እንዲሰፍን ላለፉት 25 ዓመታት በመታገሌ መከሰሴ አንሶ የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ጭምር የነበርኩት ሰው፣ ለተራ ወንጀለኛ የሚፈቀድ የዋስ መብት በመከልከሌ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለራሴ ብቻ ሳይሆን እኛም ሆንን ልጆቻችን በሰላም ይኖሩበታል በምንለው መከረኛ ሀገራችንና አላልፍለት ብሎ ለታመሰው ለመላው መከረኛ ህዝባችን ጭምር መሆኑ እንዲታወቅልኝ ነው” የሚል ንግግር አድርገዋል፡፡

Read 2325 times