Monday, 13 March 2017 00:00

በማተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋር የተጋጨው ተማሪ ራሱን አጠፋ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

 በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ኮሌጅ የ2ኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሪ፣ የሆነው ወጣት በአንገት ማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋር ተጋጭቶ “የትምህርት ውጤቴ ተበላሸ” በሚል ራሱን አጠፋ፡፡
ተስፋዬ ገመዳ የተባለው ተማሪ የስነ ልቦና ሳይንስ መምህሩ በቡድን ያዘዙትን አሳይመንት ስራ አዘጋጅቶ በመድረክ ላይ ሊያቀርብ ሲል መምህሩ፣ “በአንገትህ ላይ ያደረከውን ማተብ ወይ አውልቅ ወይም ሸፍነው” ሲሉት ተማሪው፤ “ይህ የእምነቴ መገለጫ ነው፤ ያዘዙኝን ማድረግ አልችልም” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውና መምህሩም “ያዘዝኩህን ማድረግ ካልቻልክ የሰራኸውን ማቅረብ አትችልም” በማለታቸው ስራውን ሳያቀርብ መቅረቱንና ከመድረኩ ወርዶ በእጁ የያዘውን የቡድን  ስራ ሪፖርት በንዴት ቀዳዶ መቀመጡን የአይን እማኞች አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ተማሪው ክፍለ ጊዜውን አቋርጦ ከክፍሉ መውጣቱንና ተመልሶ  ሊገባ ሲል መምህሩ አትገባም ብለው እንደከለከሉትና፣ ተማሪውም ስሜታዊ ሆኖ ከመምህሩ ጋር ለፀብ መጋበዙን፣ ተማሪዎችም በመሃል ገብተው እንደገላገሏቸውና የአካዳሚክ ዲኑ በቦታው ተገኝተው ስለተፈጠረው ችግር ተማሪዎችን በመጠየቅ፣ ፀቡን ማረጋጋታቸውን ተማሪዎች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ ቀን እንደተለመደው ተማሪው የስነልቦና ክፍለ ጊዜ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ክፍል ሲገባ መምህሩ በድጋሚ ከክፍል እንዳስወጡት፣ ተማሪውም ለአካዳሚክ ዲኑ አቤቱታ ማቅረቡንና ዲኑም የትምህርቱ የመጨረሻ ክፍል ጊዜ ስለሆነ ‹‹በቃ ተወው በውጤትህ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም›› ብለው አረጋግተው እንደሸኙት፣ የተማሪው የቅርብ ጓደኞች ገልፀዋል፡፡
በኋላም ፈተና እንዲወስድ የተፈቀደለት ሲሆን የተለጠፈውን የፈተና ውጤት ሲመለከት ግን “No Grade” (ምንም ውጤት የለም) የሚል ስለነበር ወዲያው በንዴት ወደ ተከራየበት ቤት በማምራት የዚያኑ እለት ራሱን ግቢ ውስጥ ባለ የማንጎ ዛፍ ላይ  ሰቅሎ ማጥፋቱን የቅርብ ጓደኞቹ ገልፀዋል፡፡
ፖሊስና የአካባቢው ህብረተሰብ በቦታው ደርሶ ከተሰቀለበት ሲያወርዱት ነፍሡ ከስጋው  እንዳልተላቀቀችና ወደ ሆስፒታል በመሄድ ላይ ሣለ ህይወቱ ማለፉን የጠቆሙት ምንጮች፤ የቀብር ሥነስርዓቱም ከትናንት በስቲያ በትውልድ አካባቢው በሰሜን ምዕራብ ሸዋ፣ ደገሞ ወረዳ መፈፀሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስከሬኑን ለቤተሰብ ያደረሱት መርማሪ ፖሊስ ዮሐንስ መገርሳ፤ ተማሪው ከመምህሩ ጋር በመጣላቱ ራሱን  እንዳጠፋ ጥርጣሬ መኖሩንና የሆስፒታል የምርመራ ውጤት በማስረጃነት እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩ ገና በመጣራት ላይ ነው ብለዋል - ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፡፡

Read 8497 times