Monday, 13 March 2017 00:00

“እስሩና ወከባው የሚቀጥል ከሆነ በድርድሩ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

“ሠማያዊ” በአንድ ሳምንት 19 አመራሮች ታስረውብኛል አለ
                      “ኢዴፓ” በሶስት ቀን 10 አመራርና አባላት እንደታሰሩበት አስታውቋል
    የፓርቲያቸው አመራሮችና አባላት እየታሰሩባቸው መሆኑ ስጋት እንደፈጠረባቸው የገለፁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ እስሩና ወከባው የሚቀጥል ከሆነ ከኢህአዴግ ጋር በጀመሩት ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አስታወቁ። ሠማያዊ ፓርቲ በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ 19 በየደረጃው ያሉ አመራሮቹ መታሰራቸውን የገለፀ ሲሆን ኢዴፓም በሦስት ቀን አስር አመራርና አባላት ታስረውብኛል ብሏል፡፡
የፓርቲው የቀድሞ ም/ሊቀመንበር አቶ ነገሠ ተፋረደኝና የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ብስራት አቢን ጨምሮ 19 የዞንና የወረዳ የፓርቲ ተወካዮች እንደታሠሩባቸው የገለፁት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤ ጉዳዩ ለሚመለከተው ኮማንድ ፖስት ቢያመለክቱም ምላሽ እንዳላገኙ አስረድተዋል፡፡
ከኢህአዴግ ጋር ድርድር እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፓርቲያችን አመራሮች መታሠር በድርድሩ ላይ እምነት እንዳይኖረንና በተሣትፎ መቀጠላችንን እንድናጤነው አስገድዶናል ብለዋል - አቶ የሸዋስ፡፡  ከታሰሩት 6 ያህሉ የት እንደታሰሩ እንኳ ማወቅ አልቻልንም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በዚህ ምክንያት የፓርቲ ስራዎችን ተረጋግተው ለመስራት አዳጋች እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹የአመራሮቹ መታሰር ከተጀመረው ድርድር እንድንወጣ ግፊት እየተደረገብን መሆኑን ያመላክታል›› ያሉት አቶ የሸዋስ፤ አባሎቻችን በዚህ መልኩ እየታሠሩ መንቀሳቀስ ስለማንችል ጉዳዩ የማይስተካከል ከሆነ ከድርድሩ አቋርጠን ልንወጣ እንችላለን ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ በርካታ የፓርቲው አመራሮችና አባላት መታሰራቸውንና የተወሰኑት ከወራት በኋላ መለቀቃቸውን፣ 23 አባላትና አመራሮች ከ19ኙ በተጨማሪ በእስር ላይ መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡
በድርድሩ ላይ በመሳተፋችን ከተለያዩ ወገኖች የስልክ ማስፈራሪያም እየደረሰን ነው ያሉት አቶ የሸዋስ፤ መንግስት ድርድሩ ተአማኒነት አትርፎ እንዲካሄድ የፓርቲ አመራርና አባላትን ከማሰር ተቆጥቦ ከዚህ ቀደም የታሠሩትንም መፍታት እንዳለበት አሳስበው፣ ይህን የማያደርግ ከሆነ ሰማያዊ በድርድሩ እንደማይሳተፍ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲው አመራሮችና አባላት የታሠሩት በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጉጂና አዴት መሆኑንም ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡
ኢዴፓ በበኩሉ፤ አርብ ቅዳሜና እሁድ ብቻ አስር ያህል አመራሮችና አባላቱ በባህርዳር፣ ደሴና በደቡብ ክልል እንደታሰሩበት ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ “እስሩ እንደ አዲስ መጀመሩ አስደንግጦናል፤ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ድርድሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ስለታሰሩ የፓርቲያቸው አመራርና አባላት ለኮማንድ ፖስቱ ማመልከታቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ እናጣራለን የሚል ምላሽ ቢሰጣቸውም በየቦታው ያሉ አባሎቻቸው ግን አሁንም ክትትልና ወከባ እንዳልቀረላቸው ተናግረዋል፡፡

Read 2934 times