Monday, 20 March 2017 00:00

መቄዶንያ በኤስ ኤም ኤስ ገቢ ማሰባሰብ ጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

     ሽልማቶች፣ ከተለመዱት በተጨማሪ ሙሉ የቤት ዕቃ፣ ነፃ የሆቴል መዝናኛ፣ የአየር ጉዞ፣ ነፃ    የትምህርት ዕድል፣ ነፃ የአየር በረራ ሥልጠና … ይገኙበታል
                           
       መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ምንም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በተለይም ራሳቸውን ችለው መፀዳዳት፣ መመገብና መንቀሳቀስ ለማይችሉ ሕሙማን መርጃ ኢትዮ ቴልኮም ከኅበረተሰቡ በኤስ ኤም ኤስ (SMS) ገቢ  እንዲያሰባስብ በፈቀደለት መሠረት ፕሮግራሙን ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 6 ቀን 2009 መጀመሩን አስታወቀ፡፡
‹‹ሰው ከጎዳና ሰው ያንሳ›› ‹‹ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› በሚል መሪ ቃላት በተጀመረው ሥነ-ሥርዓት፣ ኅብረተሰቡ በ3 ብር የጽሑፍ መልዕክት በ8050 የፈለገውን ቃል፣ ፊደል ወይም ቁጥር  በመላክ (ቴክስት በማድረግ) በየቀኑ መቄዶንያን በመረዳት በየዕለቱ የሚወጡ ሽልማቶችን እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ወደ 8151 የፈለገውን ቃል፣ ፊደል ወይም ቁጥር በመላክ (ቴክስት በማድረግ) ሽልማት የሌለው የ15 ብር ዕርዳታ እንዲያደርግ በማሳሰብ ራሳቸው ቴክስት በማድረግ የፕሮግራሙን በይፋ መጀመሩን ያበሰሩት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ መቄዶንያ እያደረገ ያለውን ተግባር መደገፍ የሁሉም ኅብረተሰብ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብንያም በለጠ አዲስ ባደረገው ንግግር ለፕሮግራሙ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶችና የመንግሥት መ/ቤቶች እንዲሁም ሽልማቶችን ስፖንሰር ላደረጉ በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከፍተኛ ምስጋና አቅርቦ፤ አሁንም ሽልማቶችን ስፖንሰር ማድረግ ይቻላል ብሏል፡፡ ማዕከሉን በሙያ፣ በጉልበት፣ በሐሳብ፣ አዲስና ልባሽ አልባሳት፣ ጫማዎች፣ የቤት ዕቃዎች፣ የአዋቂ ዳይፐር፣ የገላ፣ የልብስ ሳሙና ፈሳሽ ፣ ጭማቂ (ጁስ)፣ ሶፍት፣ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ የምግብ ውጤቶች፣ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና ማሽነሪዎች… በመለገስ ማዕከሉን የደገፉትን ድርጅቶችና ግለሰቦች ከልብ አመስግኖ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ድጋፍ በማድረግ ማዕከሉን እንዲረዱ ጠይቋል፡፡
ኅብረተሰቡ፣ በ8050 ቴክስት አድርገው 3 ብር ሲልኩ የሚያገኟቸው ሽልማቶች ሞባይሎች፣ ቲቪዎች፣ ላፕቶፖች፣ ፍሪጆች፣ ካውያዎች፣ ባጃጆች፣ ሞተር ቢሲክሌቶች ዳማስ መኪናና ሚኒባስ … ሌሎችም በርካታ ከፍተኛ ሽልማቶች ቀርበዋል፡፡ ሽልማቶቹ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ሙሉ የቤት ዕቃ፣ ነፃ የሆቴል መዝናኛ፤ የአየር መንገድ ጉዞ፣ ነፃ የትምህርት ዕድል፣ ነፃ የአየር በረራ ሥልጠና ሽልማቶቹ የተካተቱ ናቸው ብሏል ማዕከሉ፡፡

Read 3115 times