Monday, 20 March 2017 00:00

ካህናቱና ምእመናኑ፣ የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እንዳይፈርስ ተማፀኑ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    በአዲስ አበባ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12፣ ልዩ ስሙ አባዶ ቁጥር 1 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተሠራችው የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ  ቤተ ክርስቲያን፣ ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ በከፊል የፈረሰባቸው መኾኑን የገለጹ ካህናትና ምእመናን፣ የድረሱልን ጥሪ አሰሙ፡፡
በከተማው መልሶ ማልማት ወደ አካባቢው የሔዱት ነዋሪዎቹ፣ ሥርዓተ አምልኰ የሚፈጽሙበት ቤተ ክርስቲያን ተቸግረው መቆየታቸውንና ከአራት ወራት በፊት፣ ከግለሰቦች በስጦታ ባገኙት ቤትና ቦታ ላይ በሀገረ ስብከቱ ፈቃድ በቅድስት አርሴማ ስም ቤተ ክርስቲያን ተክለውና አስባርከው በመገልገል ላይ እንደነበሩ ካህናቱና ምእመናኑ ገልጸዋል፡፡500 ካሬ ሜትር ስፋትና 30 ቆርቆሮ ቤት ያለውን ቦታ ለመኖርያና ለእርሻ ይገለገሉበት የነበሩት ግለሰቦች፣ በስማቸው ተመዝግቦ ግብር ይገብሩበት እንደነበርና ሕጋዊ ባለይዞታዎች ለመኾናቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላቸው ካህናቱና ምእመናኑ ጠቅሰዋል፤ ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ በስጦታ ሲያበረክቱም፣ በውል ተቀባይነት የተረከቡት፣ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተወከሉ የመሥራች ኮሚቴው ካህናት መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም፣ የነዋሪዎቹን ማመልከቻና በአባሪነት ያቀረቧቸውን ማስረጃዎች መሠረት በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ይቻል ዘንድ የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤትና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ በደብዳቤ መጠየቁን አውስተዋል፡፡
ኾኖም፥ የወረዳው አስተዳደር፣ ከኹለት ሳምንት በላይ አንዳችም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፤ ያሉት ካህናቱና ምእመናኑ፣ ዝምታውን እንደ ይኹንታ በመቁጠር፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የታዘዘላቸውን ጽላት አስገብተው መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸዋል፤ የግለሰብን ቤት በቀጥታ
ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠቀም ስለሚከብድም፣ ዲዛየኑንና ቆርቆሮውን መቀየራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በማከናወን ላይ ሳሉም፣ የወረዳው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት፣ የንብረት ማስቀመጫ ኮንቴይነሩ ብቻ ሲቀር ሌላውን አፍርሶ ንብረቱን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማስገባቱን፣ ስምንት ካህናትም መደብደባቸውንና የመሥራች ኮሚቴው አባላትም ለአራት ቀናት ታስረው
እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡የታሰሩት ከተፈቱ በኋላ፣ ጉዳዩ በሕግ ታይቶ ባለመብት መኾናቸው እስኪረጋገጥ፣ ያለው ንብረት ቁልፉ ተከብሮ እንዲቀመጥ በፍርድ ቤት የእግድ
ትእዛዝ ቢያስወጡም፣ አጥሩና ምእመናኑ ለጥላ የሚገለገሉበት ሸራ፥ በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ መፍረሱን፤ ዶማ፣ አካፋ፣ ድጅኖ የመሳሰሉ መሣሪያዎችም መወሰዳቸውን፤ ዘወትርም ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንዳለ ዘርዝረዋል፡፡“ሕገ ወጥ ብንኾን፣ በሕግ እንጠየቃለን እንጂ ኢሰብአዊ በኾነ ኹኔታ ሊደበድቡንና ዘወትር እያስፈራሩን ሊቀጥሉ አይችሉም፤” ያሉት አንድ ካህን፣ መንግሥት ስለ እምነት ነጻነት ከሚናገረው አንጻር፣ “እነዚኽ ሰዎች እነማን እንደኾኑ ለመናገር እንቸገራለን፤” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡በአኹኑ ወቅት በመቅደስነት የሚገለገሉበት፣ የንብረት ማስቀመጫ ኮንቴነር መኾኑን ጠቅሰው፣ ለአራት ወራት የተቀደሰበት ቤተ ክርስቲያን እንዳይፈርስና ተረጋግተው ማገልገል እንዲችሉ፣ ለክፍለ ከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ለከንቲባው ጽ/ቤት መጠየቃቸውን አመልክተዋል፤ ጉዳዩ በፍ/ቤት ለመጋቢት 27 ለውሳኔ መቀጠሩንም አስታውቀዋል፡፡   ስለጉዳዩ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱን አስተያየት በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ፣ ጥሪ ባለመመለሱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Read 1521 times