Monday, 20 March 2017 00:00

በቲማቲም ተክል ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ ስጋት ፈጥሯል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

የቲማቲም ምርት ሙሉ በሙሉ ከገበያ ሊጠፋ ይችላል
                  ቲማቲም አምራች በሆኑ አካባቢዎች የኪሎ ቲማቲም ዋጋ 35 ብር ደርሷል
                   አንድ ሊትር የቲማቲም ፀረ-ተባይ መድሃኒት 12 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው
                          
       ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቲማቲም ተክል ላይ የተከሰተውና ቱታ አብስሉታ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ወረርሽኝ የቲማቲም ተክልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሊያጠፋው ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩ ተነገረ፡፡  በአንድ ጀንበር የቲማቲም ማሳውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ይችላል ተብሎ የተፈራው  ወረርሽኙ፤በሀገሪቱ ዋና ዋና ቲማቲም አብቃይ አካባቢዎች መከሰቱንና ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በወረርሽኙ መከሰት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የቲማቲም አምራች አርሶ
አደሮች አንዱ እንደሚናገሩት፤ከዓመታት በፊት በአካባቢው ያለ ምንም ፀረ-ተባይ መድኃኒት የቲማቲም ምርት ማምረት ይችሉ ነበር፤አሁን ግን በተለይም በያዝነው የምርት ወቅት የተከሰተው ወረርሽኝ ማሳውን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እንዳደረገባቸውና በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ኪሳራ ላይ መውደቃቸውን ገልፀዋል፡፡ “በ8 ሄክታር ላይ ያመረትኩት ቲማቲም ከጥቅም ውጪ በመሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ
ደርሶብኛል” ብለዋል - አርሶ አደሩ፡፡ ለአዲሱ ወረርሽኝ መድኃኒት ነው እየተባለ አንዱን ሊትር በ12 ሺህ ብር እየተገዛ የሚረጨው ጸረ-ተባይም በአብዛኛው የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈና ምንም ዓይነት መድሃኒትነት የሌለው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ባለፈው እሁድ በአዳማ ከተማ የተከበረውን 8ኛውን የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ቀን ምክንያት በማድረግ የግብርናና የእንስሳት ሀብት
ሚኒስቴር ለጋዜጠኞች አዘጋጅቶት በነበረው የመስክ ጉብኝት፤በምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሚ ወረዳ፣ ቆቃ ነገዋ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ተዘዋውረን የተመለከትናቸው የቲማቲም ማሳዎች በወረርሽኙ ለጥፋት የተጋለጡ ሲሆኑ አምራቾቹም ለከፍተኛ ሥጋት ተዳርገዋል፡፡  
በሥፍራው ያገኘናቸው ቲማቲም አብቃይ አርሶ አደሮች እንደሚናገሩት፤ወረርሽኙ ድንገተኛና በጥቂት ጊዜ ውስጥ ማሳውን ሙሉ በሙሉ ሊያወድም የሚችል መሆኑ ከፍተኛ ሥጋት ላይ ጥሏቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሊትር 12 ሺህ ብር እየገዙ በሚረጩት ፀረ ተባይ መድኃኒት ጊዜያዊ
እረፍት ማግኘታቸውንም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል። ሁኔታው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን በጥቂት ጊዜ ውስጥ የቲማቲም ምርት ሙሉ በሙሉ ከገበያ ሊጠፋ እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ያደረገው ምንም ሙከራ አለመኖሩን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ፤የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያ እየተባሉ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ሰዎች በየጊዜው እየመጡ ማሳውን ጎብኝቶ ከመሄድ ውጪ ያደረጉት አንዳችም ነገር የለም ብለዋል፡፡ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሚ ወረዳ፣ ቆቃ ነገዋ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃነ እሸቴ በበኩላቸው፤ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ወደ ገበሬው ለማስረፅና ገበሬውን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቅርቡ የተከሰተው ቱታ አብሱሉታ የተባለው የቲማቲም ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አልሸሸጉም፡፡  ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት መደረጉን የገለጹት አቶ ብርሃነ፤በኦሮሚያ ግብርና በኩል ኮራጎን የተባለ ፀረ ተባይ መድኃኒት ለአርሶ አደሮቹ እንዲቀርብ
ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው፣ችግር አለባቸው በሚባሉ አካባቢዎች ላይ የፀረ ተባይ መድሃኒቶች እጥረት መኖሩን ጠቁመው፤አስቸጋሪነቱ እየታየ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ ይችላል
ብለዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ መድኃኒቶቹን በውድ ዋጋ እየገዙ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የመድኃኒቱን ትክክለኛነትም ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ዶ/ር ካባ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 1003 times