Print this page
Monday, 20 March 2017 00:00

የህውሓት መስራች አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ የህክምና እርዳታ ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 መንግሥት 300 ሺህ ዶላር እንዲረዳቸው ጥያቄ አቅርበዋል
                    
       ህውሓትን ከመሰረቱት 11 ታጋዮች አንዱ የሆኑት አቶ አስገደ ገብረሥላሴ በከባድ የልብ ህመምና የልብ ደም ቧንቧ ጥበት ምክንያት ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያሳክሟቸው ጠይቀዋል፡፡ ምንም ዓይነት ሥራ እንደሌላቸውና በጡረታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አስገደ፤በመቀሌና በአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ህክምናቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው በመጨረሻ ግን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህመማቸው ከአገር ውስጥ የህክምና አቅም  በላይ በመሆኑ ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲታከሙ እንደጻፈላቸው ይናገራሉ - የህክምና ማስረጃዎችን አስደግፈው በማቅረብ። ሆኖም የህክምና ወጪው በእሳቸው አቅም ሊሸፈን የሚችል ባለመሆኑ መንግስት በተለይም ዕድሜ ልካቸውን የታገሉለት ህወሓት/ኢህአዴግ ህይወታቸውን እንዲታደግላቸው የካቲት 22 ቀን 2009 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት 33 በመቶ የሰውነት አካላቸው ጎድሎ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ለህክምና 300ሺ ዶላር እንዲረዳቸው መጠየቃቸውን አስታውሰው ሆኖም እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታቸው ጥያቄውን በይፋ በሚዲያ በኩል ለህዝብ ለማቅረብ እንደተገደዱ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
አቶ አስገደ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ለተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ተቋማት በላኩት ደብዳቤ፤ “ህይወቴ አደጋ ላይ ነው፣ መንግስትና ህዝብ ይታደገኝ” ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
እርዳታ ሊያደርግላቸው የሚሻ ወገን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000088897963 ወይም  በ0914757242 በመደወል ሊያነጋግራቸው
እንደሚችል አቶ አስገደ ገልጸዋል፡፡ 

Read 2433 times