Monday, 20 March 2017 00:00

መወገድ ያለባቸው አደገኛና መርዛማ ኬሚካሎች አሉ ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(9 votes)

 • በአገር ውስጥ መወገድ የሚችሉበት መንገድም ሆነ ቴክኖሎጂ የለም
                • ዶላር ተከፍሎ የመጣው ኬሚካል፣ዶላር ተከፍሎ እንዲወገድ ይላካል
                • ኬሚካሎቹ በአካባቢም ሆነ በህይወት ላይ አስከፊ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው
                • የኬሚካሎቹን ክምችት ለማወቅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት ተጀምሯል
                            
       በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ለህይወት እጅግ አደገኛ የሆኑና በአገር ውስጥ ሊወገዱ የማይችሉ መርዛማ የኬሚካሎች ክምችት መኖሩ ተገለፀ። ኬሚካሎቹ በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ቢሆንም አገልግሎት ላይ ከመዋላቸው በፊት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፉ በአካባቢም ሆነ በህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፋንታሁን መንግስቱ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤በአሁኑ ወቅት እጅግ በርካታ ፀረ-አረም የተባይ ማጥፊያና የበሽታ መቆጣጠሪያ ኬሚካሎች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት የተለያዩ ኬሚካሎች መጠን በአራት እጥፍ እድገት አሳይቷል። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ኬሚካሎችና በጥቅም ላይ የሚውሉት ባለመመጣጠናቸው በርካታ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው አደገኛ መርዛማ ኬሚካሎች በተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
መርዛማ ኬሚካሎቹ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለሚገኙ መጠናቸውን ለማወቅ አልተቻለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤በአሁኑ ወቅት የኬሚካሎቹን መጠንና የሚገኙበትን ሁኔታ ለማወቅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ኬሚካሎቹ በዱቄትና በፈሳሽ መልክ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመውም፣ በአያያዝም ሆነ በአጠቃቀም ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል - ዶ/ር ፋንታሁን፡፡
አብዛኛዎቹ ደግሞ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና በአገር ውስጥ ሊወገዱ የማይችሉ እንደሆኑ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ኬሚካሉን ማስወገጃ መንገድ ወይም ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ ስለሌለ ቀደም ሲል ከፍተኛ ዶላር እያወጣን፣ወደ ውጪ አገር መልሰን በመላክ እንዲወገዱ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚወገዱት ኬሚካሎች መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ  የሚጠይቀውም የውጪ ምንዛሬ ከፍተኛ ነው፤በዚህ የተነሳም ኬሚካሎቹ ሊወገዱ አለመቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ዶላር ከፍለን ያመጣነውን ኬሚካል እንደገና ዶላር ከፍለን መልሰን በመላክ እንዲወገድ ማድረግ ትልቅ ችግር ሆኖብናል” ብለዋል - ዳይሬክተሩ፡፡
ኬሚካሎቹ በአገር ውስጥ መኖራቸው ለአካባቢ፣ ለሰውና ለእንስሳት ህይወት ከፍተኛ አደጋ ያስከትላሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ኬሚካሎቹ በተፈጥሮአቸው እንደሚለያዩና የሚያስከትሉትም ጉዳት እንደየኬሚካሎቹ ተፈጥሮአዊ ባህርይ እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ኬሚካሎች የሚያስከትሉት ጉዳት ፈጣንና ወዲያውኑ የሚታይ ሲሆን የአንዳንዶቹ ግን ቀስ በቀስ የሚገለጥና ዘለዓለማዊ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ኬሚካሎቹን ጥቅም ላይ የሚያውሉት አርሶ አደሮች ስለ ኬሚካሎቹ ባህርይና አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ ስለማይኖራቸው አጠቃቀማቸው ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ ነው ብለዋል፡፡
ፀረ-ተባይና ፀረ-አረም መድሃኒቶችንና ኬሚካሎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለአርሶ አደሩ የማከፋፈሉ ሥራ በግል ባለሃብቶች ብቻ መያዙ ችግሩን እንዳባባሰው የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅባቸው ኬሚካሎች አርሶ አደሩ እጅ ሳይደርሱ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያልፍባቸዋል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብዛት ተከማችተው የሚገኙት አደገኛና መርዛማ ኬሚካሎች የሚወገዱበትን መንገድ ለማመቻቸት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፋንታሁን፤ወደፊት ኬሚካል አስመጪው ድርጅት የማስወገድ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

Read 2241 times