Monday, 20 March 2017 00:00

የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዲስ አበባ የጋራ አስተዳደር እንዲኖራት ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(36 votes)

  አራት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዲስ አበባ ከተማን የኦሮሚያ ክልልና የአዲስ አበባ አስተዳደር በጋራ እንዲያስተዳድሯት የጠየቁ ሲሆን ባለፉት 25 ዓመታት ከከተማዋ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ካሣ እንዲከፈላቸውም አሳስበዋል፡፡
የኦሮሞ ኦቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስና የኦሮሚያ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ የተሰኙት 4 ፓርቲዎች ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ፤ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማግኘት የሚገባውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ ውይይት እየተደረገ መሆኑን መረጃ እንዳላቸው ጠቁመው፤በድንጋጌዎቹ መጤን አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አስታውቀዋል፡፡
ከአሁን በኋላ ወደ ላይ እንጂ ወደ ጎን የማይሰፋ ግልፅ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዲዘጋጅ ጥያቄ ያቀረቡት ፓርቲዎቹ፤የአዲስ አበባ ከተማን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ እንዲያስተዳድሯት፣አማርኛና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች በእኩል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ፣ በከተማዋ የሚወለዱ ህፃናት የኦሮሚኛ ቋንቋ የሚማሩባቸው ት/ቤቶች በየወረዳዎቹ እንዲቋቋሙና የኦሮሚኛ ቋንቋን ባህል ሊያዳብሩ የሚችሉ የፊልምና የቲያትር ማሳያ ቤቶች እንዲስፋፉ ጠይቀዋል፡፡
 “ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች ዘር ማንዘራቸው ተፈልጎ ካሳ ይገባቸው ነበር” ያሉት ፓርቲዎቹ፤አሁን ግን ቢያንስ በ25 ዓመቱ የኢህአዴግ ዘመን ከከተማዋ የተፈናቀሉ ገበሬዎች ከያሉበት ተሰብስበው ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው እናሳስባለን ብለዋል - በመግለጫቸው፡፡

Read 12841 times