Print this page
Monday, 20 March 2017 00:00

የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(34 votes)

እስከ ትላንት ድረስ ቁጥሩ 125 ደርሷል - ነዋሪዎች
                              
      ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣በተለምዶ “ቆሼ” እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ በደረሰው የቆሻሻ ክምር መደርመስ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር 125 የደረሰ ሲሆን የከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ የአደጋውን መንስኤ ፈጥኖ ለማጣራት አለመቻሉን ጠቁመው፤ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከአሜሪካው ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን እንዲያጠናው መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ መጠነኛ የቆሻሻ ክምር መደርመስ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ጉዳት አለማድረሱን የጠቆሙት የአካባቢው ነዋሪዎች፤የቆሻሻው ክምር ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እየተገፋ መምጣቱ ስጋት ላይ ጥሏቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በቅዳሜው አደጋ ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን እስከ ረቡዕ እለት እንኳ የ75 ሴቶች እና የ38 ወንዶች አስክሬን ወጥቶ በአካባቢው በሚገኘው አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎች የመቃብር ስፍራዎች የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈጽሟል፡፡
ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ መንግስት በሚገልፃቸው የሟቾች ቁጥር ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ጠቁመው  እስከ ትናንት ድረስ አስከሬኖች በፍለጋ እየተገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ መንግስት ረቡዕ እለት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ 113 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡ አስክሬን የማፈላለጉ ስራም እስከ ትናንት ምሽት የቀጠለ መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
አስተዳደሩ ለተጎጂ የሟች ቤተሰቦች ለቀብር ማስፈፀሚያ ለእያንዳንዳቸው 10 ሺህ ብር የለገሰ ሲሆን ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከንቲባው ራሳቸው የሚመሩት ግብረ ኃይል መቋቋሙም ተገልጿል፡፡ እስካሁን የአደጋው ተጎጂዎችን ለማቋቋም ኢትዮ ቴሌኮም የለገሰውን  1ሚ.ብር ጨምሮ ከሃይማኖት ተቋማትና ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ መሰባሰቡንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ፣የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውና ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው፤መንግስትን ለአደጋው ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ መድረክ ለአዲስ አድማስ በላከው የሃዘን መግለጫ፤”መንግሥት የቆሻሻውን ተራራ የሠራው እራሱ ስለሆነና አደጋው እንዳይከሰትም ተገቢውን የመከላከል ሥራ ባለመስራቱ በወገኖቻችን ላይ ለደረሰው አደጋ ሙሉ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ተገንዝቦ፣ለሟች ቤተሰቦችና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ካሳ እንዲከፍልና ለመፈናቀል አደጋ ለተጋለጡት ደግሞ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲያከናውን፤ ተመሳሳይ አደጋ በሌሎች ወገኖቻችን ላይ ለወደፊቱ እንዳያጋጥምም ተገቢውን የመከላከልና የጥንቃቄ እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወስድ በጥብቅ ያሳስባል፡፡” ብሏል። መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲም እንዲሁ ባወጡት የሃዘን መግለጫ ለአደጋው መንግስትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡  ፓርቲዎቹ መንግስት ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍልና በአስቸኳይ መልሶ እንዲያቋቁማቸው ጠይቀዋል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት በውጭ ባለሙያዎች ጭምር እያስጠናሁ ነው ከማለት ውጪ እስካሁን ተጠያቂ አካል አላስቀመጠም፡፡
50 ዓመት ገደማ የአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ መድፊያ ሆኖ የቆየውን “ቆሼ” ቆሻሻውን በመጠቀም 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያስችላል የተባለውና 120 ሚ. ዶላር የተመደበለት ፕሮጀክት ከተጀመረ 4 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን አደጋው ከደረሰበት በግምት በ100 ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
በ“ቆሼ” ከ500 በላይ ዜጎች በቆሻሻው ክምር ላይ የላስቲክ ቤቶችን ቀልሰው የሚኖሩ ሲሆን በቦታው ላይ በየቀኑ 3 መቶ ሺህ ቶን የከተማዋ ቆሻሻ እንደሚደፋ ይታወቃል፡፡ የቆሻሻው ክምር 40 ሜትር ጥልቀትና የተናደው ተራራ የ7 ፎቅ (13 ሜትር) ያህል ከፍታ አለው፡፡
ቀደም ሲል የከተማዋን ቆሻሻ ለማጠራቀሚያነት ታቅዶ በኦሮሚያ ክልል ሰንዳፋ ላይ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የፈጀ ማከማቻ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ወራት አገልግሎት ከሰጠ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች ባቀረቡት ቅሬታ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ተመልሶ አሁን አደጋው የደረሰበት ቦታ ላይ እንዲደፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡
(ከአደጋው በህይወት የተረፉ ነዋሪዎች ምን ይላሉ በሚል የተጠናቀረውን ዘገባ /እማኝነትም ጭምር ነው/  በገጽ 3 ላይ ያገኙታል፡፡)  

Read 6932 times