Print this page
Monday, 20 March 2017 00:00

መምህራን በቤት ዕጣ አወጣጡ ቅር ተሰኝተዋል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

• “የት/ቢሮው አሰራር‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው› ነው”
                            • የቤት ጥበትና ርቀት ውዝግብ ፈጥሯል
                            • ቢሮው ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም ብሏል
                    
       በማስተማርና ትውልድ በመቅረፅ ሥራ ላይ ለ34 ዓመታት ቆይታለች፡፡ አሁንም በጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ እያስተማረች ነው፡፡ የከተማው ከንቲባ ሰብስበዋቸው መንግሥት ለመምህራን ስላደረገው ‹‹አስደሳች›› ነገር ሲነግሯቸው፣ “የመማር ማስተማር ሂደት ሳይደናቀፍ ከምትኖሩበት አካባቢ የቤት ዕጣ ታወጣላችሁ” ብለዋቸው እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤት በዕጣ አውጥታችሁ ትከራያላችሁ ሲባሉ በጣም ተደስተው ነበር፡፡ ነገር ግን የሆነው ሌላ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝንና የሚያበሳጭ ነው - ትላለች መምህርቷ፡፡ ሁኔታው፤ ‹‹ፅድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ›› የሚያሰኝ እንደሆነባቸው እሷና ባልደረቦቿ በምሬት ይናገራሉ። ከንቲባው በሰበሰቧቸው ወቅት 16 እና ከዚያ በላይ ዓመት አገልግሎት ያላቸው ባለ ሁለት ክፍል ቤት ያገኛሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዕጣ ስታወጣ ግን የደረሳት ባለ 26 ካሬ አንድ መኝታ ቤት መሆኑን ገልጻለች፡፡  
የኮሌጁ አሠልጣኝ መምህራን በበኩላቸው፤ የተሰጣቸው ዕድል በጣም ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ‹‹የትምህርት ሂደቱን ቀልጣፋና የተሳለጠ ለማድረግ…›› የደረሳቸው ቦታ አሁን ከሚያስተምሩበት በጣም ሩቅ በመሆኑ አመቺ አይደለም፡፡ መምህርቷ የደረሳት አቃቂ ገላን ሳይት  ነው፡፡ ቤቱን ሄዳ አይታው ነበር፡፡ ደርሶ መልስ በአጠቃላይ 50 ኪ.ሜ እንደሆነ ተናግራለች፡፡
ለትራንስፖርት ፐብሊክ ባስ እንዲጠቀሙ ደብተር ተሰጥቷታል፡፡ ግን ባሱን ለመጠቀም በስንት ሰዓት መነሳት አለባት? ለልጆች ቁርስ ማዘጋጀት፣ ለምሳ ሳህን ማሰር፣ ቤተሰቡን ቁርስ ማብላት፤… ሌሎችም ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ይህን ሁሉ ለማከናወን በስንት ሰዓት መነሳት ይኖርባታል? ምናልባት ከንጋቱ 11 ሰዓት፡፡ ባይሳካላትና ባሱ ቢያመልጣትስ? የግል ትራንስፖርት መጠቀም ይጠበቅባታል። በግል ትራንስፖርት ለአንድ ጉዞ 21.70 ይፈጃል። ደርሶ መልስ ደግሞ 43.40 ይጠይቃል፡፡ ይህንን በ26 ቀን ብናበዛው 1128.40 ይሆናል፡፡  እንግዲህ በየወሩ ለትራንስፖርት ይህንን ያህል ካወጣች ምን ሊተርፋት ነው?
ቤቱን ሄዳ ስታይ በሕልሟም ሆነ በእውኗም ያላሰበችው ሆኖ ስታገኘው በጣም ከመደንገጧና ከመገረሟ የተነሳ ከትከት ብላ እንደሳቀች ተናግራለች፡፡ ‹‹ቤቱ 26 ካ.ሜ ነው፡፡ ከስቱዲዮም ሳያንስ አይቀርም፡፡ አንድ አልጋ ከተዘረጋ ቤቱ ይሞላል፡፡ 34 ዓመት ሙሉ ያፈራሁትን ንብረት ምን ላድርገው? ልሽጠው? እንዳልሸጠው ደግሞ ለዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያስፈልጉኝ ናቸው፤ ምን ልሁን? ግራ ገባኝ፡፡
ቤቱ የልጅ አልጋ አያዘረጋም፡፡ በዚህ ዕድሜዬ ከልጄ ጋር ቆጥ አልጋ ላይ፣ እኔና ባሌ ከሥር፣ እሷ ከላይ እንተኛ? የሚገርም ነው፡፡ ‹‹ዕዳ ከሜዳ›› ይሏችኋል ይኼኔ ነው፡፡ ሠራተኛም መቅጠር አልችልም፤ የት አስተኛታለሁ? እኔም በየቀኑ 50 ኪ.ሜ ስንከላወስ ውዬ ማታ እቤት ስገባ ለቤተሰቡ እራት ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ማለት አለብኝ፡፡ ይኼ ኑሮ አይባልም፡፡ ጥንቅር ብሎ በአፍንጫዬ ይውጣ። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሥራ ለይስሙላ ነው፤ ‹‹እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው›› ዓይነት” ስትል ተችታለች፡፡
ሌላው የትምህርት ቢሮው አሠራር ትክክል እንዳልሆነ የገለጹት ደግሞ ከ35 ዓመት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በጀነራል ዌንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ንግግራቸውን የጀመሩት በተረት ነው፡፡ ‹‹አንድ ሀብታም የከተማውን ሰው ለማብላት ግብር ጠራ፣ አስተናጋጆችም መደበ፡፡ የተጠሩት ሰዎች ሲመጡ፣ አስተናጋጆቹ ኃላፊነትና ግዴታቸውን መወጣት ስላቃታቸው የተጋበዙት ሰዎች ሳይመገቡ ተመለሱ›› በማለት የትምህርት ቢሮውን ድክመት ገልጸዋል፡፡
ብዙ ዓመት ላገለገሉ መምህራን መንግስት ያደረገው ድጋፍ በጣም ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ- መምህሩ፡፡ ‹‹አሰራሩና መመዘኛው ከመጀመሪያው ትክክል አልነበረም፡፡ ከ35 ዓመት በላይ የሰራሁት እኔ፣ የ6 ዓመት አገልግሎት ካለው ሰው በታች ነኝ። እሱ “ቤተሰብ አለው” ተብሎ ባለ አንድ ክፍል ቤት ሲያገኝ፣ ለእኔ ስቱዲዮ ነው የተሰጠኝ፡፡ ሌላው ደግሞ ርቀቱ ነው፡፡ እኔ የምኖረው አስኮ ሆኖ ቱሉ ዲምቱ ነው የደረሰኝ፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም ርቀቱ ከማስተምርበት ኮሌጅ 30 ኪ.ሜ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፤ በቀን 60 ኪ.ሜ ያህል ማለት ነው። ይህ እንዴት ይሆናል? ምን ጊዜ ተጓጉዤ ነው የማስተምረው? አሁን ደግሞ ቤተሰብ መስርቻለሁ፤ ልጅ ሊመጣ ይችላል፡፡ ልጅ ባልወልድም ብቻዬን አይደለም የምኖረው፡፡ ከዘመድ አዝማድ ከጓደኛ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤት አያስፈልጋቸውም ማለት ነው? ግራ የገባ ነገር ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹ትምህርት ቢሮው ዕጣ ከማውጣቱ በፊት ትንሽ ጥናት ማድረግ ነበረበት፡፡ እንጦጦ የት ነው የሚገኘው? ጄነራል ዊንጌትስ? ተግባረዕድስ? …. ብሎ በመለየት፣ ቤቶቹ ባሉበት ሳይት ማነው የሚቀርበው? በማለት ዕጣ እንድናወጣ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ እነሱ ግን  ስማችንን ኮምፒዩተር ውስጥ ከትተው ዕጣ አውጡ አሉን፡፡ ይኼ ልክ አይደለም፡፡ የተማረ ሰው የሚሰራው አይደለም›› በማለት ችግሩን አስረድተዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ሃላፊ፤ “እኛ ይህ ጉዳይ አይመለከተንም፡፡ የእኛ ድርሻ የመምህራኑን የስም ዝርዝር መዝግበን ለቤቶች ኤጀንሲ መስጠት ብቻ ነው፡፡ እኛ ባልሰራነውና በማናከራየው ቤት አይመለከተንም” ብለዋል፡፡
የቤቶች ኤጀንሲ በበኩሉ፤ ‹‹እኛ አሁን እያስተናገድን ያለው ቅሬታ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የሚመለከት ነው፤1ኛ ፎቅ ተብሎ 4ኛ ፎቅ የደረሰውን፤ ባለ 2 መኝታ ተብሎ ባለ 1 መኝታ ክፍል የደረሰውን ቅሬታ በመቀበል እያስተናገድን ነው፡፡ ቤት ጠበበን የሚሉት በምዝገባ ወቅት ት/ቤታቸው በፈጠረው ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለት መኝታ ሙሉ ሲባሉ፣ ባለ አንድ መኝታ ሞልተው ይሆናል፡፡ ርቀት የተባለው ለመምህራን ተብሎ የተሰራ ኮንዶሚኒየም የለም፡፡ ይኸውም የተገኘው የመምህራንን ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት ቀደም ሲል በየሳይቶቹ ሳይሰጡ የቆዩ ቤቶችን በማፈላለግ ነው፡፡ ችግሩ ያለባቸው ሰዎች በግል ሊቀያየሩ ይችላሉ›› በማለት ገልጿል፡፡

Read 2918 times