Monday, 20 March 2017 00:00

90 ዓመታት ያስቆጠረው ሙግት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(4 votes)

 አማርኛ ቋንቋ ከግዕዝ የወሰዳቸው ሞክሼ ሆሄያት ‹‹ይቀነሱ›› እና ‹‹አይቀነሱ›› የሚለው ክርክር መቋጫ ሳይበጅለት አንድ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት ናቸው የቀሩት፡፡ ይህ ልዩነት በጉልህ  መታየት የጀመረው ከ1917 ዓ.ም አንስቶ ወይም የአገራችን የሕትመት ኢንዱስትሪ ለማደግ ዳዴ ማለቱን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በወቅቱ አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ለታላቁ ሊቅ ለአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ ለአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት አንዲያዘጋጁ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር፡፡ ምክንያታቸውን እንገምት ከተባለ ለተፈጠረው ልዩነት መፍትሔ ያመጣል ብለው ስላመኑበት ሊሆን ይችላል፡፡ በአልጋ ወራሹ ተጽፎ ‹‹የአገራችንን የቋንቋ ድኽነት መቼም የምታውቀው ነው›› የሚል አጽንኦት የሰፈረበት ደብዳቤ የደረሳቸው አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ግን ለአባቱ ለግዕዝ መዝገበ ቃላት ሳላሰናዳ ለልጁ ለአማርኛ አላስቀድምም በማለት፤ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ላሉት ግዕዝ መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ  በኋላ ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› መጽሐፋቸውን  ደቀ መዝሙራቸው ደስታ ተክለወልድ በ1948 ዓ.ም አሳተሙላቸው፡፡
‹‹ግዕዝ አማርኛ›› መዝገበ ቃላትን በማሳተማቸው፤ ለአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ሥነ ጹሑፍና ለግዕዝ ቋንቋ ትልቅ ባለውለታ የሆኑት ደስታ ተክለወልድም፤ መምራቸው ማስቀደም የሚገባኝን ስጨርስ እመለስበታለሁ ብለው ለነበረው ቋንቋ ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› አዘጋጅተው በማሳተም ክፍተቱን ሞልተው ያለፉ ታላቅ የሥነ ጹሑፍ ሰው ነበሩ፡፡ ይህን መጽሐፋቸውን ለማዘጋጀት 31 ዓመታት ወስዶባቸዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ታላላቅ መጻሕፍት እንዲዘጋጁ ምክንያት የሆነው የሞክሼ ሆሄያት ‹‹ይቀነሱ›› እና ‹‹አይቀነሱ›› ክርክር መቋጫ ሳይበጅለት ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወደፊትም ተጨማሪ ዓመታት መቆጠራቸው የሚቀጥል ይመስላል፡፡ ይህን የሚያረጋግጥልኝ መረጃ ከማቅረቤ በፊት ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝንና ‹‹የሞክሼ ሆሄያት አይቀነሱ›› የሚለውን አቋም በመደገፍ ተዘጋጅቶ የታተመውን መጽሐፍ በወፍ በረር ማስቃኘቱን ላስቀድም፡፡
‹‹ለምን ይቀነሳሉ?›› በሚል ርዕስ ነው መጽሐፉ የታተመው፡፡ ባለፈው የካቲት ወር ለአንባቢያን የቀረበው የዚህ መጽሐፍ ደራሲ መስፍን መኮንን ዓለምነህ ሲሆኑ በ170 ገጾች የቀረበ ጥራዝ ነው። መጽሐፉን ለማዘጋጀት አነሳስተውኛል  በማለት በመቅድሙ የሚከተሉትን ምክንያቶች ዘርዝረዋል፡-
‹‹ለአንድ ድምፅ አንድ ፊደል ብቻ›› በሚል የሥነ-ልሣን ጥናት መርህ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የአማርኛን ቋንቋና ሥነ-ጹሑፍ ለማሳደግ የአባቱን፣ የአሳዳጊውን የግዕዝን ፊደል መቀነስ አስፈላጊና አንገብጋቢም ጉዳይ ነው በማለት በተሰአቱ /በዘጠኙ/ ተመሳሳይ ድምፅ ባላቸው የግዕዝ ፊደላት ላይ ጭካኔ የተሞላበት ውሣኔ ማስተላለፉን የሰማሁት ቆይቼ ነበር፡፡
‹ከመቆየት አልፎ በጣም የዘገየሁ መሆኔን ያወኩት ደግሞ ውሣኔውን ተከትሎ በግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ የነበረውን እና የቀድሞዎቹን የነገሥታት ታሪክ የሚተርከውን ‹‹ክብረ ነገሥት›› የሚባለው ጥንታዊ መጽሐፍ፣የተጻፉበት ፊደሎች ታርደውና ተወራርደው ከመቃብር ከገቡ በኋላ በጉባዔው የውሳኔ መዶሻ ፀንተው በቆሙ ፊደላት ብቻ መተርጎሙን ካየሁ በኋላ ነበር፡፡
‹በዚህ ድርጊት ‹‹ለምን?›› እያልኩ ከውስጤ ጋር ሙግት ገጥሜ ስብሰለሰል የጉባዔውን ውሳኔ ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ መንግስት መስተዳድርም ‹‹ለአንድ ድምፅ አንድ ፊደል ብቻ›› የሚለውን የጉባዔውን መርህ ተከትሎ፤ አባቱና መስተዋቱ የነበረውን የተወሰኑ የግዕዝ ፊደላትን ቀንሶ በጥቅም ላይ ያዋላቸው መሆኑን አቶ ይትባረክ ገሰሰ ‹‹በኪነ ጽሕፈት ጊዜ የፊደላት አቀማመጥ›› በሚል ርዕስ ጽፈው ያሳተሙትን መጽሐፍ ከአነበብኩ በኋላ ለማወቅ ቻልኩ፡፡›
የሠርግ ቤት ገጠመኜ ግን ከሁሉም በላቀ ሁኔታ ይህንን መጽሐፍ እንዳሰናዳ ኃይልና ጉልበት ሰጥቶኛል የሚሉት የመጽሐፉ ደራሲ፤ በታደሙበት ሠርግ ቤት ከሙሽሮቹ ‹‹ዘፋን›› በስተጀርባ ግድግዳው ላይ የሙሽሮቹን ስም የያዘ የ‹‹መልካም ጋብቻ›› ጽሑፍ ተለጥፎ ያያሉ፡፡ ባዩት ነገር ቅር ስለተሰኙ አብረዋቸው አንድ ጠረጴዛ ተጋርተው ለተቀመጡ እድምተኞች ቅሬታቸውን ያካፍሏቸዋል፡፡
‹‹‹አብይ›› ተብሎ የተጻፈው የሙሽራው ሥም በዚህ ፊደል ሲጻፍ ትርጉሙ ሌላ ነው፡፡ መጻፍ የነበረበት ‹‹ዐ›› በሚለው ዓይኑ ‹‹ዐ›› ነበር። ‹‹ሠላማዊት››ም የሚለው (የሙሽሪት ሥም) መጻፍ የነበረበት በግዕዝ ፊደል ሰባተኛ በሆነው ‹‹ሰ›› ነበር› እያሉ ለማስረዳት ሲሞክሩ ያልጠበቁት መልስ ገጠማቸው፡፡ ግዕዝን አላውቅም ያለ አንድ ጎልማሳ ከሰጣቸው ምላሽ ይልቅ፤ ከጎልማሳው ሀሳብ ጋር የሚስማማው መብዛቱ ይበልጥ አሳሰበኝ ይላሉ - የመጽሐፉ ደራሲ፡፡ ጎልማሳው በየትኛውም ፊደል ቢጻፍ አንብበን እስከተግባባን ድረስ ምንም ችግር እንደሌለው፣ ትርፍ ፊደሎች ‹‹ኮተት›› በመሆናቸው ምክንያት ቢቀነሱ ቅር እንደማይለው፣ ግዕዝ የሞተ ቋንቋ በመሆኑ ማወቁ ምንም ጥቅም እንደሌለው፣ በአሁኑ ዘመን ግዕዝን ማወቅ ወንዝ እንደማያሻግር…ነበር በልበ ሙሉነት ምላሽ የሰጣቸው፡፡
የሠርግ ቤት ገጠመኜ በመጀመሪያ የንዴት ስሜት ውስጥ አስገብቶኝ ነበር የሚሉት የመጽሐፉ ደራሲ መስፍን መኮንን ዓለምነህ፤ ‹‹በክርክሩ ብቀጥል ጉንጭ አልፋ እንደሚሆን ተረዳሁ›› ይላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ማንቀራበጡን ተያያዙት፡፡ አማርኛ እንዲያድግ የግዕዝ ፊደላትን ማጥፋት ለምን አስፈለገ? የአንዱ ሞት ለሌላው ሕይወት ነው የሚለው ፍልስፍና ለቋንቋም ይሰራል ወይ? አማርኛ የራሱ ባልሆነ ፊደሎች ላይ ፈላጭ ቆራጭ ያደረገው ማነው? አማርኛ የራሱ ጥቂት ፊደላት ያሉት በመሆኑ (ሸ፣ ቸ፣ ኘ፣ ጀ፣ ጠ፣ ኸ፣ ዠ) ‹‹እፍኝ›› ይዞ ‹‹አሻሮ›› ወደያዘው የተጠጋ አይደለም ወይ? ትውልዱስ የቀድሞ ታሪኩን እንዳያውቅ ከጀርባ የሚሰራበት ደባ ይኖር ይሆን? ትውልዱ ብቻ ሳይሆን የእምነት ተቋማትና መንግሥት ቋንቋው ቅርስነቱን የሚያሳጣው እንዲህ ዓይነት ደባ ሲፈጸምበት ዝምታቸው ከየት የመነጨ ነው? እጅና እግሩን ታስሮ ለመስዋዕት እንደሚቀርብ በግ፤ የግዕዝ ቋንቋን ለማጥፋት የሚረባረበው ለምን በዛ?
የደራሲ መስፍን መኮንን ዓለምነህ ‹‹ለምን ይቀነሳሉ?›› መጽሐፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ‹‹ግዕዝ አዳምና እግዚአብሔር ይነጋገሩበት የነበረ ቋንቋ ነው። የሰው ልጆችም ቋንቋቸው ከመደበላለቁ በፊት በሰናኦር ሜዳ ላይ የጀመሩትን ግንብ ለመገንባት ውል የተዋዋሉትና የተስማሙበት ቋንቋ ግዕዝ ነው፡፡ ይህንንም ታሪክና ምስጢር አውሮፓውያን ጠንቅቀው ያወቁትና የተረዱት ስለሆነ የግዕዝን ቋንቋ በጥልቀት እያጠኑት ይገኛል›› ይላሉ፡፡
ደራሲው ለዚህ አባባላቸውም ጀርመናዊው ደልማን ግዕዝን ከአባ ጎርጎሪዮስ (ከ1595 - 1658) ተምሮ በአውሮፓ እንዳስፋፋው፣ በአሁኑ ዘመን ደግሞ  ዎልፍ ሌስላው ጥናት ስላካሄደበት በአውሮፓና በአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ቋንቋው ትልቅ ቦታ እንደተሰጠው ያብራራሉ። የግዕዝ ቋንቋ  ከመግባቢያና ሀሳብን በጽሑፍ ለመግለጫነት ከማገልገሉም ባሻገር በተለይ ፊደላቱ የቁጥር ውክልና ስላላቸው የፈጣሪ፣ የፍጥረትና የዓለም ታላላቅ ሚስጢሮች የሚተላለፉበት መሆኑንም በበርካታ ማስረጃዎች ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ሂትለር የተጠቀመበት የስዋስቲካ አርማ (አገላብጦ የተጠቀመበት ቢሆንም) ንጉሥ ላሊበላ ካሳነፀው ቤተ ጊዮርጊስ ሕንፃ መስኮት ላይ የወሰደው መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
የራሱ ፊደል ያለው፣ የቋንቋ ባለቤት የሆነ ሕዝብና አገር ‹‹ማነህ?›› ሲሉት ‹‹እኔ ነኝ›› ማለት የሚያስችል ሕልውና ይኖረዋል የሚሉት የመጽሐፉ ደራሲ፤ ግዕዝን ጥሎ በያሬዳዊ ዜማ መኩራት እንደማይቻል፣ ግዕዝን ሳይረዱ ከቀድሞው ዘመን ትውልድና ሥራ ጋር መግባባት የማይታሰብ እንደሆነ … በዚህ ሂደት ‹‹እኛ›› ጠፍተን ‹‹ሌላ›› የምንሆን  ከሆነ አቋማችን፣ ፍርዳችን፣ መርሀችን … ሌሎችን ይመስላል በማለት ማሳያ ያቀርባሉ፡፡
‹‹የጥንቱ የኢትዮጵያዊያን ሥልጣኔና ታላቅነትን ስናጠና በውስጡ የምናገኘው የሥልጣኔ ኅብር፤ ቅድስናን፣ ደግነትን፣ እውነትን፣ ውበትን፣ ጠቃሚነትን ነበር፡፡ በምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ውስጥ እነዚህን አናገኝም፡፡ የሥልጣኔው መሠረት ጠንካራው በደካማው ላይ የገዢነት መብት አለው በሚል ፍልስፍና፤ ደካማውን ባሪያ አድርጎ በግፍ በመበዝበዝ የተገነባ ሃብትና ብልፅግና በማግበስበስ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው …››
ይህንን መጽሐፍ እንዳሰናዳ ኃይልን ጉልበት የሰጠኝ የሠርግ ቤት ገጠመኜ ነበር ያሉት ደራሲ መስፍን መኮንን ዓለምነህ፤ የሙሽሮቹ ሥም የተጻፈበት ሆሄ ማስተላለፍ ከተፈለገው መልዕክት በተቃራኒ ነው የሚገልጸው ስላሉት ጉዳይም በገጽ 112 ‹‹ሠ›› ማዕከል አድርገው ማብራሪያ አቅርበውለታል። ፊደሉ በግዕዝ የራሱ የሆነ ቁጥር እንዳለው፣ አምላክ በሥጋ መገለጡን እንደሚወክል፣ ንጉሡ ‹‹ሠ›› ተብሎም እንደሚጠራ፣ የፊደሉ ቅርፅ ወደ ላይ መውጣትንና ከፍ ከፍ ማለትን  እንደሚያሳይ፣ ማማርንና መዋብን እንደሚያመለክት፣ በዚህም ምክንያት ሆሄው ‹‹ሥነ-ሥዕል››፣ ‹‹ሥነ-ሕንፃ››፣ ‹‹ሥነ-ምግባር›› … እንደሚፃፉበት ያብራራሉ፡፡ ‹‹ይህ መረጃ ሠናይት›› ለምን በንጉሡ ‹‹ሠ›› መጻፍ እንዳለበት ምላሽ ይሰጣል፡፡ በተቃራኒው ‹‹ሰ›› የራስ ያልሆነ ነገርን ስለመውሰድና ስርቆትን ስለመሳሰሉ ነገሮች አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ማብራሪያ ቀርቦለታል፡፡
የሞክሼ ሆሄያት ‹‹ይቀነሱ›› እና ‹‹አይቀነሱ›› የሚለው ክርክር መቋጫ ሳይበጅለት ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወደፊትም ተጨማሪ ዓመታት መቆጠራቸው የሚቀጥል ነው የሚመስለው ላልኩት ሀሳብ ማሳያዬ የማህበራዊ ጥናት መድረክ መጽሐፍ ነው፡፡ ‹‹ከድኅነት ወደ ልማት፡- ዕውቀትን ለትውልድ ማስተላለፍ›› በሚል ርዕስ 17 ጥናታዊ ጹሑፎችን በአንድ ጥራዝ ሰብስቦ በ2006 ዓ.ም ለአንባቢያን የቀረበው መጽሐፍ መቅድም ላይ የመጽሐፉ አርታኢ፤ የሞክሼ ሆሄያት፣ የሰዋስውና የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀምን በተመለከተ መቸገራቸውን እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡
‹‹ይህንን መጽሐፍ ስናዘጋጅ አንዱ ትልቅ ችግር የአማርኛ ሞክሼ ሆሄያት ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ሞክሼ ሆሄያት አጠቃቀም፣ ሁሉን የሚያስማማና መሪ ሊሆን የሚችል ማጣቀሻ መጽሐፍ የለም፤ ያለው አማራጭ ውሳኔውን ለደራሲው መተው ነው፤ በዚህ የተነሳ፣ የሆሄያት አጠቃቀም ዝብርቅርቅ ያለ ሆኗል፡፡ ሌላው የአርትኦት ችግር፣ የተለያዩ ጸሀፊዎች የሚጠቀሙበት የአጻጻፍ ዘዴ ወይም ስታይል ነው፡፡ የሰዋስው ጉዳይም ያለቀለት ነገር አይደለም…
‹‹ሶስተኛው ተግዳሮት ስርአተ ነጥቦችን ይመለከታል፡፡ የስርአተ ነጥቦች አጠቃቀምን አስመልክቶ፣ ልክ እንደ ሞክሼ ሆሄያቱ፣ በቋንቋው ሊቃውንት ዘንድ ሙሉ መግባባት የለም፡፡ ነጠላ ሰረዝንና ድርብ ሰረዝን የአማርኛ ሊቃውንት በተለያየ ሁኔታ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡›› በማለት ጉዳዩ መፍትሔ እየራቀው የመጣ መሆኑን ግልጽ በሆነ ሁኔታ አስቀምጠውታል፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለ90 ዓመታት ሙግት ተካሂዶበት አንድ እልባት ላይ መድረስ ያልተቻለው ግን ለምን ይሆን?! 

Read 2539 times