Print this page
Saturday, 18 March 2017 15:34

አንተም ብቃን በቃ…!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 አይ ምስኪን ሃበሻ…
ለሞትም ሸበላ…
‹‹ሞቴን አሳምረው…!›› ይላል ምልጃ ጠርቶ
በሞቱ ላይ ነግሶ… አሟሟቱን ፈርቶ
ከመቃብር በላይ… ለፃፈው ስም ሳስቶ
በቆሻሻ ደጀን… መንደሩ ተሞልቶ
ትንፋሹን ተነጥቆ… ሰርኑ ተሰንፍጦ
በአቤት ባይ እጦት… ተስፋው ፈሶ ቀልጦ
በፍትህ-ቢስ ሃገር እንባውን ‹‹ተቀርጦ››
የዘመን ዳኝነት ተረቱን ገልብጦ
…….. ‹‹ከደጃፉ ዛፍ ላይ ሞፈር ሳይቆረጥ
…….. እየሞተ ኖሮ…
…….. እየኖረ ሞቶ…
…….. በቁም ተቀበረ… በጉዳፋ ረመጥ…!!

አቤቱ ፈጣሪ…
‹‹ሞቴን አሳምረው…!›› የሞትም ቆንጆ አለ
ብሎ ለሰገደ…
መኖር ለገደፈ…
የምህረትህ ባህር… ለምስኪን ካልዋለ
ምነው ባልፈጠርከው… ውሃ ሆኖ ቢቀር
‹ለሃረጓ ሙሾ› እንኳን
ካልሆነለት ሞቱ… በሙሾ ሙሉ ሃገር…!

አቤቱ ፈጣሪ…
ኑሮዬን ትቻለሁ
አደራ አሟሟቴን… ብሎ ሲማፀንህ
ለሃበሻ ምድር… ካልሆነ ምህረትህ
እሺ ስንቴ ይሙት… ስንቴስ ይሁን ሬሳ
ለየቱስ አልቅሶ… የቱን ቀብሮስ ይርሳ…

መሞትን ሸልመህ… ከምትነሳው ፍታት
በድኑን ሳይገንዝ… ድንኳን ሳይጥልለት
ትኩስ ሬሳ ታቅፎ… ደረት ሳይደቃለት
በእንባ ጎርፍ ታጅሎ… ዋይ ዋይ ሳይልለት
ሙሾ ሳይወርድለት… ሰልስቱ ሳይወጣ
እንዲህ ከምትቀጣው… ወይ ፍርድህን ስጣ
እንደ ሰዶም በእሳት… ካሻህም በውሃው
በርግማንህ ወጀብ… ምናለ ብትጠርገው…
አቤቱ ፈጣሪ…
ዘነጋኸው እንዴ…
በሃበሻ ምድር… አንተው በፈጠርከው
ቋሚ ቀሪ ዕድሜውን…
በሃዘን ግርፋት… በየዕለት ሚሞተው
ከሟች መሞት በላይ… ባሟሟቱ እኮ ነው…!

እናም ፈጣሪ ሆይ…
ኦሪት መዝገብህን… ድሮ የተፃፈው
ከዚህ ሙት ኑሮ ጋር… አነፃፅሬአቸው
እኔም ሚስቱን እንጂ… እዮብን ስላልሆንኩ
አትቆጣኝና… እንዲህ ልልህ ደፈርኩ

‹‹ለዚች ቅድስት አገር… ለቆረበች ላንተ
ከዓለም ለይተህ…
ምህረትህ ካደላ… ሚዛንህ ከሳተ
ይብቃሽ ብለህ ባርከህ… ካልበቃን ሰቆቃ
ከዚህስ አይብስም… አንተም ብቃን በቃ…!››

ጥላሁን አበበ (ወለላው)
(መጋቢት 05፣ 2009 ዓ.ም)
ድሬ ዳዋ
በድጋሚ ለመላው ኢትዮጵያዊ መፅናናትን ተመኘሁ!!

Read 4150 times
Administrator

Latest from Administrator