Saturday, 18 March 2017 15:36

‹‹ቆሼ›› ሞክሼ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

 የዘንድሮ ግፍ አያልቅም፣ ከጎርፍ እስከ ድርቅ ድረስ
ነው እያልን፤ ስናነባ፣ ስም ስንቀያይር እንደዋስ
ባልታጣ መሬት ተጣበን፣ ጥቅም ስንለካካ
ከወገን፤ ቦታ በልጦብን፣ ስንሟገት ተካ-አልተካ
በካሣ እምቢ በካሣ እንካ
ባለልክ መካለል ጠኔ፣ ስንሻኮት ያለዱካ
ይሄው ላደጋ ተዳረግን፣ በቆሻሻ ናዳ ፉካ!
ቆሻሻ ታጥነን አድገን
ቆሻሻ አጥነን አሳድገን
ልጃችንን፤ ፍሬያችንን
‹‹ከአመድ ወደ አመድ›› እንዲሉ፣ በገዛ ቤታችን ቀበርን!!
እናት አጣን፣ ህፃን አጣን!
አባት አጣን፣ ወንድም እህት ተቀጨብን!
ጊዜ እንደ ድንገት፤ ደራሽ ወንዝ፣ በቆሻሻ ጎርፍ ወሰደን
እንደ ፍካሬ - የሱስ ቃል፣ ያለምልክት ተዋጥን!
አያ ሞት ይለው አያጣ
ድሀ፤ ሳይኖር ሲሞት አይቶ፣ የአገሩን ልቅሶ አስተውሎ
‹‹ቆሼ››፤ ሞክሼ ነው አለ አሉ፤ ስሜን ንጠቀኝ ብሎ!!
ሞት ጉዱ አያልቅም አቦ
እንዲህ ሲል ሰማሁትኮ!
ናዳ ናዳ እሚያህል ጎርሶ፣
በህፃናት አፉን አብሶ፤ ጠግቦ ሲያበቃ ደሀ አፍሶ፡-
   ‹‹ዕድሜ ለሀብታም ‹ቱሩ›!
    ዕድሜ ለቆሼ ልጆች፣ እየኖሩ ለማይኖሩ
    ዕድሜ ለአበሻ አቃጆች
    አደጋ ካላዩ በቀር፣ ቅን-መፍትሔ ለማይቸሩ!››
ከቶም ህያው ትንፋሽ አጥሮን
ዙሪያ-ገባችን ታጥሮብን
‹‹አድኑኝ›› ከማለት ጣዕር፤ ታፍኖ ከመሞት ያውጣን!
‹‹የባሰ-አታምጣ››ም እንዳያልቅ፣ እሱ ጥናቱን ይስጠን!!
(በቆሼ ሠፈር አደጋ ሰለባ ለሆኑትና
 ሐዘን ለተቀመጡ ቤተሰቦቻቸው)
መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም

Read 2599 times