Monday, 20 March 2017 00:00

የናፍቆት ስዕሎች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 ብዙ ካፍቴሪያ ብዙ ሬስቶራንት ውስጥ፣ ፎቶዋ ከነድምፅዋ ይታወሰኛል፡፡ ሳቅዋ … ፈገግታዋ … ቁጣዋ … ምሬቷ … ስድብዋ ሁሉ! ያኔ ፍቅራችን ህያው ሳለ፣ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ ስልክዋን እጠብቃለሁ … እሷም እንዲሁ ትጠብቃለች፡፡ ወደ አራት ሰዓት ከተጠጋ “ምን ሆነህ ነው!” ትላለች፡፡
“ምኑ?” እላታለሁ፣ ልቤ እያወቀ፡፡
“ብ…ሽ…ቅ!”
“ራስሽ ብሽቅ!”
ከዚያ ወሬ እንቀጥላለን፡፡ … ቀን ሙሉ የገጠማትን፣ የቢሮ ውሎዋን፣ የጓደኞቿን ስልክ፣ አንድም አይቀራት! … እኔም እንደሷው ነኝ፡፡ የባጥ የቆጡን እቀባጥርላታለሁ፡፡ ለምን እንደምወዳትም አይገባኝም፡፡ ኃይለኛ ናት፣ ትቆጣለች … ግን ደርሶ መልዐክ ትመስለኛለች። እንደ ፅጌረዳ፣ እሾህና አበባ ናት እንዳልል፣ አበባዋን ደብቃ፣ እሾህዋን ታሳየኛለች። ግን አልቀየማትም፡፡
ካፌ ስንሆን ጉርሻዋ አያምጣው! ኬኩን ማጉረስ ነው… ፍርፍሩን ማጉረስ ነው … ጨጨብሳውን ማጉረስ፡፡ ለዚህ ይሆን እናቴን የምትመስለኝ! … ፀባይዋ አንዳንዴ የጓደኛዬን የምንቴን እናት ይመስለኛል፡፡ የምንቴ እናት ልጃቸው፣ በልቶ የሚጠግብ አይመስላቸውም፡፡ ሲያጎርሱት በላይ በላዩ ነው፡፡ ሲያጠፋ ደግሞ አያድርስ! ይቀጠቅጡታል፡፡  
ኪያም እንደሳቸው ናት፤አጉርሳ አጉርሳ፣ ስትደበድብ አያምጣው! … በዱላ አይደለም፣ በምላሷ ነው፡፡ አንድ ቀን “አታጉርሺኝ!” አልኳት፡፡ ከንፈሮቿ አበጡ፡፡ ጥርሶችዋ ሸሹ! ካልሳቀች ደግሞ አታምርም፡፡ ውበቷ ሳቋ ነው፡፡ … የፊትዋ ፀሐይ ጥርሶቿ ናቸው፡፡
“ምናባክ ሆነህ ነው! … ደበርኩህ?”
“እ…. ተናገር እንጂ! …”
ዝም፡፡ … በጥፊ አጮለችኝ፡፡
“እረፊ አንቺ ሴት!” አልኳት፡፡ ሳሚ ካፌ ነበር የተቀመጥነው፡፡ አስተናጋጅዋ ሳቅዋን ዋጠችው፡፡ በልቧ አልጫ ያለችኝ መሰለኝ፡፡
ለመሄድ ብድግ ስል “ተቀመጥ!” አለች፡፡
“አልቀመጥም!” ስላት፣
“በቃ - ይቅርታ!”
ተናደድኩ፡፡ የልብ ሰርቶ ይቅርታ ምን ያደርጋል! ተቀመጥኩ፡፡ የቀደም ታሪኳን አንስታ አወራችኝ። አንጀቴ በቅናት ቅጥል አለ፡፡ … በተለይ በጣም የምትወደውን ጥቁር ከሰል የመሰለ ጓደኛዋን አስታውሳ በቅናት ገረፈችኝ፤እኔን የናቀችኝ መሰለኝ። ጓደኛዋ አፀዱ ቀይ ወንድ እንደምትጠላ ነግራኛለች። ውስጤን ከነከነኝ፡፡ እኔ ደሞ ቀይ ሴት አልወድም። እሷን የወደድኳት ቸኮሌት ስለምወድ ነው፡፡ ማኪያቶና ቸኮሌት እወዳለሁ፡፡ የበሰለ ብርቱካን እንኳን አልወድድም፡፡
“ተይ አታስቀኚኝ” አልኳት፡፡
“እንድትቀና አይደለም! .. ይበልጥ እንድትወድደኝ ነው!”
“ከዚህ በላይ እንዴት ልውደድሽ?”
“አላውቅም!”
ብዙ ቀን እንጣላለን፣ መልሰን እንታረቃለን። እውነት ለመናገር ከርሷ ጋር ፍቅር ከጀመርኩ በኋላ ለመኖር ያለኝ ጉጉት ጨምሯል፡፡ ጥሩ እንቅልፍ እተኛለሁ፣… ቀኑን ደስ ብሎኝ እውላለሁ! … በናፍቆትዋ ስሰቃይ እረካለሁ፡፡ የእርሷን ግን አላውቅም፡፡
አንዳንዴ ሙዚቃ ትመርጥልኛለች፣ መጽሀፍ ትገዛልኛለች፡፡ ፖስት ካርድ ትሰጠኛለች፡፡ ክብ ፊትዋ፣ ጠይም መልኳ፣ ጣፋጭ ድምፅዋ … ሁለመናዋ ደስ ይለኛል። … ነገርዋን ነው የምጠላው! ቢሆንም ተቻችለን ስንኖር ቆይተን፣ አንዴ ከበድ ያለ ፀብ ተፈጠረና ተለያየን፡፡ … አኮረፈች፡፡ … ለመንኳት፣ … እምቢ አለች፡፡ የምችለውን ሁሉ አደረግሁ። .. ልትመለስ ግን  አልቻለችም፡፡ … እናም የእኔና የእሷ ነገር አበቃ! …
ቁስሉ ለዓመታት ፀናብኝ፡፡ እኔም ጠጪ ሆንኩ። ሲጋራም ማምለጫዬ ሆነ፡፡ ብዙ ነገሬ ተዘበራረቀ፡፡ እሷም አሜሪካዋ ገባችና ጠፋች። በቃ ተጠፋፋን። አንዳንዴ የሰጠችኝን ፖስት ካርዶች፣ ፎቶግራፍና መጻሕፍት እያየሁ ከመብሰልሰል በቀር ሌላ አማራጭ አጣሁ፡፡ በቃ!
አሁን በቅርቡ እንደ ፍቅረኛ የቆጠርኳት ወዳጄ ያን ያህል ልቤ አልገባችም፡፡ እሷን ልታስረሳኝ አልቻለችም፡፡ ስለዚህ ሰቀቀኑ ውስጤ እንደ ባንዲራ ይውለበለባል። አንዳንዴማ መግቢያ አጣለሁ። አብረን ያሳለፍንባቸውን ቦታዎች ሳይ፣ ራሴን መቆጣጠር ያቅተኛል፡፡
‹‹ያቺን ጣዖት ዛሬም አልረሳሃትም?” ትላለች ፀዲ፡፡ ፀዲ አዲሷ ፍቅረኛዬ፡፡
‹‹አቅቶኛል›› ስላት፣ አትማረርም፡፡
“ለምን አትደውልላትም!” ትለኛች፤ ከልብዋም ባይሆን፡፡
‹‹እዚህ እያለች እምቢ ያለችኝ አሜሪካ ገብታ ምን ይሁን ብላ ትታረቀኛለች!››
‹‹አሜሪካ ያንተ ዐይነት ሀቀኛ አፍቃሪ አይገኝም፤ አሉ ችርቻሮ ነው… ስለዚህ… ማን ያውቃል!›› ታላግጣለች፡፡
ሠሞኑንም እንዲሁ ትዝ እያለችኝ ነበር ስራ የገባሁት፡፡ ማታ ማታ ተረኛ እየሆንኩ ቀን ቀን ማንቀላፋት፣ የሞያዬ ትሩፋት ስለሆነ ምንም አልመሰለኝም፡፡ … ግን እዚህች ሀገር ላይ ሀኪም መሆኔ ደስ አያሰኘኝም፡፡ በዚህ ዘመን ሲቪል ኢንጂነር መሆን ነበር! እላለሁ ሁሌ፡፡ ግን ያለፈን ነገር መመለስ አይቻልም፡፡
በተለይ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት መሆኔ ህይወት ተረት እንዲመስለኝ ሳያደርገኝ አልቀረም፡፡ ቢሆንም ከዚህች ውዴ ጋር ብሆን፤ ታስረሳኝ ነበር፡፡ እየወጋች እያደማች፤ እያቆሰለችኝም ከርሷ ጋር በኖርኩ!
ጧት ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ፤ ኬክ ነገር ቀማምሼ ወደ ሥራ ስገባ፤ እንደዚሁ ትዝ አለችኝና ተረበሽኩ፡፡ በተለይ ጓደኛዋን የምትመስል ልጅ ሳይ፣ቴአትር ቤት ገብተን ያየነው ቴአትር ሁሉ መጣብኝ፡፡ “ባቢሎን በሳሎን”ን ያየን ቀን እንዴት ነበር ያሽሟጠጠችብኝ! አቤት ሽሙጥ ስትችል!
‹‹ይሄ ሰውዬ አንተ ነህ!...›› አለችኝ፡፡
“የቱ?” አልኳት፡፡
‹‹ይሄ ሞዛዛ!››
አኮረፍኳት፡፡ እኔ ሞዛዛ ነኝ! ብዬ፡፡
ይህን እያሰላሰልኩ ወደ ሥራዬ ገባሁ፡፡ መግቢያ ላይ አዳዲስ ሴትና ወንድ ጓደኞቼ አጅበውኝ ሳለ ድንገት ሁላችንንም አንድ ድምፅ ረበሸን፡፡ ድንገተኛ ክፍል አካባቢ ሀኪም ብዙ አይረበሽም፡፡ ልቅሶና ዋይታውን ይለምደዋል፡፡ ቢሆንም ሮጥ ሮጥ ብለን ሄድን።
በዚህ መሀል አንድ ወረቀት እጄ ገባ፡፡
‹‹የምን ወረቀት ነው?›› አልኩ፡፡
የሰማኝ የለም፡፡ ለምን እንደገለጥኩትም አላውቅም፡፡ ከፈትኩት፡፡ የኔ ስም አለበት፡፡
“አዝናለሁ እጅግ አዝናለሁ፤ ምህረትህን እፈልጋለሁ ተቀጥቻለሁ፤ ተጎድቻለሁ…እንዳንተ የሚሆንልኝ ሰው አላገኘሁም!”
ተወርውሬ እንባዬን እየደፋሁት፣ ወደ ድንገተኛ ክፍል ገባሁ፡፡
‹‹ምን ሆና ነው?--- ምን ሆና ነው?›› እያልኩ ስጮህ፣ የሚያውቁኝ ሁሉ ከበቡኝ፡፡
‹‹የመኪና አደጋ ነው… ዲያስፖራ ናት!››
‹‹ትተርፋለች?››
መልስ የሚሰጥ ጠፋ፡፡
“ወደ ጥቁር አንበሳ ነበር አሉ የምትመጣው!”
‹‹በምን ውስጥ ነበረች?
‹‹በአዲሱ ታክሲ!... የውበት እስረኞች!››
ጩኸቴን አቀለጥኩት፡፡
“ት-ተ-ር-ፋ-ለ-ች-!?”
ሊያረጋጉኝ ሞከሩ፡፡
‹‹እየጠራችህ ነው!›› ብለውኝ ስገባ፣ ዐይኖችዋ ብቻ ናቸው የቀሩት፤ ከስታለች፡፡
እላይዋ ላይ ወደቅሁኝ! የለችም!!

Read 705 times