Monday, 20 March 2017 00:00

መሙላት እና መጉደል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!”
                       ከሃምሌት

      መፅሐፍ አንብቦ የማያውቅ ሰው ሁሉ ይኼንን መፈክር እየተጋተ ይመላለሳል፡፡ ሙሉ ሰው ለመሆን የማይመኝ ማን አለ? … ሞልቶለት የማያውቅ ቢሆንም ሙሉ ሰው መሆንን ያልማል፡፡ ለመሆኑ መፅሐፍ … መፅሐፍ እየተባለ የሚጠራው ነገር በቅርፅ የተጠረዘ የወረቀት ክምር ከመሆን በዘለለ ይዘቱ ምንድነው? ብሎ የሚጠይቅ ይኖራል፡፡ ቅርፅ ላይ የመፅሐፉ ምንነት ትርጉም አሻሚ አይደለም፡፡ አወዛጋቢው የይዘት ጉዳይ ነው፡፡
መፅሐፍ አዟሪነት የስራ መደብ ነው፡፡ በዚህ የስራ መደብ የተሰማሩ ወጣቶች እንደ ታክሲ ተራ አስከባሪ የመፅሐፍት ተራራ ተሸክመው ወዲህ ወዲያ ይላሉ። ቀና ብዬ እንዳላያቸው ተጠንቅቄ አልፋቸዋለሁኝ። በአይኔ አይናቸውን ካየሁ የተሸከሙትን መሬት አስቀምጠው ጭቅጭቅ ይጀምሩኛል፡፡ “መርጠህ አንዱን ግዛ” ነው ጭቅጭቃቸው፡፡ የጭቅጭቃቸው ኃይል “መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!” የሚለው መፈክር ነው፡፡ “መፅሐፍ መጥፎ ነው” ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ማንም የለም፡፡
ማርያም ቤተ ክርስቲን ፊት ቆሞ በድፍረት “ማርያም አታማልድም!” ከማለት ያላነሰ ድፍረትና ጠብ አጫሪነት የተጠናወተው ብቻ ነው አፉን ሞልቶ “መፅሐፍ አያማልድም” ማለት የሚችለው፡፡
መፅሐፍትን ሳይሆን መፈክሩን ነው እኔ የምፈራው፡፡ ግን እየፈራሁም አሮጌ መፅሐፍት ተራ ኪሴ ከበድ ሲል እሄዳለሁኝ፡፡ ኪሴ ሲከብድ … አእምሮዬ የቀለለ ለምን እንደሚመስለኝ አይገባኝም።
ከብሔራዊ ትያትር ጀርባ … ከበድሉ ህንፃ ፊት ለፊት መደዳውን በትንንሽ አርከበ ሱቆች ውስጥ የተደረደሩ አሮጌ መፅሐፍ ሻጮች ይገኛሉ፡፡ … “መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለው መፈክር የፈጠራቸው ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ማንበቡ እንጂ ሙሉ ሰው የሚያደርገው ከመነበብ በፊት መፅሐፉን የሚፅፍ ስለማስፈለጉ ትንፍሽ የሚል አይገኝም፡፡ መፅሐፉን ለመፃፍ መጀመሪያ ሰውየው መሙላት ይኖርበታል፡፡ ከሙላቱ ቀንሶ ነው ወደ መፅሐፉ እውቀቱን የሚያፈሰው፡፡
ግዴለም! ለማንኛውም አሮጌ መጽሐፍት ተራ ኪሴ ሲሞላ ጎራ እላለሁኝ፡፡ አንዳንዴ እንደ ሴተኛ አዳሪ መንደር ይመስለኛል ቦታው፡፡ መስለው የታዩኝን ገልጬ ነግሬያቸው ግን አላውቅም፡፡ እደብቃቸዋለሁኝ፡፡ ምክኒያቱም መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ስለሚያደርግ ነው፡፡ መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ መፅሐፍ አቅራቢውን በሴተኛ አዳሪ መመሰል … የጉድለት ሰባኪ መሆን ነው፡፡ ቅልብስ ስነ ልቦና አለው ይኼ ራሱ፡፡
ደንበኛ አለኝ፡፡ ገና ሲያየኝ ፈገግ ይላል፡፡ ከእኔ ኪስ ትንሽ ገንዘብ ተቀንሶ ወደሱ ኪስ እንደሚገባ እርግጠኛ ስለሆነ ነው ፈገግ የሚለው፡፡ አንዳንዴ ወደ እሱ ሱቅ ከመድረሴ በፊት … ደረሰልኝ ብሎ ለሀጩን እያዝረበረበ ሳለ ድንገት እጥፍ ብዬ ሌላ ነጋዴ ሱቅ ጥልቅ እላለሁኝ፡፡ በጠለቅሁበት መፅሐፍ ይቀርብልኛል፡፡ ያንንም ያንንም እያነሳ መጀመሪያ ይሰጠኛል፡፡ ምን አይነት መፅሐፍ እንደምፈልግ ለማወቅ ነው፡፡
በቀላሉ የሚገኙና በፍፁም የማይገኙ መፅሐፍትን አውቃለሁኝ፡፡ ለምሳሌ የኧርቪንግ ዋላስ መፅሐፍ ካልኩኝ በቀላሉ የሚገኝ መፅሐፍ ነው የጠራሁት፡፡ እንግሊዝኛ ማንበብ እንጂ ገና ማጣጣም ያልጀመረ አንባቢ ምርጫ ነው፡፡ ነጋዴው ደስ የሚለው ይኼን አይነቱ አንባቢ ነው፡፡ በቀላሉ ከደረደረው ክምር እየናደ፣ በዚህ መሰሉ መፅሐፍ ሊያጥለቀልቀው ይችላል፡፡
እኔ ግን ጨዋታ ሲያምረኝ እንደ ኧርቪንግ ዋላስ የመሰለ ቀላል ሚዛን ደራሲ እጠራለሁኝ፡፡ መፅሐፍቱን በእጄም በአገጬም በጥርሴም እንድነክስ አድርጎ ካዥጎደጎደብኝ በኋላ … በቀላሉ የማይገኝ የኧርቪንግ ዋላስን መጽሐፍ እጠራበታለሁኝ - “The Seventh Secret” የሚለውን ነው የፈለኩት እለዋለሁኝ፡፡ ድንገት ነጋዴው ኩምሽሽ ይላል። The Seventh Secret” በቀላሉ የማይገኝ ቀላል መፅሐፍ ነው፡፡ በከባድ ፍለጋ የሚገኝ የቀላል ሚዛን ደራሲ ስራ ነው፡፡ የነጋዴው አገጭ በተስፋ መቁረጥ ይንጠለጠላል፡፡ የተንጠለጠለውን አገጩን ትንሽ ተስፋ ሰጥቼ ሰብሰብ እንዲያደርግ እረዳዋለሁኝ፡፡
ኧርቪንግ ዋላስን ትቼ ኧርነስት ሄሚንግዌይን ስጠኝ እለዋለሁኝ፡፡ ሄሚንግዌይ የኖቤል ደራሲ ነው። ከባድ ሚዛን ነው፡፡ ግን ገበያ ላይ ይገኛል። ተንኮሉ ያለው የትኞቹ መጽሐፍቱ በገበያ ላይ እንደሚገኙ ማወቁ ላይ ነው፡፡ በህንዶች የታተመ “The Old Man and the Sea” መፅሐፍ እንደ አፈር ይገኛል፡፡ “The Snows of Kilimanjaro and other Stories” የሚለውም እንደ ቁንጫ ከሰው እጅ ወደ አሮጌ ተራ ሲፈናጠር ይገኛል፡፡
የማይገኘው የቱ እንደሆነ አውቃለሁኝ፡፡ ለምሳሌ፡- “For Whom the Bell Tolls” አይንህ እስኪፈስ፣ ጫማህ እስኪያልቅ ብትፈልግ አታገኘውም፡፡ እንዲያውም የአንድ ሰውን የአንባቢነት መፈተን የፈለገ የማይገኙ መፅሐፍት የት እና ማን ጋ ማግኘት እንደሚቻል በመጠየቅ ብቃቱን መፈተን ይቻላል፡፡ … ምናልባት መጽሐፍትን አድኖ ለማግኘት ብቁ ከሆነ ያደነውን አብስሎ መመገብ (ማንበብ) ላይከብደው ይችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን መፈክሯ “Operative phrase” ናት፡፡ መፈክሯ “መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!” የምትለዋ መሆኗ እንዳትዘነጋ፡፡
የመፅሐፍቱን ሚዛን ከፍ እያደረኩ … ግን ከመደርደሪያው ላይ በቀላሉ አውርዶ “ይኼው!” እንዳይለኝ እየተጠበብኩ … ትንሽ ካንገላታሁት በኋላ … በተስፋ መቁረጥ ጭንቅላቴን ነቅንቄ ድንገት ከጠለቅሁበት ሱቅ እወጣለሁኝ፡፡ … መጽሐፍ ሸመታ የድርድር ጥበብ የሚንፀባረቅበት መድረከ ነው፡፡ ›
በድርድር ህግ፤ ቶሎ መስማማት የዋህነትን አመላካች ነው፡፡ ገንዘብ ከእኔ ኪስ በቀላሉ ወጥቶ ወደ መፅሐፍ ነጋዴው ኪስ ከገባ በጨዋታው ህግ ተሸናፊ ነኝ፡፡ ሞኝ፤ የዋህ እና ተሸናፊ ነው። ለመግዛት ወስኖ የመጣውን መፅሐፍ ከአንዱ ቢያገኝ እንኳን በአንዴ መግዛት የለበትም፡፡ ትንሽ ማልፋት አለበት። ሻጩም ገዥውም ትንሽ ላብ መጥረግ ይገባቸዋል። ይህ ደግሞ በግዢ እና ሽያጭ አለም ብቻ ሳይሆን በእንስሳትም ግዛት ተመሳሳይ ነው፡፡ አውሬም እኮ የቋመጠለትን በቀላሉ ካገኘ አቅሙን መፈተን ይሳነዋል፡፡ ይሰንፋል፡፡ ድመት አይጥን በቀላሉ ከያዘቻት በኋላ በአንዴ ወደ አፏ አትጨምራትም። ትጫወትባታለች፡፡ አቅሟን እንደ እስፖርት ለማሰልጠኛ ትጠቀምባታለች፡፡ ለቀቅ - ታደርጋትና ለማምለጥ ስትሞክር ዘላ ትይዛታለች፡፡
እኔ እያደረኩ ያለሁትም ተመሳሳይ ነው፡፡ የእኔን የመፅሐፍት እውቀት በሻጩ ላይ መሞከር አለብኝ። ሙከራዬን ደግሞ በተገቢው ሁኔታ አፀፋዊ ምላሽ የሚሰጥ ተፎካካሪ ካገኘሁ - አልፍቼ - እኔም ለፍቼ በመጨረሻ እገዛዋለሁኝ፡፡
ስለዚህ ተራ በተራ እፈትናቸዋለሁኝ፡፡ “የመጀመሪያውን እትም ካልሆነ አልፈልግም” ሁሉ ልላቸው እችላለሁኝ፤ በጨዋታው አስጨንቀው ሊረቱኝ እንደሆነ ከፈራሁኝ፡፡ ግን ሙሉ ጨዋታ ብቻም አይደለም አላማዬ፡፡ የእውነት የምፈልጋቸው መፅሐፍት አሉ፡፡ ለምሳሌ የቡካውስኪ ማንኛውንም መፅሐፍ ይዣለሁ የሚል ካገኘሁኝ … በአንድ አፍ መክፈሌ አይቀርም፡፡
ችግሩ መፅሐፉን ይቅርና ደራሲውን እንኳን ሰምተውት የሚያweቁ ገጥመውኝ አያውቁም፡፡ የደራሲውን ስም ከነገርኳቸው በኋላም ማስታወስ የቻሉ የሉም፡፡ ስለዚህ በስተመጨረሻ አሸናፊው እኔ እሆናለሁኝ፡፡ ማሸነፍ ማለት መሸነፍም ነው፡፡ ብር ሳላወጣ እንደ አመጣጤ መመለስ ማሸነፍ ከሆነ … “መፅሐፍት ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል›› በሚለው መፈክር አንፃር ደግሞ ተሸናፊ ነኝ፡፡
ምክኒያቱም፤ መጽሐፍ ተነቦ ወደ ሙሉ ሰውነት ከማደጉ በፊት ሙሉ አድራጊው መፅሐፍ መሸመት አለበት፡፡ ሳይሸመት የሚነበብ መፅሀፍ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ተውሼ የማነበው መፅሐፍም… የሆነ ሰው ከሆነ ቦታ ገንዘቡን አውጥቶ የገዛው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ደንበኛዬ ጋር የምደርሰው መጨረሻ ላይ ነው። እጄን ይመለከታል፡፡ መፅሐፍ ከሌሎቹ ገዝቻለሁ ወይንስ አልገዛሁም የሚለውን ለማረጋገጥ፡፡ መፅሐፍ ነጋዴ እንደ ሴተኛ አዳሪ ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ ከሌላ ሰው ከገዛሁ መፅሐፉን ነጥቆ ይመለከተዋል፡፡ ‹‹ምን አይነት መፅሐፍ ቢሆን ነው የገዛኸው?›› እንደ ማለት በቅናት ይመለከተዋል፡፡
ተመልክቶ ‹‹ልክ ነህ ይህ መፅሐፍ እኔ ጋ የለም›› ብሎ መልሶ አያውቅም፡፡ በቁጭት ‹‹እኔም ጋር እኮ ነበረ›› ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደሱ ኪስ መግባት የነበረበት ሀብት ወደ ሌላ ባላንጣው መግባቱ ያበግነዋል፡፡ መብገኑ ያስደስተኛል፡፡ በጨዋታ ህግ ገዢ፣ ሻጭና ማብገን ከቻለ መጠነኛ ነጥብ ይቆጠርለታል፡፡
ያው ሴተኛ አዳሪዎች ‹‹ እሷ ላይ ከእኔ የተለየ ምን አይተህ ነው›› እንደሚሉት ነው ነገሩ፡፡ መፅሐፍ ሻጭም እንደ ዝሙት አዳሪ፣ የሚሸጠው መፅሐፍም በሴቶች ላይ የሚገኘውን ብልት ድንገት ተመሳስሎ ወይ የተመሳሰለ መስሎህ ታገኘዋለህ፡፡
ደንበኛዬ ጠባዬን ያውቃል… በቀላሉ ብር እንደማልሰጠው ከብዙ ተሞክሮ ጠንቅቆ አይቷል፡፡ ስለዚህ ጨዋታው ይከራል፡፡
‹‹ባለፈው አስመጣልኝ ያልከኝን ‹‹Holy blood, holy grail›› መፅሐፍ በስንት ልፋት አግኝቼልሀለሁ። እንዴት እንዳለፋችኝ አትጠይቀኝ›› ምናምን ይለኛል።
‹‹መች አስቀምጥልኝ አልኩህ›› ብዬ እሸመጥጠዋለሁኝ
እቺ እንኳን ተራ ማጭበርበር ናት፡፡ እሱ እየሣለ ይገዘታል፤ እኔ እሸመጥጣለሁኝ፡፡
መጨረሻ ላይ ሌላ ከባድ መፅሀፍ ያወጣል - ወይ የሩሶን ወይ የ‹‹MAUPASSANT››ን ሊሆን ይችላል። መፅሐፉ በሁሉም ደረጃ የእኔን ኪስ ገበብር ወደ ውጭ የሚለብጥ ነው፡፡ ከባድ ሚዛን ይዘት ያለው በከባድ ሚዛን ፈላስፋ የተፃፈ መሰረታዊ መፅሐፍ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የትም ወድቆ የሚገኝ አይደለም፡፡ በአጭሩ በገፅ ሉኮች የተጠረዘ ወርቅ ነው፡፡
ግን እኔ ጨዋታ ውስጥ መሆኔን አልዘነጋም፤ በአንዴ አልዝረከረክም፡፡ በአድናቆ የአፌን በር ገርበብ አድርጌ አልከፍትም፡፡ ጨዋታ ውስጥ ነኝ፡፡
‹‹የእነዚህን የሞቱ የፈረንሳይ ፈላስፎች እና የ“Twist” ደራሲያን በቃ አትተውም… ደግሞ ሳልገዛው እቀራለሁ ብለህ ነው!... አዎ እንዲያውም ትዝ አለኝ፡፡ ገዝቼው ነበር … የሆነ ሰው አውሼው ሳይመልስልኝ ቀርቷል፡፡ ዋጋው ለመሆኑ ስንት ነው?››
ልክ ዋጋውን ስጠይቅ እየተሸነፍኩ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ሸምቀቆውን ማጥበቅ ይጀምራል። ‹‹መቶ…ሃምሳ›› እላለሁኝ ‹‹ከሶስት መቶ ፈቅ አልልም›› ይላል፡፡ ‹‹በቃ ተወው እለዋለሁኝ››.. ወጣ እላለሁኝ፡፡… ጠርቶ ያመጣኛል፡፡ ሁለታችንም ህጉን ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ በቶሎ ‹‹በጄ›› ማለት መሸነፍ ነው፡፡ ጨዋታው አስፈላጊ ነው ወይ? ብዬ አንዳንዴ ራሴን በትዝብት እጠይቃለሁኝ፡፡ የቂል ጨዋታ ይሆንብኛል፡፡ ግን መፈክሩ ትዝ ይለኛል፡፡
“መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል”
በመፈክሩ እስማማለሁኝ፡፡ ከተስማማሁኝ ደግሞ ለስምምነቴ ዋጋ መክፈል አለብኝ፡፡ ግን ጀማሪ አይደለሁም፡፡ የመፈክሩን ትርጉም እኔ የምረዳበትና ሌላው ተራ የመፅሐፍ ሸማች የሚመነዝርበት የአረዳድ መንገድ ለየቅል ነው። እኔ መፅሐፉን በቅርፁ ብቻ ሳይሆን በይዘቱም እለካዋለሁኝ፡፡ ለመፅሐፍ ብዙ ብር የሚከፍል ሰው ለከፈለበት ምክኒያቱን ሲጠየቅ “ክብሩን ለመግለፅ” እንደሆነ ደረቱን ነፍቶ ይናገራል። ግን ደረቱን ነፍቶ እየተናገረ ያለው የምርጥ ነገሮችን ዋጋ ስላለማወቁ እና አለማወቁን ደግሞ በገንዘብ ሸፋፍኖ ለማለፍ ስለመሞከሩ ብቻ ነው፡፡
... ከብዙ ክርክር በኋላ መጀመሪያ የተጠራው ዋጋን በሚያሸማቅቅ ያሽቆለቆለ ተመን የፈለኩትን ገዝቼ እንደ አመጣጤ ወደምሄድበት እቀየሳለሁኝ፡፡
የምርጥ ነገሮች ዋጋ በመሰረቱ “ምንም” ነው። እውቀትና የፀሐይ ብርሐን የማንም አይደሉም፡፡ መፅሐፍ ሻጭ መሀል ቤት ተቀምጦ ሊደልልባቸው አይገባም፡፡ ስለማይገባ ግን አይችልም ማለት አይደለም፡፡ የድርድሩ ህግ ያስፈለገው ለዚህ ነው። “መፅሐፍ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” ሙሉ ለመሆን ሲባል ኪስን ያለአግባብ ማጉደል ግን ተገቢ አይደለም፡፡ 

Read 1034 times