Sunday, 19 March 2017 00:00

“አኹንም ብዙ ብርሃን!”

Written by  ከክፍሌ ተክለጽዮን
Rate this item
(4 votes)

 ርእስ፦ የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ­­-­­­ቃላት
(Giyge’s Advanced Supplement to Concise Amharic-English Dictionaries)           
የገጽ ብዛት ፦  xiv መግለጫ የያዙ የፊት ገጾች + 382 ገጾች
አሰናጅ ፦    ግርማ ጌታኹን ይመር
አሳታሚ ፦ ክብሩ ክፍሌ/Kibru Books
ዋጋ፦  ብር 230
የታተመበት ቦታ ፦ ፋር ኢስት፥ አዲስ አባባ
የታተመበት ዓ.ም :- ጥር፣ 2009 ዓ.ም

የጸሓፊ ደዌ ያታሚ መከራ፣
ጠንቅቆ አለማወቅ የፊደልን ሥራ።
እንዳገኙ መጣፍ በድፍረት በመላ፣
የቋንቋ ደረመን የመጽሐፍ ቢስ ገላ።
ንባብ የሚያሳክክ ምስጢር የሚቈምጥ፣
መልክአ ትርጓሜ የሚለዋውጥ።
(ኪዳነወልድ ክፍሌ)
እንደ መነሻ
ስለ አንድ ጽሑፍ የሚሰጥ አስተ፟ያየት ከኹለት ነገር ይመነጫል፤ አንድ፦ ስለቀረበው ጽሑፍ አድናቆትን ለመግለጽ፣ ሌላው፦የቀረበው ጽሑፍ ከሚጠበቀው ደረጃ በታች ከኾነ ሒስ ለመስጠት። የኔው ካንደኛው ይካተታል። እንዲያም ቢኾን ግን ምድር የለቀቀ ውዳሴ አላቀርብም፣ በወደዱት ነገር ላይ እንከንን አይወድዱምና ለእኔ መስለው የታዩኝን እጠቋቍማለኹ።
ከአሥራ ሰባተኛው ምእትያ አንሥቶ እስከ ኻያኛው ማብቂያ ድረስ፣ ቍጥራቸው ትንሽ የማይባል፣ ዋና ዋና የኾኑ፣ ልሳነ-ዋህድና ልሳነ-ክልኤ መዛግብተ-ቃላት ባገራችን ቋንቋዎች ላይ ተዘጋጅተዋል። በግእዝና ዐማርኛ ቋንቋዎች ላይ፣ ባገርና በውጭ ሊቃውንት የተጻፉትን በደፈናው ስናያቸው አሰነዳዳቸው በሦስት ይመደባል፤ አንድ፦ በሀለሐመ የፊደል ተራ የተሰደሩ፣ ለዚኹም የኢዮብ ሉዶልፍ ኹለቱ መዛግብተ-ቃላቱ የግእዙና  ያማርኛው (1661, 1698)፥ የዊልያም ኢዘንበርግ (1841)፥ የአውጕስጦስ ዲልማን (1865)፥ የአንጦንዮስ ዳ’ባዲ (1881)፥ የኢግናጥዮስ ጕይዲ (1901)፥ የዮሴፍ ቤትማን (1929)፥ የተፈራ ወርቅ አርምዴ (1947)፥ የተሰማ ሀብተሚካኤል (1951)፥  የሞገስ ዕቁበጊዮርጊስ (1960)፥ የዎልፍ ሌስላው (1976)፥  የቶማስ ላይፐር ኬንና (1990) የጥቂት ሌሎችም። በትግርኛ ላይ የተዘጋጁት የፍራንሲስኮ ዳ’ባሳኖና (1918)፥  የአባ ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር (1948/49)፥ በትግረ ላይ የተዘጋጀው የኤኖ ሊትማን (1962) ሥራ ይኸንኑ ፈለግ ተከትለዋል። ኹለት፦ በአበገደ የፊደል ተራ የተሰደሩ፣ ለዚኹም የክፍለጊዮርጊስ-ኪዳነወልድና (1948) የደስታ ተክለወልድ (1962) ሥራዎች። ሦስት፦ዎልፍ ሌስላው በሮማይስጥ የፊደል ተራ ድምፀ-ሞክሼ ሆህያቱን በማከታተል ግን እየቅል የሰደረበትና Comparative Dictionary of Ge’ez (1987) ን ያዘጋጀበት ቅደም ተከተል ናቸው። ሊቃውንቱ በተለያየ የፊደል ተራ ያዘጋጁበትን ምክንያት ለማወቅ ምክንያተ ጽሕፈታቸውን በየመጻሕፍቶቻቸው ስለገለጹት ከዚያው ማየት ነው። የግርማም መዝገበ-ቃላት የተዘጋጀው፣ በተለመደው በሀለሐመ ቤት የፊደል ተራ ነው፣ ነገር ግን ይለያል። በነገራችን ላይ፣ ማከያ መዝገበ-ቃላት መጻፍም የተለመደ ነገር ነው፤ ለምሳሌ ለምናውቀው ታላቁ የአውጉስጦስ ዲልማን መዝገበ-ቃላት Sylvian Grébaut በተባለ ፈረንሳዊ የግእዝ ሊቅ የተዘጋጀለት ማከያ አለ (521 ገጾች፥ 1952)። ከመኻላችን ወንድ ጠፍቶማ እንጂ አይዶለም ማከያ፣ ለዲልማን Critical Edition የሚዘጋጅበት ጊዜ ነበር፤ከተዘጋጀ’ኮ አንድ ምእት ተኵል ዐለፈው! ይኸም’ኮ እንደሌላው ኹሉ ወንድ ይጠይቃል።  ይጠብቅ። አንድ ነፍሱ የምትንገበገብ ወንድ የናቱ ልጅ፣ ማን ያውቃል፣ ድንገት ከተፍ ይል ይኾናል። ሌላኛው፣ የኢግናጥዮስ ጕይዲ መዝገበ-ቃላትም ከተጻፈ ከአርባ ዓመት ግድም በኋላ፣ ደቀመዛሙርቱ ፍራንሲስኮ ጋሊናና ኤንሪኮ ቼሩሊ ማከያ ጽፈውለት ነበር። እኒኽ ኹለቱ ማከያዎች የእናት ሥራዎቹ ዐምስትያ ቢኾኑ ነው።
ነገር ግን፣ ይኸ የግርማ ሥራ ማከያ ከኾናቸው ሥራዎች፣ ከአምሳሉ አክሊሉ Amharic-English (1979, ኹለት የተሻሻሉ እትሞች፣ 381 ገጾች፥ 1996፥ 2003) እና ከWolf Leslau Concise Amharic-English/English-Amharic (538 ገጾች 1976) Dictionaries በመጠኑ እምብዛም አይተናነስም። በጊዜያቸው የተሰናዱበት ዓላማ አንደኛው ለኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ከዚያም በላይ ላሉቱ ሲኾን፣ ሌላኛው ደግሞ ኋላ ላይ ተሻሽሎ በታተመበት መልክ ወጣ እንጂ፣ ፊት ሲዘጋጅ ወዳገራችን ይመጡ የነበሩትን የሰላም ጓዶች ዐማርኛን ለማስተማር ተብሎ ነበር። ከነዚህ ሥራዎች የግርማ የሚለየው በብዙ መንገድ ነው፤ አደረጃጀቱም ብቻ አይዶለም፤ ቃላቱ፣ በጥንቃቄ የተመረጡና የተነቀሱ፣ ወዝና ረዴት ያላቸው ቄንጠኛ ቃላት በመኾናቸው ጭምር እንጂ። በዚህ ላይ ዐውዳዊ ነው። ከምጥንና ክት አተረጓጐም ጋር። ሌላው የሚለዩበት፣ እነዚያኛዎቹ ለማንም ማንም ዐማርኛን ኾነ እንግሊዝኛን መማር ለሚሻ ዅሉ መኾን ይችላሉ፤ ይኸ ግን ላላፊ አግዳሚው አይኾንም። የቃላትን ጣምና ምረር ለቀመሰ ነው። ምዑዝና ጥዑም የኾኑ ቃላትን ለሚሻ ለዚያ ሰው። ባይኑም፥ በዦሮውም ቃላትን ለሚያጣጥመው ለዚያ ሰው ናት። እርግጥ፣ እነዚያ የያዙት የቃላት መጠን በጣም ብዙ ነው። እንደገናም፣ ግርማ እንደ ባለቅኔ፣ ለቃላቱ የሚጠበብና የሚጨነቅ፣ ቃላት ሒወት እንዳላቸው ቢጤ ደም እንደሚረጩ ዐይነት፣ የሚጠበብላቸው የሚሳሳላቸው ይመስላል። ያለወጉ፥ ያለሥራቱ እንዳይውሉ። ግርማ ግን ባለቅኔ የማያደርገውን ያደርጋል፤ መልክአ ፊደላቱንም ጭምር ይጠነቅቃል። ለሕግ ይገዛል። እሱ የመዝገበ-ቃል ሰው ነዋ! የፍቅር ሥራ!
ግርማን ከዚህ ሥራው አስቀድሞ ባራት ነገሮቹ ዐውቀዋለኹ፤ መዠመሪያ፣ ፊት ጊዜ ለሥነ-ምርምር ገጽ  በሰጠው ረዥም ቃለ-ምልልስ ሲኾን፣ ከዚህም የተገነዘብኹት ግርማ እጅግ ሥር የሰደደ የቋንቋ ቀናዒነትና ተቆርቋሪነት፥ በተለይም ለቀደሙቱ ሊቃውንቶቻችን ገደብ የሌለው ፍቅር እንዳለው ነው። ከዚሁ ቃለ-ምልልስ ጋር ምናልባት ለውይይት መነሻ ይኾን ዘንድ ብሎ ስለ ድምፀ-ሞክሼ ፊደላትና ድምፀ-ሞክሼ ቃላት ያዘጋጀውን ሥራም አይቼዋለኹ። ኹለተኛ፦ በኢትዮጵያ የጥናት ተቋም ልሳን በኾነው መጽሔት (ቅጽ 30፥  ቍ 2፥ ገገ.27-88፥ 1997) ላይ ስለ ጋፋት ሕዝብ ጥንታዊ ልማዳዊ ሕግ የጻፈውን ረዥም ጽሑፍ፣ ሦስተኛ፦ የጐጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይን አንብቤ፣ እውነትም ግርማ ጥንቅቅ ያለ የቋንቋና የታሪክ ምሁር መኾኑን ተረዳኹ። ድሮ፣ ገና ያኔ፣ በነውጡ ዘመን፣ ጽሑፎች በኅቡዕ በእጅ እየተባዙ በሚሰራጩበት በዚያን የጥድፊያና የሽብር ሰዓት እንኳ፣ ስለሆህያት አገባብ አብዝቶ ይጨነቅ እንደነበር የስሚ ስሚ ሰምቻለኹ። ከዚያም በላይ ትምህርቱንም የተከታተለው በዝነኛው ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ነው። ያ ስንኳ ዋስትና ባያሰጠንም።
አ. ቅጥና ቅርጽ
መጽሐፉ የተከፈፈበት የውጭ ሽፋን ታፍፎ የተሰተረ ብራናን ይመስላል፣ ለመጽሐፉ አንዳች ሞገስ ሰጥቶታል። ባለ ኹለት ዐምድ ኾኖ፣ የተጻፈበት የሆህያት ቅርጸት ልቅም ያለ በመኾኑ ዐይን ይስባል። በተለምዶ መዛግብተ-ቃላት ብዙ ቃላት ዐጭቆ ለመያዝና ቦታን ለመቆጠብ የቅርጸት መጠናቸው ባናነሰ ፊደላት ይጻፋሉ። ይኸ ግን፣ ፊደላቱ መጠናቸው ጐላ-ጐላ ብሎ ዘና ያሉ በመኾኑ፣ የወጣቱንም ኾነ የአዛውንቱን ዐይን አያስጨነቍርም፥ አይበዘብዝም።
በ. ስያሜ
በውጭው ዓለም አንድ መጽሐፍ በደራሲው ስም የሚጠራው፣ ብዙ ጊዜ አካዳሚያዊ ሥራ ኾኖ፣ መዝገበ-ቃላትም ቢኾን ምድቡ ከአካዳሚያዊ ሥራ ነውና፣ ተደጋግሞ ከታተመና በተለይም በየጊዜው በተማሪው ወይ ባንባቢው ዘንድ ከተወደደ፣ ወይ ደራሲው በዕድሜ ሳቢያ ከቤት ከተሰበሰበ በኋላ፣ ወይ ወደ ቸሩ አገር ከኼደ፣ መጽሐፉ ለመዘከሪያው በስሙ ይጠራና በየጊዜው እየታተመ የተለመደውን አገልግሎቱን ይሰጣል። ይኸ በኛ አገር እንግዳ ነገር ነው። ለዚህ የበቃም ሥራ የለንም። እንዳይማል፣ ተሰማ ሀብተሚካኤል ያውም በገዛ ራሳቸው ስም ሳይኾን፣ ብዙ የደከሙበትን አንድያ የበኵር ሥራቸውን፥ መጪውን ግብ፟ሩን በማሰብ ከሣቴ ብርሃን ተሰማ ብለው ሰይመውታል። እሱም ቢኾን እንደሌላው አገር ደጋግሞ የመታተም ዕድል አላጋጠመውም። ለነበ፟ር የሚኾን ሥራ ዅሉ፣ የዘመንን ወዠብ በራሱ ተቋቁሞ ከዘለቀ፣ ያ የሚጓ፟ጓ፟ለት ክብር የኋላ ኋላ መምጣቱ ያለ ነው። የኋላ ልጅ፣ ለሥራውም ለደራሲውም የክብር አክሊል ይጭንለታል። ትሕትና፣ በብዙው የኅብረተሰብ አባላት ዘንድ ያልተጻፈ ውስጣዊ ሕግ ኾኖ በሚያገለግልበት አገር፣ ቢያንስ በኛ ዘመን ትውልድ ግን ራስን እንደመቆለልና ልብን ማግዘፍ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል። ያንን ያደረገው ዕውቀቱ ድግዝግዝ ኾኖ፥ ልቡ የሠባው ዳመና ልርገጥ ባዩ፥ ያገሬ ልጅ ቢኾን አይገርመኝም ነበር። እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠሩ ራሳቸውን አንቱ የሚሉ ያገሬ ልጆች አደባባዩን ሞልተውታል። መጽሐፉ አስቀድሞ ሲታተም ይዞት የነበረውን ስሙን ይዞ ወጥቶ በነበር ይበልጥ ባማረ።
ገ. ምንጮች
መዝገበ-ቃላት የሚያዘጋጅ ሰው፣ የማይታክት የኪዳነወልድ ክፍሌና የደስታ ተክለወልድ ትጋትና ብርታት፥ የማይበርድ ቍርጥ ፍቃድ፥ ከትግዕሥት ጋር ያሹታል። እርግጥ ነው፣ ከተሟሸ ከተፈተነ ዕውቀት፥ የጥበብና የቃላት ፍቅር ጋር። ግርማ ዕድለኛ ኾኖ፣ እንደ ኪዳነወልድ፥ እንደ ደስታ፥ እንደ ኬን ያሉ መዛግብተ-ቃላትና የደለበው ያማርኛ ሥነ-ጽሑፍ አሉለት። ግርማ  ቃላቱን የሰበሰባቸው በቆይታም ብዛት ነው፤ሒሳቡን በጥሬው ብናሰላው ለመዠመሪያው እትም ወደ ዐሥራምስት ዐመት ገደማ ፈጅቶበታል፤ ከአስራዘጠኝ ሰማንያዎቹ መገባደጃ እስከ 2003 ድረስ ማለት ነው።
ነገር ግን ከዚያ አንሥቶ እስካኹንም የቦዘነ አልኾነም። እስካኹኗ እትም ከኻያ ዐምስት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ ደክሟል። አብዛኛዎቹ ቃላት የተወሰኑ መጻሕፍትን በጥንቃቄ፥ በጥልቀት ከማንበብ የሰበሰባቸው ናቸው። በተለይም የአለቃ ተክለየሱስን ኹለት ሥራዎች -ለኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥናት ያቀረበበትንና እሱ ራሱ በአ.አ.ዩ. ያሳተመው ስለ ጐጃም ትውልድ የሚገልጸው-የሰውዬው ሥራዎች ናቸው። እንዳውም በግርድፍ ስሌት ያለ ማጋነን ከኻያ በመቶው ያላነሱቱ የቃላቱ ስብስብ ከነዚህ ሥራዎች ይመስላል። የሳቸው ስም ቢያንስ አንዴ ያልተጠቀሰበት ገጽ እምብዛም ብዙም አይዶለ። በሕዝቡ መኻል አገልግሎት ላይ የነበሩ ቃላትን ዅላ እሳቸው መጻሕፍት ውስጥ በመገኘታቸው ብቻ እንደሳቸው ኾነው ተወስደዋል። የኋላ ልጅ ቃላቱን ወይ አገላለጹን እሳቸው የፈጠሯቸው ነው የሚል ግንዛቤ እንዳይወስድ ያሰጋል። ይኸ አደራረግ አግባብ የሚኾነው ቃሉ፣ እንግዳ፥ ቀበልኛ፥ ጐጥኛ፥ ወንዜኛ፥ የተለየ ሰዋስዋዊ አገባብ ወይ አጠቃቀም ኖሮት ቢኾን ነበር። ወይ ብቸኛ ምንጭ ኾነው በነበር ባልገደደ። ዕጓለ ገብረዮሐንስ፥ ዳኛቸው ወርቁና ዮሐንስ አድማሱ የምናውቃቸውን ቃላት በየራሳቸው መንገድ እንደሚያቃብጧቸው ዐይነት ቢኾን በዚያ በኵል ልክ ይኾን ነበር። እንኳን የጻፉትን ቀርቶ ተክለየሱስ የሚባሉ ሊቅ ከናካቴው መፈጠራቸውን ሳያውቅ፣ ከመኻከላችን፣ ከጐጃም አይዶለም እዚህ ታች አንጨቆረር ተወልዶ ያደገው፣ ቃላቱን ከነፍቺያቸው የሚያውቅ ስንትና ስንት ሰው አለ? የደቀመዝሙር ጥኑ ፍቅር? ዐውዳዊ መኾኑና በዋቢ መደገፉ የመጽሐፉ ዐቢይ መለያም ጌጡም ነው።
ከተዘረዘሩት ዋቢ መጻሕፍት ውስጥ መረጃቸው ምሉእ ያልኾኑ ጥቂት ሥራዎች አሉ፤የጂ.ፒ. ሞስባክና የአምሳሉ አክሊሉ English-Amharic Dictionary መዠመሪያ የታተመችው በ1965 ነበር። የብርሃኑ ዘርይሁን ዋዜማ የአብዮት ዋዜማ የመዠመሪያዋ ቅጽ የወጣችው በ1972 ዓ.ም. ነበር። ከዚያን፣ ቀሪዎቹ ኹለቱ ቅጾች በተከታተሉት ዓመታት ተለጣጥቀው ወጥተዋል።
የዋቢ መጻሕፍቱ ቅደም ተከተል ትክክል ቢኾንም፣ ወጥ አይዶለም፤የደራሲው ስም ከነአባቱና የመጽሐፉ ርእስ የመዠመሪያዎቹ ፊደላት በአኅጽሮተ-ቃል ተወስዶ በእስከ ሰረዝ ተያይዞ ለብዙዎቹ ሲሠራ ለጥቂቶቹ አልሠራም። ለምሳሌ የኪዳነወልድ፥ የደስታ ተክለወልድ፣ የተሰማ ሀብተሚካኤል፥ የገብረሕይወት ባይከዳኝ፥ የጸሓፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ፥ የገሪማ ታፈረ። ስሞቻቸው በአኅጽሮት አለ፤ነገር ግን እንደሌሎቹ፣ ሥራዎቻቸው አልተከተሏቸውም። በደንብ ይታወቃሉ ከማለት ካልኾነ። ሌላው፣ የመጻሕፍቱ አርእስት ኖረው ከስሞቻቸው ጋር ያልተያያዙ ደራሲዎች-የመጽሐፈ መድኀኒትና የሥዕላዊ መዝገበ-ቃላት-አሉ።
እንዲሁም፣ በዋቢዎቹ ዝርዝር ውስጥ የሌሉ ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ አሉ፤ ለምሳሌ፦ገገ 1፥ 114፥ 216 በኹለተኛው ዐምድ ላይ MGZ-M, AW-A, AW-WA የሚሉ አሉ። የኋለኞቹ ኹለቱ ዓለማየሁ ሞገስ፥ ወይዘሮ ዓለሚቱ ለማለት ይመስላል፤ወይስ ሌላ ይኾኑ? ገጽ 287 ከመዠመሪያው ዐምድ MSWM, 114 የሚል አለ፣ ኹለት የማኅተመሥላሴ ሥራዎች ተጠቅሰዋል፤በዚኽ ቦታ ላይ ግን ዝክረ ነገር ለማለት ነው።
ግርማ መዝገበ-ቃላቱን ሲያሰናዳ አብዛኛዎቹን ቃላት ያሰባሰበው ከታተሙና ካልታተሙም ሥራዎችም ጭምር ነው ይላል (ያልታተመ ሥራ ርእስ የለውም?) ቃላቱንም ሲመርጥ የተከተለው የራሱ የኾነ መመዘኛ (ገጽ iii) ሰጥቷል። የታተሙቱን ያማርኛ ጽሑፎች ሥራትና ዙሪያ-ገብ በኾነ መልክ አላደረስኩምም ብሏል፤ነገር ግን ታትመው የብዙ ለየት ያሉ ቃላት ምንጭ ሊኾኑት ሲችሉ ያልተጠቀመባቸው ብዙ የቀደሙ ሥራዎች አሉ፤ለምሳሌ፦የተክለሐዋሪያት ተክለማርያም ትንሽ ስለእርሻ መፈተኛ (1922)፥ የዕጓለ ገብረዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ (1956)፥ የመንግሥቱ ለማ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኀይሉ ወልደታሪክ (1959)፥ የበቀለ ተገኝ መኰንን ኹለት ትርጕሞች፣ የዩልዬስ ቄሣር አሳዛኝ አሟሟት (የሼክስፒየር፥ 1949) እና፥ የምዕራብያውያን የሥልጣኔና የፍልስፍና ታሪክ (የበርትራንድ ረስል፥ 1984)፥ የዳኛቸው ወርቁ ለደረጃ መዳቢዎች አዘጋጅቶት የነበረው የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት፣ ዐማርኛ-እንግሊዝኛ/እንግሊዝኛ-ዐማርኛ (1974) እና የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ  (1977) ከአምሳሉ አክሊሉ ጋር አዘጋጅቶት የነበረው የአማርኛ ፈሊጦች (1979)፥ የተስፋ ስንታየኹ ጫዎታ በየሩሳሌም (1981)…ዋናዎቹ ሲኾኑ ሌሎችም ሙያዊ የኾኑ ጥቂት የኋላ ሥራዎች ነበሩለት።  እሱ ቀረለት፣ ለእኛ ግን ቀረብን።
ደ. ይዘት
ግርማ መደበኛ በኾነው የመዝገበ ቃላት አዘገጃጀት መሠረት፣ ዘሩን ወይ አንቀጹን በመነሻነት ባማርኛ ሰጥቶ-ብዙ ጊዜ ሥርወ-ቃል የሚኾነውን- አነባበቡን በሥራተ-ድምፅ (IPA) አጻጻፍ ጽፎ አቻውን ፍቺ በምጥን እንግሊዝኛ ይሰጣል። ቃሉ ካንድ በላይ ትርጉምም ካለው እንዲሁ። ዘሩ፣ ብዙ ቁጥር ካለውም፥ ሰዋስዋዊ መደቡን፥ በተለያየ መልክም ይጻፍ እንደኾነም፥ ያራዳም፥ ነውርም… ከኾነ ይገልጻል። ከሥርወ-ቃሉ የሚወጡትን ውሉድ ቃላትም፥ ድርብ ቃላቱንም ጨምሮ አነባበባቸውን ሰጥቶ አቻ ፍቺያቸውን፣ ዐልፎ ዐልፎም ቃሉ የፈለሰበትንና ተመሳሳዩን ይሰጣል። አገባቡንም ከሥነ-ጽሑፉ በሚጠቅሳቸው ያሳያል። የግርማ አተረጓጐም ከኬን የሚሻልበትም ቦታ ትንሽ አይዶለም።
የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት ዋና ዓላማው  ለአምሳሉ አክሊሉ Amharic-English እና ለWolf Leslau Concise Amharic-English/English-Amharic ሥራዎች በዋናነት ማሟያ  ይኾን፣ እንዲሁም የቶማስ ላይፐር ኬን Amharic-English መዝገበ-ቃላት (2vols.፥  2351 ገጾች፥ 1990) ከ1990 ዎቹ ወዲኽ ወደ’ለት በ’ለት አገልግሎት የገቡትን ቃላት ስለማያጠቃልል ያንን ጉድለት ለማሟላት ነው። በተጨማሪም በመዛግብተ-ቃላቱ ውስጥ ኖረው፣ በሚገባ ያልተስተናገዱትን ቃላት አካቶ ተገቢውን ፍቺ ሰጥቷቸዋል። እርግጥ ነው፣ ብዙ ዐዳዲስ ቃላት ተወልደዋል፥ ተውሰናል፥ አዳቅለናል፥ እንዳሉም ወስደናል። እነዛን ማካተት ጊዜው ይጠይቃል። ባጠቃላይ፣ እጅግ በጣም ብርቅ የኾኑ ዐልፎ ዐልፎ ካልኾነ ያውም የኛን የቀደሙ ሥራዎች ባላነበቡቱ ዘንድ የማይታወቁ ቃላትን(መናዎ፥ ራዎት፥ እድብ፥ ውጁ ጦር፥ የቦ…)፥ አንዳንዶችም ከዘወትር አገልግሎት ውጪ የኾኑቱን (ለፎ፥ ሥንቆ፥ ናጀለ፥ ወገት፥ የርቦራ…) ፈሊጣዊ የኾኑ አገላለጾችን (ልክ ልኩን ነገረው፥ ሌባው ከነሰለባው፥ ሰማይ ግንባርኽን እስቲመታኽ ሽሽ፥ አገርሽቶት ይሞታል አህያ ተማልሎ ጅብ አወረደ…)፥ በዘፈኖቻችን ውስጥ ያሉ ቀልብ የሚስቡ አዝማች ቃላትን (ሌቦ ነይ፥ ኧረ መላ፥ አንገቱ በምን ሰላ፥ ተው ስማኝ አገሬ፥ በማተቧ ልዳኝ…)፥ የግጥም ወይ የቅኔ አንጓዎችን (የማነች ቀዘባ ያች ዐይነ ሌባ፥ አመሳሶ እሚባል በሞት ቤት የት አለ፥ የልጅ አመሳሶ የለውም ለናት፥ የያዘኝ አባዜ ገለል እስኪልልኝ…)የዘመኑ ያራዳ ቃሎችን(ነፍሱ፥ ነፍሴ፥ ነፍስ ነች፥ ደቡር፥ ጀነጀነ፥ አልማዝ ባለጭራ…)ዐዳዲስ ስያሜ ወይ ፍቺ የተሰጣቸው ቃላትን (ሀገር-በቀል፥ ምቹጌ፥ ምንደራ፥ ብዝኀ-ሕይወት፥ ዐረቦን…)፥ ምንጫቸው ዐረቢ ኾኖ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የተለመዱ ቃላትን (ሐድራ፥ ሙዐዚን፥ አዛን፥ ዑለማ፥ ኒካን አሰረ…)፥ ሥነ-ምድራዊ፥ ባሕራሳባዊ፥ ሕክምና-ጤና ነክ ሃይማኖታዊ ትውፊታዊ ቃላት፥ እንዲሁም፣ የአዕናቁና የአእባን ስያሜ በተለመደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቺዎቻቸው ተካተዋል። በተለይ-በተለይ በየትኛውም በታተሙ ልሳነ-ክልኤ መዛግብተ-ቃላት በኬን ካልኾነ በስተቀር፣ የማይገኙ፣ የአዕዋፋት፥ የዕፅዋት፥ የእንስሳት፥ የአራዊት ስም ከነሳይንሳዊ ስሞቻቸው ጭምር ተካተዋል። ባሳብ ደረጃም እንኳን ቢኾን፣ ይኸንን እንደ ክፍለጊዮርጊስ፥ ኪዳነወልድና ደስታ ተክለወልድ ጕዳዬ ብሎ አንድም ያሰበበት አልነበረም። ክፍለጊዮርጊስ የመዠመሪያውን ዝግጅት አጠናቀው ከምፅዋ ወደ ከረን ዐብረው የላኩት ጦማር ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ፦የዚህ ግስ ሥራው ገና አልተጨረሰም፤ስምና ግብር፥ ግዕዘ ብሔር ቀርቶታል፤ጊዜ ቢገኝ ኋላ ሲታተም ይጨረሳል። …(ኪወክ ገጽ 7) እንዲሁም ኪዳነወልድ የሀገርና  የስም ተራ መሰብሰብና መተርጐም ሲያስቡ…(ኪወክ፣ የፊት ገጽ) ደስታም አንባቢ ሆይ ያማርኛ ቋንቋ ይህ ብቻ እንዳይመስልኽ። ከዚህ የቀረውን የእንስሳትንና የአራዊትን የዓሣትን የዕፅዋትን ያገርንና የሰውን ስም አምልተን አስፍተን ከነትርጓሜው አውጥተን ለማሳየት ሐሳብ አለን። ለዚሁም ያምላካችን ፈቃዱ ይኹን፤አሜን። (ደተወ ገጽ 7) ያም መልካም ሐሳብ ሳይሳካ ቀርቷል። ግርማ ዘመንና ቦታ ያገዘውን ያኽል አካትቷል። በኛ አገር ሥራት ባለው መንገድ ያሉትን ዕፅዋትና እንሰሳት በቅጡ አካ፟ቶ በሳይንሳዊ መንገድ ያሰናዳ የለም፤በሙያው የተሰለፉትም ቢኾኑ እንኳ። እርግጥ እንዳይካድ፣ ጥቂት የሙከራ ጥንቅሮች አሉ። ይኸ በራሱ እንግዲህ አንዱ ገዳቢ ነው።
        
ጀ. አደረጃጀት፣ የሆህያት አሰዳደር
የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት የተከተለው አሰዳደር ሀ-ሐ-ኀ-ኈ ለ መ ሠ-ሰ ረ… ቀ-ቈ … አ-ዐ ከ-ኰ … ገ-ጐ … ጸፀ … ቤት ተራን ነው። ከፊተኞቹ አሰናጂ ዎች መኻል በተለይ ይኸንን መንገድ የፈለመው ኢግናጥዮስ ጕይዲ በVocabulario Amarico-Italiano (xiv + 918 cols. 1901, 1935, 1953) መጽሐፉ ሲኾን፣ ኋላም ፍራንሲስኮ ጋሊናና ኤንሪኮ ቼሩሊ በማከያው ሥራ ይኸንኑ አካኼድ አጽንተውታል። ተከትሎም፣ ዎልፍ ሌስላውና ቶማስ ኬን ተከትለውታል። ሀሐኀኈ፥ ሠሰ፥ አዐ፥ ጸፀ እንዳንድ ቤት ተሰድረዋል።
ሌሎች በቀደዱት መንገድ ግርማ ዘልቆበታል። ግርማን ካተጉት አንዱ ሌስሎው፣ የጕይዲን ፈለግ ሲከተል አምሳሉ ግን በነባሩ ሥራት ዘልቋል-ድምፀ-ሞክሼ ፊደላቱን ባንድነት አልጣፋቸውም፥ ባንድነት አልገሰሳቸውም እየብቻቸው በየጠባያቸው እንጂ። ግርማ ከሌስላው (2003? የትኛው ሥራ?) የቀሰመው አለ፣ ዘሩን ወይ ሥር ወ-ቃልንና አንቀጹን ወይ ውልድ ቃል አመራረጥንና አደረራደር፥ ያነባበብን አጻጻፍ። ግርማ በነጕይዲ በነሌስላው መንገድ በሀለሐመ ቤት ፊደላቱን ይሰድርም እንጂ ሥራተ-ጽሕፈቱ የተከተለው የወዲያኛውን ቤት  ነው። ግርማ የመረጠውን መንገድ ሲያጸና የሰጠው ምክንያት ባጭሩ የተለመደና፥ ለተጠቃሚ ቀላልና የሚመች ስለሚኾን ነው ይላል። የያንዳንዷን የፊደል ቅንጣት አጠቃቀምና (ጨ ስትቀር) ሥራተ-አጻጻፍ የተከተለው ኪዳነወልድና ደስታ ተክለወልድን ነው፤ ለየት ያለበትም መንገድ ቢኖር።
‘በካህናትና በሀገረሰብ ቋንቋ’ መኾኑ ቀርቶ፣ በንግግርና በድምፅ፥ መመሥረቱ ቀርቶ ሥርወ-ቃላቱን ብቻ መሠረት ያደረገ ይኹን ነው። እንግዴህ፣ የግርማ ትልቁ ብያኔም ይኸው ነው።
የዚኅ አሰዳደር ሌላ ዐይነተኛ ጠቀሜታው በድምፀ-ሞክሼ ሆህያቱና ድምፀ-ሞክሼ ቃላት ተመሳሳይነት ሳቢያ የሚታየውን የትክክለኛ አጠቃቀም ጕድለት ለማስወገድ ይረዳል የሚል ነው። በተለይ፣ ድምፀ-ሞክሼ የኾኑትን ቃላት ካንድ ላይ መሰደሩ የሥርው-ቃላቸውን ልዩነት መሠረት አድርጐ የተጠነቀቀ ወጥ ሥራተ-ጽሕፈት እንዲኖረን ያስችላል ነው። መሠረት  ያለው የቀና ትርጉምም ይሰጠናል ነው። ላብነት ሦስት ቃላትን እንውሰድ፣ ሣለ፥ ሳለ፥ ሳለ። የሦስቱም ሥርወ-ቃል ልዩ ልዩ ነው፣ እንደየቅደም ተከተላቸው ሠዐለ፥ ሰሐለ፥ ሰዐለ ነው፤ ትርጕማቸውም እንዲሁ። ሥዕል ሣለ፣ ቢላውን ሳለ፣ ሳል ሳለ። ይኸ ዐይነት አደራደር አጻጻፍን፥ አገባብንና ትርጕምን እንድንጠነቅቅ ያደርገናል ነው። የፊደላቱና የቃላቱ ድምፅና አጻጻፍ በሥራት ከተጠነቀቀ ወዲያዉም ትርጉሙ ፍቺው ከፊደሉ ይታወቃል ነው። ከኹሉ በላይ ቅጥ ያጣው አጻጻፋችን ሥራት ይኖረዋል ነው ጭንቁ። ስለ ቋንቋው ግእዝ ሲያወሩ ግዕዝ ብለው የሚጽፉ ናቸው’ኮ ሰዎቹ።
ሌላው የግርማ ሥራ ልዩነት፣ መነሻ ቃሉን ወይ ቀዳማይ አንቀጹን በትክክለኛው ሆህያት ከሰጠ በኋላያው ቃል በድምፀ-ሞክሼ ሆህያቱ ሳቢያ ወይም ሌላ፣ ትክክልም ኾኖ ባማራጭ ሊጻፍ የሚችልበትን፣ አልያም ስሕተትም ኾኖ በተለምዶ የሚጻፍበትንና የሚነበብበትን የሚነገርበትንም በቅንፍ ውስጥ ይሰጣል። ላብነቱ፦ገጽ 294 በኹለተኛው ዐምድ ድኻ የሚል ቃል አለ- ይኸ ትክክለኛው አጻጻፍ ነው፣ በቅንፍ ደግሞ በዘልማድ፣ ነገር ግን በስሕተት፣ የሚጻፍበትን የሚነገርበትን መልክ ድሃ፥ ድኃ፥ ደኻ ይሰጣል። ገጽ 236 ላይ ውሃ በመነሻ ቃልነት ተሰጥቶ እንደዚህም ሊጻፍ ይችላል ነው መሰለኝ እንዳማራጭ ውኃ፥ ውሀ በቅንፍ ተሰጥተዋል። እነዚህ ግን፣ የኋለኞቹ በስሕተት የሚጻፉበት መልክ ናቸው። መቼስ ስለ ፊደል ጥንቀቃ ከኪዳነወልድ ክፍሌና ከደስታ ተክለወልድ ውጭ የምንጠራው ሌላ ባለሥ፟ልጣን የለንም።
መቼም መረሳት የሌለበት፣ በብዙው እጅ ዐማርኛ የግእዝ ልጅ ነው፤ያባት የኾነ ዅሉ ለልጅ መውረዱ ያለ ነውና ብዙዎቹ የግእዝ ሕግጋት ዐማርኛም ላይ ይጸናሉ። የሚወራረሱ ፊደላት አሉ (ለምሳሌ፦ጕርዔያውኑ  ሀሌታው ‘ሀ’ በአልፋው ‘አ’፥ ሐመሩ ሐ በዐይኑ ‘ዐ’ ይተካል…። )በዚህም ኾነ በሌሎች ሕግጋት የተነሣ፣ የሚጐርዱ፥ የሚቀየሩ፥ የሚዋጡ ፊደላት አሉ። እንዲህ ያሉቱ እንደስሕተት ሊቆጠሩ ወይ ሊወሰዱ አይገባም። ክዑበ-ድምፅ የኾኑቱ ሕጹጻን ፊደላትም (በተለይ ካዕብና ሳብዕ የኾኑቱ) አጻጻፋችንን ያሳስታሉ፣ ቈጠረ በማለት ፈንታ ቆጠረ ብለን እንድንጽፍ። በተለይ የሕጹጻን ፊደላትን ጠባይ ጠንቅቀን ባለማወቃችን ሳቢያ ስንጽፍም ስናነብም የምንሳሳተውን በየቦታው አግዝፎ አሳይቷል። ይኸ-ይኸ ኹሉ የቋንቋችንን ሥራት በቅጡ ካለማወቃችን ነው።
ያም ኾነ ይኽ፣ ይኸ የግርማ አካኼድ እንደሌላ ዐይነት የመዝገበ-ቃላት ያደረጃጀት ሥራት ሊወሰድ ይችላል። ቅድምናን ለሥርወ-ቃል እንደሚሰጥ። እንዲህም ቢባል ያንንም አላነገዋለለውም። የሚዘወተሩትን ቃላትም አካቷቸዋል።
ምናልባትም በቋንቋው ዘርፍ በተለይም በልሳነ-ክልኤ መዝገበ-ቃላት አዘገጃጀት ከአምሳሉ ተከትሎ በዚች ምድር ቀና ያለ ልጅ ነው - በምሁራዊ ቃናው።
ግርማ ሥርወ-ቃልን መሠረት አድርጐ በአበገደ ቤት አስኪዶትስ ቢኾን?!
ሀ. የቃላት ብዛት
ይኸ የግርማ መዝገበ-ቃላት ቀደም ብሎ  በ2003 ጀርመን አገር ታትሟል። የዛኔ የገጹ ብዛት  398 ነበር። የዚያ እትም የቃላት ብዛት ወደ 6000 ቃላትና ወደ 2700 ሐረጐች ነበሩት። ይኸኛው እትም፣ በገጽ ብዛት ባይበልጥም የቀደመው እትም የነበረውን ስሕተት ነቅሶ፥ ተጨማሪ ቃላትን በመጨመሩ ያካተተው የቃላት ብዛት በጨዋ ግምት ከ8000 አያንስም፤ ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ሐረጋቱ ደግሞ እስከ ሦስት ሺ ሊደርሱ ይችላሉ።
ወ. ጥቃቅን እንከኖቿ
ለከርሞው፣ ሦስተኛ እትም ስትኼድ፣ ሌሎቹንም እንከኖቿን ነቅሳ፣ ሽፋኗ ላይ፣ ከጐን የተጻፈው ስሟ የጣለው ጥላ እንዳይኖር የፊደላቱ መጠን ተቀንሶ ቢጻፍ፥ የደራሲው ስም ቢታከልና ቦታው ከበቃም ያሳታሚው ስም ቢገባ መልካም ይኾናል።
ግድፈት
አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላት የፊደላት ግድፈት ዐልፎ ዐልፎ ይታያል፣ ገጽ 4 ላይ sword ማለት ሲገባ sward ተብሏል፣ ይኸን የመሳሰሉ በጣም ጥቂት ግድፈቶች ይታያሉ።
ገጽ 43 መገን ላድናቈትም ይኾናል፣ መገን  የፊቷ ውበት!
ገ.225 ላይ ኮሾ ሲጋራ ትምባሆው በስስ ወረቀት ተጠቅልሎ ይማግ የነበረ ሲጋራ። የሚጠቀለለው በበቈሎ ገለባ ከኾነ ደግሞ ቈረንዲ። ገ.243 ላይ ውሃ ወራጅ፣ ውሃ ለመቅዳት ገምቦዋን ይዛ ወደ ወንዝ የምትወርደዋ ሴትም። ገገ.305/306 ላይ እንግሊላ፥ ገ.308 ላይ ጋመረች፣ ገ.325 ላይ ግዕዛን፥ ገ.336 ላይ ጥሙሮ፥ ገ.345 ላይ ጥንውት ሊታከሉ ይችሉ ነበር።
ስሕተት
ያማርኛ-እንግሊዝኛ ትርጕማቸው የተሳሳተ ጥቂት ቃላት አሉ፤ለምሳሌ፦ክብረሰማይ ወይ ሕብረሰማይ ገገ.4 ና 226 ላይ iodine ተብሎ ተፈትቷል፣ vitriol blue (CuSO4) ኾኖ ሳለ።
 ገጽ 11 ለምጽ albinism በሚል ቃል ተፈትቷል፣  ትክክለኛው አቻ ቃል ግን vitiligo ኾኖ ሳለ። ላሽ (ገጽ 11) የሚለው ቃል Tinea capitis ተብሎ ተፈቷል።  አንዱ ምክንያቱ ሊኾን ይችላል እንጂ ግን አግባብ ያለው ፍቺው አይዶለም፣ አቻ ቃሉ alopecia ነው።
ገጽ 29 መስቴ፥ ገጽ 39 ማዞሪያ ኹለቱም  እንጀራ ማስፊያ ናቸው።
ገጽ 42  ማጅራት ገትር በተለዋጭ መንጋጋ ቈልፍ ተብሎ ላይ የእንግሊዝኛው እኵያ ቃል ደግሞ  meningitis ተብሎ ተፈቷል፣ ኹለቱም የተለያዩ በሽታዎች ናቸው። ትክክለኛው ቃል፣ ለማጅራት ገትር meningitis ሲኾን ለመንጋጋ ቈልፍ ደግሞ tetanus  ነው።
ገጽ 92 ቈላ ከሚለው ሥርወ-ቃል አንዱ ጭፍራው የቈላ ቍስል የሚለው በሌላ ያማርኛ ቃል ጫዌ የሚባለው ሲኾን፣ የእንግሊዝኛውም አቻ ቃል  yaws ነው።
ገጽ 196 አንከሊስ ኵፍኝ ማለት ነው።
ገጽ 207 ኹለተኛው ዐምድ ላይ ዐደር በሚለው ነባር ሥር ወታደር ስለማለት ወጥቶ-ዐደር ወይስ ዋትቶ-ዐደር? (ደተወ ገጽ 474)
ገጽ 247 የወተት አንዠት፣ ባጠቃላይ ትንሹን አንዠት እንጂ rectum ን አይዶለም፤ይኸ፣ ደንዳኔ ማለ ት ነው።
ገጽ 297 በምንም ዐይነት ድግጣና ዶቅማ ተመሳሳይ ኾነው ዐያውቁም።
Wormwood (Artemisia afra) ን ግርማ ኹለት ቦታ ገገ.183ና 356 ላይ አሪቲ፥ ሌላኛው’ጋ ጭቍኝ ብሎ ተርጕሞታል። ብዙ ዐይነት ዝርያዎች ያሉት ሲኾን እነዚህ ኹለቱም ኀይለኛ ሽታ ያላቸው የተለያዩ ተክል ናቸው። ምናልባት፣ ለዚህ ቃል ሊኾነው የሚችለው ፍቺ ኪዳነወልድ (ገጽ 685) እና ዲልማን (ዐምድ 1016)  ዕጕት ወይ ዕጉትሣር ወይ ዕጕሥታር ያሉት ይኾን?
ሰዋስው፣ ማጥበቅና ማላላት
ግርማ ሲነበቡ የሚጠብቁትን ቃላት ያሳየው እንደተለመደው፣ በእንግሊዝኛው አነባባቸውን ሆህያቱን በመደበል ነው። እርግጥ ነው ግርማ፣ የሚጠብቍ ተነባቢዎችንና ረዥም ድምፅ ያላቸው ተናባቢዎች ላይ ይኸን ያልተለመደ (:) ምልክት አኑሯል፣ ልማዳቸው ወጣ ያሉ ያማርኛ ቃሎችን-በተለይ ሳድስ ፊደላት ያላቸውን-ሥርው-ቃሉንና እንደምን እንደሚነበቡ ለመጠቈም።  
    በዚህ ዘመን የተሠሩ የማስሊያ ሥራቶች ለማላላትም ለማጥበቅም የሚያገለግሉ ምልክቶች አሉዋቸው (ለምሳሌ፣ ዋዜማ)። ከእነዚያ አንዱን ተጠቅሞ ቢኾን ከዚህ ችግር ይላቀቅ ነበር። ይኸ የሚጠቅመው ዐማርኛን መማር ለሚሹቱ የውጭ ሰዎች ነው። ለዅሉም እንዲጠቅም ግን ማድረግ ይቻላል።
    ሌላው ነገር፣ ብዙ ቦታ ቃሎች በሰዋስዋዊ ምድባቸው ስም ይኹኑ ቅጽል፥ ግስ ይኹኑ ተውሳከ ግስ አልተሰጠም። ዘሩ ወይ ቀዳማይ አንቀጹ ወይ ውልዱ ቃል፣ ሊኾን የሚችለው ምድብ የታወቀ ነው ከሚል ከኾነም ለኹሉም የቀና አይኾንም።
የቦታዎች አቀማመጥን አገላለጽ
የሚታወቁትን ትላልቆቹን ከተሞችና ቦታዎች እንኳ ብንተወው፣ ለትናንሾቹ ትክክለኛ ይኾን የነበረው ሥነ-ምድራዊ አገላለጽን የተከተለ ሉላዊ ማገሮችን  (ኬክሮስና ኬንትሮስን) ቢኾን የተሻለ ይኾን ነበር። ዕድሜ ለGoogle Earth! ኹሌ ፖለቲካዊ ለውጥ የአካባቢዎችን አከላለል ሲቀይር ታይቷልና። እውን የድሬዳዋ ኤረር በሶማልያ የአስተዳደር ክልል ሥር ነበረችን?
ማጠቃለያ
አእምሮም ጭምር ቅኝ በተያዘበት በዚህ ዘመን እንደ ግርማ ዐይነት ጥንቍቅ ምሁር ማግኘት አዳጋች ነው። በባዕድ አገር እየተኖረ አስችሎት እንዲህ ዐይነት ጥንቅቅ ያለና የተጨረሰ ሥራ ማዬት ተስፋችንን ያለመልመዋል። ሰው አለን ለካ እንድንል። ለ’እነምናለበት ለእነኹሉ ቀኙ’ የግርማ ድካም በከንቱ ነው። የግርማ ሥራ ጠቀሜታ ከ-እስከ የሚባል አይዶለም። ያማርኛን ጣዕም ጠንቅቆ ማወቅ ለሚሻ ሰው ኹሉ ናት። በተለይም፣ ትክክለኛ ወዝና ቃና ያላቸውን ቃላት በጥንቅቅና ለመጠቀም ለሚተጋ የሥነ-ጽሑፍ  ሰው ታላቅ አጋር ናት። ግርማ ከግእዝ ፊደላት ሌላ ታላቅ ዐማርኛ-ባማርኛ የኾነ መዝገበ-ቃላት ማርገዙን ወፍ ነግራናለችና የእርግዝናው ዘመን ሳንክየለሽ ኾኖለት መወለጃው ደርሶ የምጡ ጊዜ ያጥር ዘንድ እኛንም አድርሶን፣ ማርያም! ማርያም! ማርያም! እንል  ዘንድ ያብቃን! ጭራሹን ያሳምርለት! ቢስ አይይብን! ብርሃን!ብርሃን!አኹንም ብዙ ብርሃን!
ሌላው ደስ የሚለው ነገር፣ የዚህን እትም መታሰቢያነቱን በዚያን ዘመን ለወደቁት የሰናድር ሰፈርና ለኳስ ሜዳ ልጆች ማድረጉ ነው።
በስተመጨረሻም፣ በዋናነት የመሸታ መጻሕፍት በሚሸጡበት አገርና ፍሬ ሥራዎች፥ ቍም መጻሕፍት እስከዚህም በማይሸጡበት አገር፥ ገበያውም በማያስተማምንበት ጊዜ፥ ትላልቅ ሥራዎች የእንዲሠሩ፥ የእንዲተረጐሙ ፍቅሩ አስክሮት በድፍረት እንዲታተም የወሰነውን ክብሩ ክፍሌን ልናመሰግነው ይገባል። እንደሱ ዐይነት ደፋሮች ባይኖሩን እንዲህ ዐይነት ሥራዎችን አግኝተን ልንጠቀምባቸው ባልተቻለንም ነበር።
ሌሎቻችን ደግሞ ሌላው ሌላው ቢቀርብንና ባንችል ባለሙያ ያሰናዳውን የዕውቀት ድግስ ለመፋተት ለመቋደስ ስለምን አንተጋም? ስለምንስ አንጣደፍም?! አያ ኒቼ እንዲህ ብሏል፦If you can’t be one of the saints of knowledge, then I pray you be one of its warriors.

Read 3081 times