Print this page
Sunday, 19 March 2017 00:00

ሀብትን ከብክነት መታደግና በ”ጣይቱ” የተጀመረው አዲስ አሰራር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

  ”ምግብን በግራም ገዝቶ መብላት ነውር የለውም”

           የአገር ሀብትን ከብክነት መቆጠብ ከቤት ጀምሮ እስከ ትልልቅ ተቋማት መዝለቅና ባህል መሆን አለበት በሚል ሀሳብ የባላገሩ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ አየለ (ባላገሩ) ከጣይቱ ሆቴል ባለቤት ጋር በመመካከር ከሰሞኑ አዲስ ንቅናቄ ጀምረዋል፡፡ ሰዎች በቤታቸውም ሆነ በውጭ ማንኛውንም ሀብት በመቆጠብ
አገርን ከውድቀት መታደግ አለባቸው በሚል የተጀመረው ንቅናቄ፤ሰዎች ምግብ በግራም እንዲበሉና ለተጠቀሙት ብቻ እንዲከፍሉ የሚያስችል “በልኬ ምግብ ቤት”ን በጣይቱ ሆቴል አስተዋውቋል፡፡ ይህ አሰራር ከሆቴል ቢዝነስ አንፃር፣
ከተመጋቢዎች ፍላጎትና መብት አኳያ እንዴት ይታያል? ሰው ገንዘቡን እስከከፈለ
ድረስ የፈለገውን ያህል የመመገብ ወይም መብራትም ይሁን ውሃ የመጠቀምን መብት ማን ሊጋፋው ይችላል? በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ሀሳቡን ካመነጩት ከአቶ ተሾመ አየለ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡

      የአገርን ሀብት ከብክነት ለማዳን በሚል፣በጣይቱ ሆቴል ስለጀመራችሁት አሰራር ቢያብራሩልኝ?
እኔ እንደ ባለሀገሩ ቱርስም ሆነ ጣይቱ ሆቴል ያሰብነውና መተግበር የጀመርነው የአገርን ሀብት ከብክነት የሚታደግ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሀሳቡ ተዓምርና የማይታወቅ ነገር ነው ባይባልም በቸልተኝነትና ገንዘብ ስላለን ብቻ ብዙ የአገር ሀብት ለብክነት እየዳረግን ነው፡፡ ስለዚህም ጣይቱ ሆቴል በአገራችን የመጀመሪያው ሆቴል እንደመሆኑ፣ ከቅርባችን ተነስተን ሀሳቡን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረናል፡፡ አንድ ሰው መብላት የሚችለውንና የሚፈልገውን በመመገብ፣ በተመገበው ልክ መክፈልና ምግብን ገበታ ላይ አስተርፎ የኔ ቢጤ (ደሀ) ይበላዋል የሚባለው ነገር መቅረት አለበት፡፡ አንድ ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ የማይበላውን አቅርቦ ከገበታ ላይ ስንትና ስንት ምግብ ይደፋል፡፡ ይሄ መቆም አለበት፡፡ ውሃን ብንወስድ አንድ ጊዜ ገላን ለመታጠብ ከ15-20 ሊትር ውሃ ይባክናል፡፡ ሌሊት ላይ ዞር ዞር ብለሽ ከተማዋን ብትጎበኚ፣ አንድ ህንፃ ሙሉ (በየክፍሉ) መብራት ያለ ስራ ሲበራ ያድራል። ለምን? ያ የህንፃ ባለቤት የመብራት ሂሳብ ሲመጣ ይከፍላል ግን ሲያባክን የሚያድረው መብራት ሌሎችን ብርሀን ያሳጣል፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ስላለ ብቻ የሚባክን የአገር ሀብት ይቁም ለማለት ነው፡፡
በጣይቱ ሆቴል ስለጀመራችሁት አዲስ አሰራር በዝርዝር ያብራሩልኝ?
ቀደም ብዬ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ ጣይቱ ሆቴል እንደ ቀደምትነቱ ይሄንን ተግባር ለሌሎች ማስተማር አለብን በሚል ምግብን በግራም በማቅረብ ብክነትን መከላከል ጀምረናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በአማካይ ከ600 -650 ግራም ምግብ ይበላል እንበል፡፡ ይህ ሰው ከቀረበው ቡፌ ላይ ከሚፈልገው አይነት በሚበቃው መጠን በማንሳት ተመግቦ፣ በተመገበው ልክ ከፍሎ ይወጣል፡፡ ይሄ አንደኛ እንደ ግለሰብ ኪስን አይጎዳም፣ ሁለተኛ ለጤንነትም ቢሆን ሰውነታችን በሚያስፈልገው መጠን መመገብ ውጤታማና ጤነኛ ያደርጋል። ሶስተኛ በአገር ደረጃም ስንት የተራበ እያለ ያለአግባብ ምግብን ማባከን አግባብ አይደለም። ውሃን በሚመለከት ለምሳሌ ሻወር ቤት ገብተን እየታጠብን ቢሆን ሳሙና ሰውነታችንን እስክናሽ ውሃውን አንዘጋውም፡፡ ለምን? በቃ ግድ የለንም። ሳሎን ቁጭ ብለን ቴሌቪዥን እያየን ወይም እየተጨዋወትን የመኝታ ቤቱ፣ የማዕድ ቤቱ፣ የሽንት ቤቱና ሌሎችም ክፍሎች መብራት ይበራል፡፡ ይሄ የአገር ሀብት ብክነት አይመስለንም፡፡ ይሄ መቆም አለበት። ለምን? መብራት የማይደርሰው ወገን አለን። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ለማለማመድ በቅርባችን ያለው ምግብ ቤት ስለሆነ፣ ከጣይቱ ሆቴል ባለቤት ከአቶ ፍፁም ጋር በስፋት ተነጋግረን፤ “በልኬ ምግብ ቤት”ን እዚሁ ጣይቱ ስራ አስጀምረናል፡፡ ብዙ ሰው ወዶ ተቀብሎታል፡፡
ይሄ ከሆቴል ቢዝነስና ከደንበኞች ፍላጎት አንፃር እንዴት ይታያል? ሰው ገንዘቡን እስከከፈለ ድረስ ያሻውን ማግኘት የለበትም? የሰውን መብትና ፍላጎት መጋፋት አይሆንም?
ሆቴሉም ሆነ ተመጋቢው ይህን እንደ ስህተት ቆጥሮ መታረም አለበት እያልን ነው፡፡ ጣይቱ በዚህ በኩል ቢዝነሴ ላይ አደጋ ያመጣል ሳይል ተግባራዊ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ እንደ ቀደምትነቱ ይህን ማስተማር ጀምሯል፡፡ ሰውም ምግብ አይን አዋጅ ሊሆንበት አይገባም፡፡ ለጤናውም ለኪሱም ተስማሚ የሆነ ምግብ ነው መመገብ ያለበት፡፡ ሁለቱንም ወገን ማሳመን ቀላል ባይሆንም ጥረቱ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላውም ሆቴል ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ በሌላ በኩል አንድ ቢሮ ለፅሁፍ ወረቀት የሚጠቀም ከሆነ ፊት ለፊቱን ብቻ ሳይሆን ጀርባውንም መጠቀምና አዲሱን ከማባከን መቆጠብ አለበት፡፡
ግን እኮ ከየሆቴሉ የሚተርፉ ምግቦችን ችግረኞች ይመገቡታል …
በጣም ጥሩ! እኔ ብዙ ጊዜዬን ከጎዳና ልጆች ጋር አሳልፋለሁ፡፡ ከሚመገቡት ትርፍራፊና አንዳንድ መጠጥ ጋር በተያያዘ  ለብዙ ችግር ሲጋለጡ አያለሁ። በዚህ ላይ በሽታ ለመቋቋም የሚሆን አቅም የላቸውም፡፡ አንድ ሰው በልቶ ሲጨርስ እጁንና አፉን የጠረገበትን ሶፍት፣ ስቴክኒና መሰል ቆሻሻ ነገር የተረፈው ምግብ ላይ ይቀላቅለዋል። ያ ተጠራቅሞ ነው እነዚህ ሚስኪኖች ጋር የሚደርሰው። ይሄስ ነገር አግባብ ነው? ሰው ቆም ብሎ ቢያስብ፣ እነዚህ ልጆች ገንዘብ ስለሌላቸው ብቻ እንጂ ከሌላው ሰው በምን ያንሳሉ? ሰብአዊ ፍጡር አይደሉምን? ለምን በልካችን በልተን ለእነሱ ያልተረፈ አንሰጣቸውም፡፡ ተለብሶ ተለብሶ የነተበ ልብስ (ውራጅ) ከምንሰጣቸው እኛ የሚበቃንን ያህል ልብስ ብቻ ገዝተን፣ ለእነዚህ ልጆች ለምን አዲስ አንገዛላቸውም? ሲጀመር ትራፊም ሆነ ልባሽ ልብስ ለእነዚህ ልጆች መስጠት ኢ-ሞራላዊ ስራ ነው፡፡ ከሚተርፈን ቆጥበን፣ ከምናባክነው አስቀርተን እናብላቸው እናልብሳቸው፤ካሰብንበት እንችላለን፡፡ ዛሬ በቸልታ የምናልፋቸው ነገሮች ዋጋ እያስከፈሉን ነው፡፡ ነዳጅ የምንቀዳው የምንፈልገውን ያህል፣ የምንከፍለውም በቀዳነው ልክ ነው፡፡ ትንሽ ነዳጅ ጠብ ሲል የምንቆጣውን ያህል፣ ውሃ ሲፈስ መብራት ያለ ስራ ሲበራ ለምን አንቆጣም? እንደ ነዳጁ የምንፈልገውን ወስደን፣ በወሰድነው ልክ ለምን አንከፍልም፡፡ ይሄን ስናደርግ ከብክነት የተረፈው ነገር ዕድሉን ላጡት ወገኖች ይደርሳል። ዛሬ አንድ ቤት የሌለው ሰው እያለ፣ ሌሎች ብር ስላላቸው አምስት ስድስት ቤት እየገዙ፣ ብዙዎች ጎዳና ያድራሉ፣ በቤት ኪራይ ይሰቃያሉ፡፡ ይሄ መቆም አለበት፡፡
በጣይቱ ሆቴል የተጀመረው “በልኬ ምግብ ቤት” ተቀባይነቱ እንዴት ነው?
በጣም ጥሩ ነው፡፡ እንደውም በርካታ ደንበኞች በአድናቆት እየመጡ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጣይቱ ሆቴል ከ10 ዓመት በፊት ምግብ ቤት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ ነውር ነው ብሎ ያወጀና ተግባራዊ ያደረገ ነው፡፡ በዚህም አስተማሪነቱን ይቀጥላል። ሁሉም ሰው በሆቴል ብቻ አይደለም፤ በመኖሪያ ቤቱም ሀብትን ከብክነት መጠበቅ አለበት። መብራት፣ ውሃ፣ ምግብና አልባሳት በልክ መግዛትና ለሌላውም መትረፍ አለበት፡፡ ለምሳሌ አገራችን የውሃ ማማ ናት እያልን እናወራለን፡፡ በሌላ በኩል በአየር ንብረት መዛባትና በደን መራቆት አዲስ አበባ ከ50 ዓመት በኋላ ውሃ እንደማታገኝ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ እኛ ዛሬ ለሽንት ቤት፣ ለገላ፣ ለመኪና እጥበት … ከመጠን በላይ ውሃ እናባክናለን። ለልጅ ልጆቻችን ማሰብ አለብን፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው አስተሳሰብ ካልቆመ አሁንም ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ያለንን ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማችን ቀደምት ስልጡንና ኩሩ የነበርን ህዝቦች፣ በየጊዜው በሚጎበኘን ድርቅና በተለያዩ ችግሮች የተነሳ የፈረጅ ስንዴ ጠባቂ ሆነናል፡፡ ጥቂቶች ገንዘብ ስላላቸው ከልክ በላይ ሲያግበሰብሱ፣ አብዛኛው ለጠኔ እየተዳረገ ይገኛል፡፡
አገራችን ብዙዎች የሚቀኑባትና የተፈጥሮ ሀብት የታደለች ብትሆንም በእኛ በዜጎቿ ቸልተኝነት የተነሳ ከችግር መውጣት አልቻለችም፡፡ ስለዚህ ማስተዋል፣ ነገንና የልጅ ልጆቻችንን እጣ-ፈንታ ማሰብ አለብን፡፡ በጣም የሚገርምሽ ከመቶ ሰው የሚነሳው ትራፊ 20 ሰው ይመግባል፡፡ ታዲያ ለምን ከሶፍትና ከቆሻሻ ጋር ሳይቀላቀል አስተርፈን ለ20 ሰው አንመግበውም። እኔ በበኩሌ ትራፊ እንኳን ለሰው ልጅ ለውሻም ይመጥናል ብዬ አላምንም፡፡
እኔ ያልገባኝ ነገር --- ለምሳሌ ሆቴል የሚበቃኝን ብቻ በልቼ ከፍዬ ብሄድ ለሌላው የምተርፈው እንዴት ነው?
 በጣም ጥሩ፡፡ አንቺ የሚበቃሽን ብቻ ተመግበሽ በልክሽ ከፍለሽ ከሄድሽ በቂ ነው፡፡ የድርሻሽን ተወጣሽ፤ አላባከንሽም፤ የግድ ስጡ አላልንም፡፡ ለመስጠት ፀጋ መታደል አለብሽ፤ በግድ የሚሆን አይደለም፡፡ ይሄንን ሀሳብ በአገር ደረጃ እይው፡- አንድ ገበሬ ጤፍ፣ ስንዴ፣ አትክልት ---- ሲያመርትና ለገበያ ሲያቀርብ ከአፈር፣ ከተፈጥሮ፣ ከአረም፣ ከዝንጀሮና መሰል ፈተናዎች ጋር ተዋግቶ ነው፡፡ ይሄንን ምርት ብር ያላቸው ጥቂቶች ይቀራመቱትና ገበያ ላይ እጥረት ይፈጠራል፡፡ እጥረት ሲኖር ዋጋ ይንራል፤ ገንዘብ የሌለው መሸመት አይችልም፡፡ ያ ገንዘብ ያለው ሰው ደግሞ ቤቱ ወስዶ ያባክናል ይደፋል፡፡ ሌላው ያለ ምግብ ተደፍቶ ያድራል፤ ስሌቱ ይሄ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሆቴል በወር ለእንጀራ 10 ኩንታል ጤፍ ቢገዛና ለተመጋቢው የሚቀርበው ሰባት ኩንታል ጤፍ ቢሆን ሶስቱ በትራፊ መልክ ተደፋ ማለት ነው፡፡ ገበያ ላይ 3ቱ ኩንታል ቢቀር ግን ሌሎች ገዝተው ይጠቀሙበታል፡፡
አንድ ህንፃ በርካታ አምፖሎችን ያለ ስራ ሲያበራ ሲያድር ሌላው አካባቢ መብራት ጠፍቶ ያለ ብርሃን የሚቀር ወገን አለ፡፡ አንዳንድ አካባቢ ውሃ ያለመጠን ሲደፋ ስንቱ የአዲስ አበባ አካባቢ ውሃ የሚያገኘው በሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ነው፤ አይዳረስም፡፡ ይሄ መቆም አለበት፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ባለመስጠቱ አይወቀስም፡፡ ከእርሱ ተርፎ የሚደፋውን ብክነት ከቀነሰ በራሱ ትልቅ ነገር ነው እያልን ነው፡፡
ስለዚህ ሳንወድ በግድ ወደ ሶሻሊዝም እያመራን ነው ማለት ነው?
 አማራጭ የለንም፡፡ በግሌ ሶሻሊዝም በሀሳብ ደረጃም የሚበረታታና የሚደነቅ ነበር፡፡ አተገባበሩ ችግር ስለገጠመው ይመስለኛል ለውድቀት የበቃው።
አሁን በጣይቱ ሆቴል የጀመራችሁት አሰራር ለውጥ ያመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?
እኛ የድርሻችንን መወጣት ስላለብን ጀምረነዋል። በጣይቱ ሆቴል ደረጃ ከጅምሩ ውጤታማ ነው። ህዝቦቿ ደሀም ይሁኑ ሀብታም ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፡፡ ድህነት ያሳፍራል፤ አንገት ያስደፋል። ከአገር መጥፋት አለበት፡፡ የሚጠፋው በፀሎት ወይም በጉራ አይደለም፤ በስራና በስራ ብቻ ነው፡፡ የሰራ ሰው ማግኘት፣ ያገኘውን ሀብትም በፈለገው መልኩ መጠቀም መብቱ ነው፡፡ ከብክነት ውጭ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በዚህ እያገኘ፣ በሌላ በኩል የሚበትን ከሆነ አገሩንም ወገኑንም ራሱንም ይጎዳል። ከታች በድህነት ለሚኖሩት ወገኖቹ በማሰብ፣ ለመኪና ማጠቢያ የሚፈሰውን ውሃ፣ በየህንፃው ሲበራ የሚያድረውን መብራት፣ በየቤቱ የሚደፋውን ምግብ አቁሞ ላልደረሰው እንዲዳረስ፣ የሚበቃውን ብቻ መጠቀምና ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡
“በልኬ ምግብ ቤት”ን ስታስተዋውቁ ሀሳቡን ያልተቀበሉ እንደነበሩም ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
ሁሉም ሰው አንድን ሃሳብ መቶ በመቶ ይቀበላል ማለት ግብዝነት ነው፡፡ እንዴት ምግብ በግራም ይበላል ያሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጤፍ የምንገዛው፣ ቲማቲሙ ሁሉ በኪሎ አይደለም እንዴ! ገበታ ላይ ሲቀርብ በግራም መሆኑ ነውሩ ምንድን ነው፡፡ ለጤናም ለኪስም ተስማሚ ነው ብለን ስናስረዳቸው ሀሳቡን የደገፉ አሉ፡፡ የአገር ኢኮኖሚ ያለአግባብ አናቃውስ፣ ለሌሎቹም ዕድል እንስጥ፤ ሁላችንም የሀገሪቱ ሀብት ተቋዳሽ እንሁን፤ አብረን እንኑር ያለንን እንካፈል ነው ሀሳቡ፡፡ ይሄንን በቅንነት የማይመለከት ካለ እሱ ሌላ ነገር ነው፡፡ አባቶቻችን የመከሩን “እንጀራ ከእጅህ ላይ ሲወድቅ፣አንስተህ ስመህ ጉረስ ነው” “እንኳን የእህልና የድንጋይ ጡር አለው” ነው የሚሉት አባት አያቶቻችን፡፡ ዛሬ አንድ መኪና ድንጋይ ስንትና ስንት ብር እያስከፈለ እንደሆነ በተጨባጭ የምናየው ነው፡፡ ስንት የአውሮፓ አገሮች ያደጉት እንደኛ የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራቸው ግን ባላቸው ነገር ላይ ተጣጥረውና ቆጥበው ነው፡፡ ይህን መካድ አይቻልም፡፡ በሌላው በተለይ ባደገው ዓለም የሀብታምና የደሀ ልዩነት አንድ ስንዝር አይሞላም። ሀብታም ባተረፈ ቁጥር ግብር መክፈሉን ይጨምራል፡፡ ያ ግብር ለድሆቹ ይደጎማል፡፡
እስካሁን የተነሱት ሀሳቦች የግለሰቦችን መብት አይፃረሩም?
ጥያቄሽ እንደገባኝ … አንድ ሰው በገንዘቤ በሀብቴ ያሻኝን አደርጋለሁ ቢል ምን ይደረጋል … የሚለው ነው አይደል?
ትክክል ነው፡፡
እኔ ከሁሉም በላይ ነገሩን በሰውኛ መንገድ ብንመለከተው ይሻላል፡፡ አሁን ያለውን የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት፣ በየጎዳናው ሰው በችግር ላይ ወድቆ እኛ ሀብት ስንበትን ስንረጭ የምንኖር ከሆነ ይሄ ሰውኛ ባህሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በአግባቡ ሀብትና ፀጋ የሰጠን ሰዎች፣ ከኛ በታች ያሉትን ማየት አለብን፡፡ እንዳለን የምናውቀውና የምንረዳው የሌለውን ስናይ እኮ ነው፡፡ በዚህ መጠን ካላሰብን እንዴት ነው፣ ሰው መሆናችን የሚረጋገጠው፡፡ ቅድም በአንድ በጣይቱ ብቻ ለውጥ ይመጣል ወይ ብለሽኝ ነበር፤ እኛ እንደ ጅምር የበኩላችንን እናደርጋለን፡፡ አለምንና የዓለምን አስተሳሰብ የቀሩት ጥቂት የሀሳብ ባለፀጎች ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ህዝብ ነው፡፡ ጥሩ ነው ብሎ ካመነ ሀሳብን ይቀበላል፡፡ ከዚህ በኋላ ትራፊን ለሌላ መስጠት ባህል መሆኑ መቅረት አለበት የሚለው መጥፎ ሀሳብ አይመስለኝም፡፡ ከነጮች ሁለት ነገር ብቻ አደንቃለሁ፡፡ አንዱ የአመጋገብ ስርዓታቸው ነው፡፡ የሚፈልጉትን አይነትና መጠን ይመገባሉ። ሁለተኛ ሰብዓዊነታቸው ይገርመኛል፡፡ መንገድ ላይ ወድቆ ላገኙት ሰብአዊ ፍጡር የተረፋቸውን አይሰጡም፡፡ መሰረታዊ ችግሩን ያጠናሉ እንጂ። እንግዲህ በአገራችን ያለውን የበጎ አድራጎት ድርጅት መዓት ተመልከቺ፡፡ እስከ መቼ በነጮች መደገፍ ይቀጥል? እኔና አንቺ አንድ አንድ ልጅ ለምን አንመግብም፡፡ በወር 300 ወይ 400 ብር ብናወጣ፣ አንድ ልጅ ቁርስ ምሳ እራት መመገብ እንችላለን እኮ፡፡ አንድ ሰው በቀን አራት ቁርጥ እንጀራ የሚበላ ከሆነ፣ አንድ ቁርጥ ቀንሶ 30 ቁርጥ እንጀራ ያስተርፍና ወደ ሂሳብ ያምጣው፡፡ ይቻላል፤ቸልተኝነታችንን ከተውን፡፡ አሮጌ ልብስ ስንለግስ፣ በልጆች ስነ-ልቦና ላይ የሚያሳድረው ጫና አለ፡፡ እኛ የመኪና ጎማ አዲስ ስናጣ ገብቶ የወጣ እንላለን፤ ያገለገለ ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለልጆች በት/ቤት ልባሽ ልብስ ሲለገስ ‹‹ገብቶ የወጣ›› እያሉ የልጆቹ ስነ-ልቦና ሲነካ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ ቀርቶ ብክነትን ቀንሰን፣ በዓመት አንድ ጊዜም ቢሆን አዲስ ልብስ እንግዛላቸው ነው ሀሳቡ፡፡
አንድ ሰው በአማካኝ ስንት ግራም ይመገባል? ትንሹ ግራም ምን ያህል ነው? ዋጋውስ ስንት ነው?
እንደ የኪሎያችን የምንመገበው ይለያያል፡፡ አንድ ሰው በአማካይ ይመገባል ተብሎ የሚታሰበው ከ600-650 ግራም ነው፡፡ በሆቴሉ መነሻ ግራም ከ450-550 ግራም መልካም ነው ብለው የምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ከ47 ብር ጀምሮ እስከ 60 ብር በሚደርስ ክፍያ ሰዎችም በልካቸው መመገብ የሚችሉበትን መንገድ ጣይቱ ሆቴል ዝግጁ አድርጓል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አንድ አባት ያሉንን ላስታውስ፡- አንድ ሰው እስከ 40 አመቱ ገንዘብ ይሰበስባል፤ ከ40 በላይ ገንዘቡን እየበተነ ጤናውን ለመሰብሰብ ይሮጣል፤ አዋቂ ሁሉንም አጣጥሞ በሰላም ይኖራል ብለውኛል፡፡
እርስዎ ይህንን የሀብት ብክነት ቅነሳ በግልዎ ይተገብራሉ?
በገጠር እንደ መወለዴ ተርፎ ይነሳ በሚባልበት ማህበረሰብ ባድግም፣ አስተሳሰቡ ትክክል አይደለም። ይህን ባህል ትቼ በአግባቡ ነው የምኖረው፡፡ ማደግ ያለበት ባህል ማደግ፣ መቅረት ያለበት መቅረት አለበት፡፡ በቤቴ ብክነት የለም። የተረፈም አንሰጥም፤ ያለንን አካፍለን በሰላም እንኖራለን፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡
በመጨረሻ በባለሀገሩ ቱርስ እና በጣይቱ ሆቴል መካከል ከአከራይና ተከራይ ወይም ከጉርብትና ውጭ ሌላ የስራ ግንኙነት አለ?
እኔ በግሌ የሆቴሉን ማኔጅመንት በጣም አደንቃለሁ፡፡ ከሆቴሉ ማህበረሰብ ከሁሉም ጋር ጥሩ ግንኙነት ቢኖረኝም ከማኔጅመንቱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት አለኝ፡፡ ባለሀብቱ አቶ ፍፁም በጣም ቅን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ጥሩ ስብዕና ያለውና በስራ የሚያምን ነው፡፡ እኔ ደግሞ ማንም ይሁን እንዲህ አይነት ቀና አስተሳሰብ ያለው፣ በስራና በለውጥ የሚያምን ሰው አደንቃለሁ፤ አከብራለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ከአከራይና ተከራይ ያለፈ ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ የአገርን ሀብት ብክነት አንስቼ ስንወያይ፣ ምግብን በግራም መሸጥ በሚለው ተስማምተን፣ ሀሳቤን ተቀብሎ ከ15 ቀን በፊት ይህንን አሰራር በይፋ ጣይቱ ጀምሯል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የጣይቱ ሆቴል ባለቤትን አቶ ፍፁም አስገዶምን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እንደ አቶ ፍፁም ያሉ 10 አገር ወዳዶች ቢገኙ ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግስትም በአገር ሀብት ብክነት ላይ አይኑን ጥሎ እልባት ማበጀት አለበት እላለሁ፡፡

Read 2165 times