Print this page
Saturday, 18 March 2017 16:04

ትራምፕ አሜሪካ የምትሰጠውን እርዳታ ለመቀነስ አቅደዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ሁለት ዳኞች አዲሱን የትራምፕ የጉዞ ገደብ አግደውታል

     ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በራሱ ለጋሽ ድርጅቶች በኩል ለአለማቀፍ እርዳታና ለልማት የምትሰጠውን የገንዘብ መጠን በ28 በመቶ ያህል ለመቀነስ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ምክረ ሃሳቡ በኮንግረስ ተቀባይነት ካገኘ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ የአለማችን አገራት የልማት እርዳታ የሚያደርገው የዩኤስ አይዲ አመታዊ ድጋፍ በ28 በመቶ ያህል ይቀንሳል ያለው ዘገባው፤ በሌሎች ተቋማትና መስኮች የተያዙ በጀቶችም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰው ብዙዎችን ተጎጂ እንደሚያደርጉ ገልጧል፡፡
አነጋጋሪ የሆነው የትራምፕ የበጀት ቅነሳ ምክረ ሃሳብ፣ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም በጀት በ31.4 በመቶ፣ የጤናና የሰብአዊ አገልግሎቶች በጀት በ16.2 በመቶ፣ የግብርና ዘርፍ በ21 በመቶ፣ የትራንስፖርት ዘርፍ በ13 በመቶ ቅነሳ እንዲደረግባቸው የሚጠይቅ መሆኑንም አስረድቷል፡፡
የትራምፕ የበጀት ቅነሳ ምክረ ሃሳብ ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥመዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ ምክረ ሃሳቡ መከላከያን ጨምሮ በአንዳንድ ዘርፎች ከፍተኛ የበጀት ጭማሪ እንደሚያደርግ ገልጾ፣ ሃሳቡ ተቀባይነት ካገኘ የመከላከያ ወጪ በ10 በመቶ ወይም በ54 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ አብራርቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም የሃዋይ እና የሜሪላንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች ተሻሽሎ የወጣው የትራምፕ የጉዞ ገደብ ተፈጻሚ እንዳይሆን ማገዳቸው ተነግሯል። ዳኞቹ የስድስት አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለውን አዲሱ የጉዞ ገደብ ትዕዛዝ ህጋዊነትም ሆነ አግባብነቱን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ የለውም በሚል እንዳይተገበር የሚያግድ ትዕዛዝ ማውጣታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 2462 times
Administrator

Latest from Administrator