Monday, 27 March 2017 00:00

ቤት የፈረሰባቸው የቦኮሽነን ቀበሌ ነዋሪዎች አፋጣኝ እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(20 votes)

 በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የቦኩሽነን ቀበሌ ነዋሪዎች፤ የከተማው ግብረ ኃይል በላያቸው ላይ ቤት በማፍረሱ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን አስታወቁ፡፡ ከ2000፣ ከ2004 እና ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በስፍራው ባለይዞታ ከሆኑ አርሶ አደሮች እንደየአቅማቸው የተሰራ ቤት በመግዛት ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ መንግስት በሚንቀሳቀስበት የልማት ስራ በመሳተፍ፣ በፀጥታ ዙሪያ አብረው በመስራት በተረጋጋ ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የአዳማ ከተማ መስተዳድርም ነዋሪነታቸውን በመቀበል ለከፊሎቹ መታወቂያ ከመስጠቱ ባሻገር ዘይት፣ ስኳርና ሌሎች የፍጆታ እቃዎችን እንዲያገኙ ኩፖን ሰጥቷቸው እየተጠቀሙ እንደነበር ተፈናቃዮቹ ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከ10 ቀን በፊት የከተማው ፖሊስ ከሌሎች ግብረ ኃይሎች ጋር በመተባበር ያለምንም ማስጠንቀቂያና ያለምንም ዝግጅት ንብረታቸውንም ሆነ ራሳቸውን ማዳን በማይችሉበት ሁኔታ በላያቸው ላይ ቤታቸውን እንዳፈረሰ ገልፀው፤ በዚህ ሳቢያ ለፀሐይ፣ ለንፋስ፣ ለረሀብና ለበሽታ  መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ የአንድ ወር አራስ፣ የ5 ወር ህፃናት፣ ድርስ ነፍሰጡሮች፣ በሰው ሸክም የሚነሱና የሚቀመጡ አዛውንቶች … ያለመጠለያ በፈረሰ ግድግዳ ስር ለጸሀይ ተጋልጠውና ለበሽታ ተዳርገው እንደሚገኙ በስፍራው ተገኝተን ለመታዘብ ችለናል፡፡
ከአዳማ ከተማ ትንሽ ወጣ ብሎ በሚገኘው በዚህ ቀበሌ፤ ምንም ዓይነት የውሃና የመብራት አገልግሎት ባለመዘርጋቱ፣ ሰዎች በጭለማ ውስጥ ልጆቻቸውን ከአውሬ ለመጠበቅ ቆመው እንደሚያድሩ የተናገሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከአዳማ ከተማ እየተለመነ በሚመጣ አንድ አንድ ዳቦ ነፍሳቸው ለማቆየት እየሞክሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ቤቱ በፈረሰ ጊዜ ለምን አታስጠነቅቁንም በሚል ተቃውሞ ያነሱ የቀበሌው ነዋሪዎች፣ በፖሊሲ እየተደበደቡ ለእስር መዳረጋቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ገልፀውልናል፡፡
 “ከገበሬው የገዛችሁት በምን አግባብ ነው” በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “እኛ መኖሪያ ስናጣ ከገበሬው ጋር በመስማማት ከ30 ሺህ እስከ 400 ሺህ ብር አውጥተን መኖር ጀመርን” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ይህንን ስናደርግና ይህን ሁሉ አመት ስንኖር ጥፋት ነው ያለንም የለም ብለዋል፡፡ “እኛ ከገበሬው የተሰራ ቤት መግዛታችን ጥፋት ከሆነና ወንጀል ነው ከተባለ የአገሪቱ ዜጎች በመሆናችን ለልጆች ቤት እስክንፈልግ፣ ንብረታችንን እስክናወጣና እስክናዘጋጅ ድረስ ጊዜ ሊሰጠን ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ልክ እንደጠላት በላያችን ላይ በስካቫተር ቤት ሲፈርስብን ዜግነታችንን ተጠራጥረናል” ብለዋል፡፡
ግማሾቹ የቀን ስራ እየሰሩ፣ ከፊሎቹ በአረብ አገር በበረሀ ተቃጥለው የቋጠሩትን ጥሪት በቤቱ ላይ ማፍሰሳቸውን የገለፁ ሲሆን አሁን የተፈፀባቸው በደል ደግሞ እንዳያገግሙ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ህፃናት የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተውና ትምህርታቸውን አቋርጠው በችግር ላይ መሆናቸውን የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለተፈጠረባቸው ችግር መንግስትና ህዝቡ አስቸኳይ የምግብ፣ የመጠለያና የህክምና እርዳታ እንዲያደርግላቸው ከ300 በላይ የሚሆኑት የቢኮሽነን ቀበሌ ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ በአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ቅሬታና አቤቱታ ሰሚ ክፍል የስራ ሂደት መሪ ለሆኑት አቶ ዓለማየሁ ኢሮ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ብናደርግም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

Read 2745 times