Monday, 27 March 2017 00:00

የአዮዲን እጥረት በሽታ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

  “ህብረተሰቡ በበቂ መጠን አዮዲን ያለው ጨው እያገኘ አይደለም”
                     
       በኢትዮጵያ የአዮዲን እጥረት በሽታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተጠቆመ፡፡ 51.8 በመቶ በመውለጂያ ዕድሜ ያሉ ሴቶችና 47.5 በመቶ ለትምህርት የደረሱ ልጆች የአዮዲን እጥረት በሽታ አደጋ ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በካፒታል ሆቴል አዘጋጅቶት በነበረው የሁለት ቀናት ጉባኤ ላይ እንደተገለፀው፤ በአገሪቱ ያለው የጨው አቅርቦት የአዮዲን እጥረት ያለበት በመሆኑ ከግማሽ በላይ ያህሉ ህዝብ ለአዮዲን እጥረት በሽታ ተጋላጭ ሆኗል፡፡
በኢንስቲቲዩቱ በተደረገ አገር አቀፍ የማይክሮ ኒዩትረንት የዳሰሳ ጥናት እንደተመለከተው፤ 37 በመቶ ለወሊድ ዝግጁ ከሆኑ ሴቶች ውስጥ 10.8 በመቶ የሚሆኑት በአዮዲን እጥረት ሳቢያ በሚከሰት የጤና ችግር ተጠቅተዋል፡፡ የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ኃይሉ በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት፤ለምግብነት የሚውለው ጨው ከአዮዲን ጋር እንዲደባለቅ አስገዳጅ ህጉ በ2003 ዓ.ም የወጣ ቢሆንም በተገቢው መንገድ አዮዲን ያለበት ጨው ለተጠቃሚው እየደረሰ አይደለም። ይህንኑ ሁኔታ ለማየት በኢንስቲቲዩቱ ጥናት መደረጉን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከቤት ለቤት በተሰበሰቡ ናሙናዎች በተደረገ ጥናት መሰረት 26 በመቶ የሚሆነው ጨው ብቻ በበቂ መጠን አዮዲን የያዘ መሆኑ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህብረተሰቡ አዮዳይዝድ ጨው ለማግኘት እንዲችል ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ከቱርክ ባለሃብቶች ጋር በጋራ በመሆን በዓመት 450 ሺ ኩንታል ከአዮዲን ጋር የተቀላቀለ ጨው በማምረት ለገበያ እንዲቀርብ ጥረት ቢደረግም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ህብረተሰቡ አሁንም ጤንነቱ የተረጋገጠና በበቂ መጠን አዮዲን ያለው ጨው እያገኘ አይደለም ብለዋል፡፡
SVS የሚባለውና በቱርክ ባለሃብቶች የተቋቋመው የጨው አምራች ድርጀት በበኩሉ፤ ከአንድ ወር በፊት በተጀመረው ጨውን ከአዮዲን ጋር በመቀላቀል ለገበያ የማቅረብ ሥራ፤ በየወሩ ከ4 እስከ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግ ጠቁሞ፣ ቀደም ሲል በኩንታል 210 ብር ይሸጥ የነበረውን ጨው በ529 ብር ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሆኖም  የአዮዲን እጥረት ያለበት ጨው በስፋት በገበያ ላይ በመኖሩ፣ አዮዲን ያለበት ምርቱ  እንዳይሸጥ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የአዮዲን እጥረት ለእንቅርት በሽታ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ ነፍሰጡር እናቶች እጥረቱ በሚያጋጥማቸው ወቅት ማስወረድ፣ የሞተ ልጅ መውለድ፣ ከጊዜው በፊት መውለድና በህፃኑም ላይ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ችግሮችን ያመጣል፡፡

Read 2416 times