Monday, 27 March 2017 00:00

በዚህ ወር ዝናብ ካልዘነበ፣ የድርቅ የተረጂዎች ቁጥር ይጨምራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ከለጋሾች የሚጠበቀው እርዳታ በሚፈለገው መጠን አልቀረበም ተብሏል
   በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በያዝነው ወር ዝናብ ካልዘነበ፣ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ከውጭ ለጋሾች የሚጠበቀው እርዳታም በሚፈለገው መጠን እየቀረበ አይደለም ተብሏል፡፡
በድርቅ ለተጎዱ 5.6 ሚሊዮን ዜጎች እስካሁን መንግስት አስፈላጊውን እርዳታ እያቀረበ መሆኑን በቀረበው ጥሪ የአሜሪካ፣ የካናዳና ስዊድን መንግስታት ከሰጡት ምላሽ ውጪ በሚፈለገው መጠን እርዳታ አለመገኘቱን ጠቁመው፣ በመጋቢት ወር ዝናብ ካልዘነበ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅት ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ክልል ለክልል እርዳታ እየተሰጣጡ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ አማራ ክልል ለኦሮሚያ፤ ትግራይ ክልል ለሶማሌ የሰጡትን እርዳታ ጠቅሰው የአፋር ክልልም ለሶማሌ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁንም ከለጋሽ አገራት ተጨማሪ እርዳታ ይጠበቃል ተብሏል፡፡  
ለጋሾች ለጥሪው ፈጣን ምላሽ መስጠት ያልቻሉት ከኢትዮጵያ በከፋ ሁኔታ “ረሃብ” አጋጥሞናል ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በመኖራቸውና በየመንና በሶሪያ ባለው አለመረጋጋት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ከድርቁ ጋር ተያይዞ በሶማሌ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የአተት ወረርሽኝ መቀስቀሱን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል የህክምና እርዳታ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን 20 ሚሊዮን ዜጎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡



Read 2284 times