Print this page
Monday, 27 March 2017 00:00

እየተዋወቅን መወሻሸት

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንደሚነግሩን ከሆነ ‘ፈረንጆቹ’ አገራት ሰዉ ቴሌቪዥ ላይ ማስታወቂያዎች ማየት ይወዳል ይባላል፡፡ ፈጠራ የሚታየው እዛ ላይ ነዋ! እኛ መቼ ነው… ማታ ስልክ ሲደወልልን… “ቆይ እባክህ ቲቪ ላይ ማስታወቂያ ተላልፎ ሲያልቅ መልሼ እደውለልሃለሁ…” የምንባባለው! አሁን አሁንማ ጭራሽ ብዙዎቹ ማስታወቂያዎች ሲመጡብን የሚቀናን ጣቢያ መለወጥ ሆኗል፡፡ ልክ ነዋ…ከተራ ማጋናን ይልቅ ቅልጥ ያለ ውሸት የሚመስል ነገር ስንስማ፣ አይደለም የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የመኖሪያ ጣቢያ የማንለውጥሳ!
ስሙኛማ…እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኖ ቀረ ማለት ነው!
እናላችሁ… መሥሪያ ቤቱ በአንድ መቶ አንድ ነገር ተተራምሷል፡፡ ሥራ አስኪያጁ መድረክ ላይ ይወጣና “በእውነቱ በድርጅታችን ሠራተኞች መሀል የሚታየው የሥራ ፍቅር ለሌሎች ድርጅቶችም ሁሉ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው… ምናምን ይላል፡፡ ይሄኔ ትክክለኛው እርምጃ ምን መሰላችሁ… በፉጨትና በጩኸት ከመድረክ እንዲወርድ ማደረግ፡፡ ልክ ነዋ… “የዘንድሮ አፈጻጸማችን አርባ ዘጠኝ በመቶ ነው” እየተባለ የምን ጭብጫቦ፣ ምሳሌ መሆን ቅብጥርሰዮ ነው! ግን ምን ቢሆን ጥሩ ነው… አዳራሹ በጭብጨባ ይደበላለቃል፡፡
እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኗላ!
ለምሳሌ እንደ እኛ አይነቱ የዕለት እንጀራውን ወረቀት ላይ በመቸክቸክ የሚያሳድድ አለ፡፡ እናላችሁ… ከተያዩ ረጅም ጊዜ ከሆነ ወዳጅ ጋር ይገናኛል፡፡ ያው የተለመደውን… “እኔ እኮ ከዚህ አገር የወጣህ ይመስለኝ ነበር፣ እንደውም በቀደም እንትናን አግኝቼው አሜሪካ የትኛው ስቴት ውስጥ እንዳለህ ጠይቄው ነበር፣” ይላችኋል፡፡
ይቺ እንግዲህ ታክቲካዊ መዋሸት ትባላለች፡፡ አለ አይደል… “አንተን የመሰለ ሰው እዚህ አገር ምን ይሠራል!” አይነት ሜዳሊያ ድርደራ፡፡ ታዲያላቸሁ አሜሪካ ያላንሁበትን ስቴት አድራሻ ሲያፈላልግ የቆየው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው… “ይገርምሀል አንድም ቀን የምትጽፈው አምልጦኝ አያውቅም!” እንዴት ነው ነገሩ!  የአሜሪካ ጉዳይስ! የማክዶናልድ በርገር ጉዳይስ! እኛም…አለ አይደል… “ለምን ታንገላታኛለህ…  ወይ አሜሪካ እንደወሰድክ እዛው ተወኝ፣ ወይ እዚህ ካመጣኸኝ ሮፓክ፣ ሲ.ኤም.ሲ. ምናምን አስቀምጠኝ…” አይነት የመብት ትግል እንደማካሄድ… “ቢራውን ጨርስና ሌላ ድገም እንጂ፣ ሻይ አደረግኸው እኮ!” ምናምን ብለን ራሳችንን ‘በመሸወድ’ ድራማ ላይ እንሳተፋለን፡፡
እናላችሁ…አብሮ ለመኖር መዋሸት ገዴታ እየሆነ ነዋ፡፡ እኛ ጸሃፊዎቹ ሊከፋን ይችላላ! “እሱ ማን ሆኖ ነው የእኔነ ጽሁፍ የማያነበው!” ልንል እንችላላና!
እናላችሁ…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…እየተወሻሸን እንደሆነ እየተዋወቀንም እንቻቻላለን።
“ኸረ እባክህ…አበዛኸው…”
“ይሄ እንኳን ትንሽ መስመር አለፈ…”
“ኸረ ሰው ምን ይለኛል በይ!”
ብሎ ነገር የለም፡፡ እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኗላ!
እናላችሁ…የእኔ ቢጤውን …
“አንተ! ይሄ ሁሉ ሻኛ ከየት መጣ… ልክ ጆን ዌይንን አክለህ የለም እንዴ!” ሲሉን…አለ አይደል… “ይሄም በዛ፣ ለራሴ ጭብጦ አክዬ ነጥብ ልመስል ምንም አልቀረኝ…” ምናምን ከማለት ይልቅ በትልቅ ፈገግታ እንቀበለዋለን፡፡
እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኗላ!
ለምሳሌ እሷዬዋ እንትን ቡቲክ ሄዳ ዓመት ባጠራቀመችው ብር አሪፍ ልብስ ትገዛለች፡፡
“እንዴት ነው፣ አላማረብኝም” ትላለች፡፡ እንግዲህ ይሀ አስተያየት መጠየቅ አይነት ቢመስልም የሚፈለገው አስተያየት ሳይሆን ማረጋገጫ ነው። (አብሮ ለመኖር አስተያየት ሳይሆን ማረጋገጫ የመስጠት ጥበብ እንሚያስፈልግ ማወቁ… “እሱ ማን ሆነና ነው!” ከመባል ያድናል፡፡)
እናላችሁ… “ማማር ብቻ ይገልጸዋል እንዴ፣ አንቺ ለካስ እንዲህ ቆንጅዬ ነሽ!”
“ብቻ ከሰው ዓይን ይጠብቅሽ… ሰው እንዲህ ያምርበታል!”
እያልን እንደረድረዋለን፡፡ ይለቁንም…
“ለምንድነው የሚያማክርሽ ሰው ይዘሽ የማትሄጂው!”
“ገና ለገና ውድ ልብስ ስለተለበሰ ቁንጅና አለ እንዴ!”
ምናምን አይነት “ለክሬ፣ ለማተቤ” ብሎ ነገር የለም፡፡ አለበለዛ… ወዳጅነት አበቃለት ማለት ይሆናላ! ወዳጅና ዶላር (ቂ…ቂ…ቂ…) እንደ ሰማይ ቤት በራቀበት ወዳጅ ማጣት አያስፈልግማ!
እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኗላ!
የሆነ ወዳጅ፣ ዘመድ ቤት የቀረበልን ምንም ይሁን ምን…
“ምግቡ እንዴት ነው!” ስንባል… አለ አየደል…
“በጣም ነው የሚጥመው” ምናምን እንላለን። “እንዲህ አየነት የጣፈጠ ምግብ ከበላሁ ስንት ዘመኔ!”
በሆዳችን እኮ… “ቤቴ ሳልደርስ የሄ ነገር መንገድ ላይ ጉድ እንዳያደርገኝ” እያልን ነው፡፡ ግን አፍ አውጥቶ እንዲህ አይባልማ!  እንዲሀ አይነት ግልጽነት  ከሰው ጋር አያኗኗርማ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንድ ሁላችን ሳንነጋገር የተስማመንባት የምትመስል “ይገርምሀል፣ ልክ ልደውልልህ ስል ነው የደወልክልኝ…” የምንላት ‘የውሸቶች ሁሉ እናት’ አለች፡፡ መጨረሻ የተደዋወሉ ጊዜ እኮ ትረምፕ ገና ሊወዳደሩ አልወሰኑም ነበር፡፡
“ይገርምሻል ለምን እንደሁ ትናንት ስላንቺ ሳስብ አልውል መሰለሽ!…”
“አታምነኝም፣ ሌሊት በህልሜ አይቼሀ ለማን ልንገረው ስል ነው እኮ የመጣኸው…”
አራትና አምስት ዓመት በምንም አይነት ዘዴ ሳንገናኝ ከርመን … አለ አይደል… “አልረሳሁህም፣ አልረሳሁሽም” አይነት ነገር ነው፡፡ የምር ግን ግጥምጥሞሹ አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ… ‘ልክ ልንደውል ስንል’ ወይንም ‘ልክ ስለ እሱ ስናስብ’ ሰውየው ይደውላል፡፡  ከሰባት ዓመታት በኋላ ‘በህልም  ባየነው ማግስት’ ቢሯችን ዘው ይላል፡፡
እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኗላ!
መረሳሳት ይቻላል እኮ፡፡ ምን ክፋት አለው… ዘንድሮ አይደለም የድሮ ወዳጅና የትምህርት ቤት ጓደኛ፣ ራሳችንን እንኳን እየረሳን አይደል እንዴ!  ዛራና ቻንድራ እንኳን ተረስተው የለም እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… (ስሙኝማ… እግረ መንገዴን… እንደዛ የከተማችን ዓቢይ ርዕስ የሆኑ፣ ባልና ሚስትን ‘አንተ፣ አንቺ’ አባባሉ የተባለላቸው፣ ባይረጋገጥም ለፍቺ ምክንያት ሆኑ የተባለላቸው ዛራና ቻንድራ በእንድ ጊዜ አንትን የነካው እንጨት ሆነው አረፉትሳ! እንኳንም ሰልፍ ሳይካሄድባቸው በቃቸው፡፡)
እኔ የምለው… ‘ፕሮፋይል’ ፎቶ የሚሏት ውሸት ደግሞ አለችላችሁ፡፡ ‘የጦቢያ ወንድ ሁሉ እንዲህ ሀንድሰም ነው እንዴ!’ ያሰኛል፡፡ የምር ግን…ፕሮፋይል ፎቶ በሚሉት ነገር… ልክ እቅጯን መልካቸውን የሚመስሉ ሰዎች በመቶኛ ይቀመጡልንማ! አሀ…የእኛ አይነቱ የቀሺም ቲማቲም ድልህ የተጣለ ጣሳ የመሰለው ሁሉ…አለ አይደል… “ገና ሲያዩት ያስደነግጣል!” ምናምን የሚያሰኝ ፎቶ እየለጠፍን ለመራጭም ችግር ሆነ እኮ!
እየተዋወቅን መወሻሸት አብሮ የመኖር ጥበብ ሆኗላ!
ደግሞላችሁ… የ‘ቦተሊካ’ ውሸት አለ፡፡ እንደውም “ፖለቲካ በአሳማኝ ሁኔታ የመዋሸት ጥበብ ነው…” ምናምን የሚለ ጥቅስ… አለ አይደል…ገና ባንደርስበትም… የሆነ ቦታ ግን አለ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በዚሀ ዘመን አለ አይደል… “እኔ የምበላውና የምጠጣው አጥቼ አይደለም፡፡ ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት ህዝቡን ለማገልገል ብዬ ነው…”  
(ድንገት ዘው ብሎ ገብቶ ‘ታማኝነቱን’ በተግባር ለማስመስከር ከሚለፋ ትኩስ ቦተሊከኛ ይሰውራችሁ፡፡ አለ አይደል… የሆነ ያለሆነውን ሲዘረግፍላችሁ እኮ የራሱ ‘አገር በቀል ዳስ ካፒታል’ የሚል ገና ያልታተመ መጽሐፍ ያለው ነው የሚመስለው፡፡)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3183 times