Monday, 27 March 2017 00:00

ሰው የመሆን መፍጨርጨር

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ(singofbird@gmail.com)
Rate this item
(7 votes)

 አሁን በቀደም ዕለት የአይሁዳዊቷን ልጃገረድ አና ፍራንክ “the diary of anna frank” ከአስር አመታት በኋላ በድጋሜ እያነበብኩ ነበር፡፡መጽሐፉን እጄ ላይ የተመለከተ አንድ የንባብ ወዳጄ ‹‹የናዚዎችን  ጭካኔ በብዙ መጻሕፍት ላይ አንብበነዋል፡፡ ምን ይሁነኝ ብለህ ነው ከዚህ መጽሐፍ ጋር የምትታገልው›› አለኝ። ምስኪን ይህች ሚጢጢ ትንግርተኛ ልጃገረድ በጠያቂ ነፍሷ ነፍሴን ስንት ጊዜ እንዳራቆተቻትና እንበደቧጨረቻት ቢያይልኝ ምናለ፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት ይህንን መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ ማልቀሴን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህችው ንባቤ ከማልቀስ ይልቅ ‹‹ሰው የመሆን መፍጨርጨር ግን ምንድን ነው?›› የሚል ግማሽ ድንቁርና የታከለበት ጥያቄዬን ታቅፌ ተመለስኩ፡፡ ፍቅር ምንድን ነው? ሕይወት ምንድን ነው? ብሎ ጥያቄ ከግማሽ ድንቁርና ውጭ ምን ሊሆን ይችላል?
አዎ ሰው የመሆን መፍጨርጨር ብሎ መጀመር ትንሽ ግር የሚል ነገር አለው፡፡ እህ ግን እኮ ከላይ ከላይ ስታዩት የቀለለ የሚመስለው ሰው የመሆን ነገር በጥያቄ መልክ ሲቀርብ ለመመለስ ከሚያዳግቱ ጥያቄዎች ቁንጮው እኮ ነው፡፡ ኸረ እንዲውም የእግዚብሔርን ሕልውና ከማጠየቁ ሂደት ሳይስተካከል ይቀራል?
ሰው የመሆን መውተርተር የመነሻ ውሉ እኔነት ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ ከጊዜ ወንዝ ላይ በጨለፍኳቸው 28 የእኔነት ዓመታት ባሰመርኩት መስመር ላይ እልፍ የደበዘዙ ምስሎች ይታዩኛል። አንዳንዳንድ ጊዜ የኢየሱስ ደቀመዝሙር ሆኜ በሰፋፊ የእግር ዳናዎቹ ላይ ትንንሽ ፈለጎቼን እያለካካሁ በተሰጠኝ መክሊት ሚጥጥዬ ክዋክብትና ጨረቃዎችን ስፈጥር አያለሁ፡፡ ሌላ ጊዜ ከውሻ ወዳጁ ዛራስቱራ የሚቀዳ ድቅል ማንነት እንዳለኝ አስብና ይምታታብኛል፡፡ ደግሞ ሌላ ጊዜ የባይተዋር ገድሌ የሚነበብ የሲሲፐስ አቻ ፍጥረትነት ይሰማኝና እኔነቴ ይሳከርብኛል፡፡
ይህንን ሁሉ ከንቱ ቅዠት ብለን ልናልፈው ብንችል አንኳን ሰው የመሆን መፍጨርጨር ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ መሸሽ እንዴት ይቻለናል? በእርግጥስ አያቶች ‹‹ሰው ለመሆን ጣር›› ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ደጃች፣ ፊታውራሪ፣ ራስ፣ እንቶፍንቶ ሁን ለማለት ፈልገው? እንዲያ ከሆነ እንደ ጎልድመንድ አሊያም እንደ ዛራስቱራ የትም ውሎ የትም የሚያድር መድረሻ ቢስ በመሆን ሰውነትን መላበስ አይቻልም ልንል እኮ ነው? ቆይ ቆይ የኢየሱስ ምድራዊ ማንነትስ በጥልቀት ሲጠና ከዚህ ወለፈንዲ ኑረት ምን ያህል ኢንች ይርቃል? በበኩሌ ምንም እላለሁ፡፡
እኛ በውስጣችን የሚመላለሱ የጥያቄዎች ንጥር ውጤቶች ሳንሆን እንቀራለን? እኔ እኮ ያለ ጥያቄዎቼ ከዘመናት በፊት ንቦቹ እንደ ለቀቁት ቀፎ ምንም ነኝ። የአንድ ሰው ማንነትስ በዕልፍ የሚለካውስ በእነዚህ የጥያቄዎች ውል የለሽ ፍጭርጭሮሽና እሱን ተከትሎ በሚመጣው ሽሽት አይደለም ትላላችሁ? ‹‹የራስን ልብ በራስ አዕምሮ መፋለም ምን ክል ከባድ ነው።›› ትላለች አና ፍራንክ ይሄ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ሰው መሆን መፍጨርጨር ምን ማለት ነው? ፀጥ ያለ፣ በኑሮው የረካ፣ የተረጋጋ፣ ግርማ የተላበሰ፣ እንዲያ ዓይነት ሰው መሆን ማለት ማለት ይሆን? ግን እኮ በየአደባባዩ፣ በየመዝናኛ ማዕከሉ፣ የሰከነና የተከበረ የሚመስለው ሰው ሁሉ በሩን ዘግቶ ግን የራሱ ዓለም ያለው የማናውቀው ሌላ ሰው እኮ ነው፡፡ በየብቻ ዓለሙ የሚንሰቀሰቅበት የሚፈነድቅበት የራሱ ዓለም ያለው፤ በጥቂት መዳፈር በብዙ ውስልትናና ውምብድና ያደፈች ነፍስ ያለው፤ እንደገና ይህችን በሃጥያት ያደፈች መሰለችውን ነፍሱን ነፃ ለማውጣት ለሱባዔ የሚተጋ፣ ለምህላ የሚሰለፍ ተፍገምጋሚ ነፍስ ያለው፤ ከሞላ ጎደል የሁሉም ሰው ዓለም በግርድፉ ሲነበብ እንዲህ ነው፡፡
እናስ ሰው የመሆን መፍጨርጨር በመጠኑ ወደ ሰከነ በሀብትና በዕውቀት ወደ መጠቀ የሕይወት ፅንፍ መጓዝ ነው ብለን መደምደም እንችል ይሆን? ግን ግን ለምንም ባለመጓጓትና ለምንም ባለመታዘዝ ቤተክርስቲያን የገባች ውሻ የሚገጥማት አይነት ሕይወት ውስጥ ሰው የመሆን መፍጨርጨርን ማግኘት አይቻልም ለማለት ምን አመክዮ አለን? ምንም፡፡ ጀግኖች ሆነን ሳለን የፈራንባቸው አጋጣሚዎች ሺ ምንተሺ ይሆኑብናል፡፡ ተጉሃን ሆነን ሳለን እልፍ ጊዜ ሰነፎች ነበርን፡፡ ለማንም ደንታ የለኝም በለን እነዳልደፋን ከሕይወታችን በመውጣታቸው ለዓመታትና ከዚያም ለሰፋ ጊዜ ተብከንክነናል፡፡ ሌላም ሌላም… ይህም ሁሉ ሆኖ ሰው መሆን መፍጨርጨር እንዲህ ነው ብለን ያንን ለመኮነን ይሄንን ለማድነቅ አንዴት ይቻለናል?
ደግነቱ ለተነሳንለት የሚገዳደር ጥያቄ አንድ ዓይነት መልስ የማግኘት ግዴታ ውስጥ አይደለንም። ቀድሞ ‹ምንድን› ብሎ ጥያቄ ግማሽ ድንቁርና የታከለበት የፈላስፎች ጥያቄ መሆኑን ተናዘናል፡፡ ቢሆንም የመጠየቅ መብታችንን ተጠቅመን ሰው የመሆን መፈጨርጨር ምንድን ነው እንላለን፡፡ እርስ በርሱ በሚጣረስ ዕጣ ፋንታ በተምታታ ህልውና ውስጥ መሆናችንን እያወቅን እንኳን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሰው የመሆን መፍጨርጨር ምንድን ነው? እንጮሃለን፡፡ እንደእኔ እንደእኔ ትውልዶች ሁሉ በዕልፍ ዓመታት ሂደት እየተቀባበሉ ይህንን ጥያቄ ቢያስተጋቡት እንኳን መልሱ ያው መልሱ  አልተሰጠም ይመስለኛል፡፡ አይ አይ ቁርጥ ያለ መልስ አለን የምትሉ የምትሉ ካላችሁ ልትጨምሩበት መብት አላችሁ፡፡  

Read 2889 times