Monday, 27 March 2017 00:00

የአልጋ ላይ ጦርነት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(13 votes)

 አባወራው ሚስቱን ያሳጣበት ደብዳቤ ምን ይላል?
                     
        ከሰው ልጆች አብሮነት ውስጥ ትዳር አስቸጋሪውና ውስብስቡ ግንኙነት ነው ይላሉ፤ ዘ ሜሬጅ አፌርስ በሚል መፅሐፍ ውስጥ ጠቢባዊ ጽሁፍ ያበረከቱት አስቦርኔ፡፡…ትዕግስት፣ ኪህሎት፣ መንፈሳዊና አካላዊ ብስለት ይጠይቃል ሲሉም ያብራራሉ፡፡  
 ትዳርን በተመለከተ  የሥነ ጋብቻና የሥነ ልቡና ምሁራን ብዙ ትንተና ይሰጣሉ፡፡ እንደ አጋጣሚ እኔም በዚሁ ጉዳይ አንድ ሁለት ኮርሶችን ስለወሰድኩ አንዳንዴ ጉዳዩ ያብከነክነኛል፡፡ አንድ የገባኝ ቁምነገር ግን ምን መሰላችሁ ----- ጉዳዩ በትንታኔ ብቻ የሚቃና ሳይሆን ሙሉ ትኩረትንና የየእለት ውሳኔን የሚጠይቅ መሆኑን ነው፡፡
ጉዳዩ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማትን ድጋፍ የሚናፍቅና የሚጠብቅ አይደለም፡፡…ሃገር ታላቅ እንድትሆን፣ማህበረሰብና ህብረተሰብ በቀና መንገድ ወደ ብልጽግናና ሰላም እንዲሸጋገር የቤተሰብ ሚና ታላቅና ዋነኛ ነው፡፡
  ብዙ የሥነ ጋብቻ ምሁራን እንደሚሉት፣ ትዳር መመስረት ከባድ አይደለም፡፡ ይልቅስ ፈተናው መዝለቁ ላይ ነው፡፡ ጀምስ ኤች ጀውንሴይ የተባሉ ጸሃፊ፤”ቃል መለዋወጥ እንኳ ሳይቻል በፍቅር መሾር፣በመውደድ መጦፍ ይቻላል፡፡ ትልቁ ነገር ነበልባሉን አልፎ፣የበሰለ ፍም ሆኖ ፍቅርን ማቆየቱ ላይ ነው” ብለዋል፡፡ አንድ የኖርዌይ ወታደርና አንዲት የሜክሲኮ ወጣት በፍቅር ወድቀው ነበር፡፡…እርሱ እንግሊዝኛ ይሞካክራል፤ስፓኒሽ አይችልም፡፡ እርሷ ደግሞ ሁለቱንም አትሞክርም፤ታዲያ አጅሬ ፍቅር መች ቀልድ ያውቃል፡፡…ነፍሳቸውን አሳጣቸው፡፡ ሰውየው ግን እንዴት እንደሚዘልቁ እንጃ ነው የሚሉት፡፡…እንዴት እንደሚዘልቁ መገመትም ያዳግታል፡፡…ግና ፍቅር እንዲህም ነውና ያጣምዳል፡፡
ብዙ የምናያቸውና የቆሙ፣የማናያቸው የወደቁ፣ውስጣቸው ተቦርቡሮ፣ለመውደቅ የሚያጣጥሩ ሁሉ ሲጀምሩ፣ባብዛኛው በፍቅር ወይም በወረት ነው፡፡ ምናልባትም በስለው ወደ ጋብቻ የመጡት ብዙ አይደሉም፡፡ አሁን አሁን ደግሞ  የዘመኑ ተፅዕኖም ሰውን ወደ ሃብትና ቁሳቁስ እንዲያዘነብል ያደረገው ይመስላል፡፡…”ምን አለው”…”ምን አላት›› የሚለው ሳይበዛ አይቀርም፡፡
አንዳንዶች ደግሞ የትዳር መናጋት የተግባቦት ችግር ነው ይላሉ፡፡ አርኖልድ ቤኔት የተባሉ የሥነ ጋብቻ ባለሙያ እንደሚሉት፤ ሌላው ቀርቶ የምንነጋገርበት መንገድና ድምጸት እንኳ ከጀርባው ሌላ ትርጉም ሊፈጥር ይችላል፡፡ “90% of the friction in life is caused by the tone of voice.” ባይ ናቸው - አርኖልድ፡፡
ስለዚህ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና በርካታ የሥነ ጋብቻ ባለሙያዎችና በጋብቻ ላይ የተጻፉ መፃህፍት እንደሚገልጹት፤የግብረ ስጋ ግንኙነት አለመጣጣም የሚፈጥረው ክፍተት ለቤተሰብ መፍረስ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ዶ/ር መለሰ ወጉ በሥነ ጋብቻና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ መጻህፍት የጻፉ ሲሆን የጋብቻ የምክር አገልግሎት በመስጠትም ልምድ አካብተዋል፡፡  
ባለሙያው በጋብቻ አማካሪነት አገልግሎታቸው ከገጠሟቸው ውስጥ አንድ ከሚስቱ ጋር በግብረ ሥጋ ግንኙነት ያልተጣጣመ አባወራ፤ከሃያ ዓመት በፊት የጻፈላቸውን ደብዳቤ ዋቢ በማድረግ የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት ጥረዋል፡፡ ደብዳቤው በእጅጉ ስሜት የሚነካና ለፍርድ የሚያስቸግርም ዓይነት ነው፡፡  የደብዳቤውን አጻጻፍ ስንመለከት አባወራው የጻፈው ለዶክተሩ ብቻ ሳይሆን በግብረ ስጋ ረሃብ ላሰቃየችው ሚስቱም ጭምር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ዶክተሩ በመጽሐፋቸው ላይ ደብዳቤውን እንዲህ አቅርበውታል፡-
‹‹የተወደድሺው ውድ ባለቤቴ ፣ባለፈው ዓመት ካንቺ ከውድ ባለቤቴ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ለመፈጸም ፈልጌ 365 ጊዜ ያህል ጥያቄ አቅርቤልሽ ነበር፡፡ ይግረምሽና ‹‹እሺ›› ብለሽ የፈቀድሽልኝ 36 ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ‹‹እምቢ›› ያልሺባቸውን ምክንያቶችሽን ከዚህ በታች በቅደም ተከተል ዘርዝሬያቸዋለሁ፡-
23 ጊዜ በጣም መሽቷል አልሺኝ፡፡
27 ጊዜ ልጆቹ ይነሳሉ አልሺኝ፡፡
15 ጊዜ ገና አልመሸም አልሺኝ፡፡
16 ጊዜ በጣም ሞቆኛል አልሺኝ፡፡
5 ጊዜ በጣም በርዶኛል አልሺኝ፡፡
47 ጊዜ እንቅልፍ እንደያዘሽ አስመስለሽ
              እምቢ አልሺኝ፡፡
10 ጊዜ ጎረቤት ይሰማል አልሺኝ፡፡
27 ጊዜ ወገቤን አሞኛል አልሺኝ፡፡
14 ጊዜ ጥርሴን አሞኛል አልሺኝ፡፡
18 ጊዜ ራሴን አሞኛል አልሺኝ፡፡
6 ጊዜ እየሳቅሽ፣ሳቄ አስቸግሮኛል ብለሽ
              እምቢ አልሺኝ፡፡
36 ጊዜ ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም
              አልሺኝ፡፡
10 ጊዜ ሆዴ ሙሉ ነው (በጣም
             ጠግቤያለሁ) አልሺኝ፡፡
17 ጊዜ ቴሌቪዥን ስለማይ አልችልም
              አልሺኝ፡፡
11 ጊዜ እኔን በመንቀፍ እምቢ አልሺኝ፡፡
አሁንም 11 ጊዜ እንግዳ አለ በማለት እምቢ
              አልሺኝ፡፡
19 ጊዜ መጸዳጃ ቤት መሄድ አለብኝ
            አልሺኝ፡፡
በጠቅላላው 329 ጊዜ እምቢ አልሺኝ፡፡ ግብረ ስጋ እንድንፈጽም በፈቀድሽልኝም ጊዜም ይህን ያህል ሙሉ ደስታ (እርካታ) አላገኘሁም፡፡ ምክንያቱም፡-
6 ጊዜ ማስቲካ ታኝኪ ነበር፡፡
7 ጊዜ ቴሌቪዥን እያየሽ ነበር፡፡
16 ጊዜ “ቶሎ ጨርስና እባክህ
             ተነሳ”አልሺኝ፡፡
6 ጊዜ እንቅልፍ ወሰደሽ፡፡
1 ጊዜ ስሜት ኖሮሽ በመንቀሳቀስሽ
              የጎዳሁሽ መሰለኝና ደነገጥኩ፡፡
ውዷ ባለቤቴ፣ታድያ ብዙ ጊዜ አምሽቼ መምጣቴ፣ ሰክሬ ወደ ቤት መግባቴ ይህን ያህል ሊደንቅሽ አይገባም፡፡”
ይህ ሁሉ የባልየው አቤቱታ ነው፡፡ ሰውየው 365 ቀናት ያህል የግብረ ስጋ ግንኙነት መጠየቁ በራሱ ግራ አጋቢ ነው፤ምናልባት ብዙ ሙከራ አድርጎ ጥቂት ለማሳካት ይሆን!?
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ እነዚህ ባለትዳሮች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አልጋ ለይተዋል፡፡ ምናልባትም በሚስትየው በኩል ያለውን ቅሬታ ስላልሰማን ማንም ላይ ለመፍረድ አንችልም፡፡..ግን አንድ ነገር እናስባለን፤ በመካከላቸው ግልጽነት ያለመኖሩንና የተግባቦት ክፍተቱን!
 እናም የትዳር መፍረስ የሃገርና ትውልድ መፍረስ በመሆኑ ሁላችንም የዚህ ዓይነቶቹን መናጋቶች ስቀን ልናልፋቸው አይገባም፡፡ በእውነት አይገባም!!  

Read 11735 times