Monday, 27 March 2017 00:00

የፖለቲካ ቀውስ - በቁርጥራጭ ሃሳቦች!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(42 votes)

  ከዚህ በታች የቀረቡት ቁርጥራጭ ሃሳቦች የዛሬ ዓመት ግድም በአገራችን የህዝብ አመጽና ተቃውሞ ተቀስቅሶ በነበረበት ወቅት በተለያዩ ጊዜያት የተከተቡና ፌስቡክ ላይ ፖስት የተደረጉ ናቸው፡፡ ከጭንቀት፣ ግራ ከመጋባት፣ ከፍርሃት፣ መጪውን ካለማወቅ፣ ተስፋ ከመቁረጥ፣ ለራስ  ደህንነት ከመፍራት፣ አገርን ከመውደድ (ወይም ነፍስን)፣ በዕጣ ፈንታችን ከማዘን፣ በመሪዎቻችን አርቆ አሳቢ አለመሆን ከመቆጨትና ከመንገብገብ ---- የተወለዱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ እዚህ መቅረባቸው ያለፈ ሰቆቃን ለማስታወስ አይደለም፡፡ ምናልባት ትውስታው ጥፋታችንን እንዳንደግም ያሳስበን ይሆናል፡፡ አሁንስ የት  ነው ያለነው ---- የሚለውንም በቅጡ እንድንፈትሽ ያነቃን ይሆናል፡፡ ሃሳቦቹ በተለያዩ ቀናት የሰፈሩ ሲሆኑ የወቅቱን ሁኔታ የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡     መልካሙን ዘመን ያምጣልን፡፡

       ዲሞክራሲን ከ”ብላክማርኬት” እያፈላለግሁ ነው
 ምሁሩ የቢዝነስ ሰው አቶ ክቡር ገና፤ በወቅታዊ ችግሮቻችን ዙሪያ ሲናገሩ፡- “ህገመንግስት ለሰው ይሰራል እንጂ ሰው ለህገመንግስት አይሰራም።” ብለው ነበር፡፡ ትክክል!!  ባልታደለች አገርና ባልታደለ ህዝብ ውስጥ ግን በተቃራኒው ነው፡፡
እኛ አገር ከሰው ህይወትና ከህገ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠው ለህገ መንግስት ነው፡፡ የህገ መንግስቱ መሰረታዊ ዓላማ ግን ህይወትን መጠበቅ፣ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ነው፡፡ ለህይወት ክብርና ነጻነትን ማጎናጸፍ!!
 የጸረ-ሽብር ህጉስ? እሱም ቢሆን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት፣ ከአሸባሪዎች ጥቃት ብቻ ሳይሆን ስጋት ጭምር ማዳን ነው፡፡ እኛ አገር ግን ራሱ የሽብርና የፍርሃት ምንጫችን ሆኖ አረፈው፡፡ ገና ስንሰማው በፍርሃት የሚያርደን፡፡ (ስንቱ በሽብር ወንጀል ተከሶ፣ ወህኒ እንደወረደ ልብ ይሏል!)
 ምርጫስ? የሰለጠኑ ህዝቦች መሪዎቻቸውን በድምጻቸው የሚመርጡበት፣ የሚያወርዱበት፣ አንዳንዴም የሚቀጡበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ለእኛስ? አገር በፍርሃት ቆፈን የምትያዝበት፣ ተቃዋሚዎች የሚታደኑበት፣ ምርጫ ቦርድ ሆደ ሰፊነቱን የሚያውጅበት፣ የግል ሚዲያዎች የሚከሰሱበት፣ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች ለስደት “የማርያም መንገድ” የሚያገኙበት፣ በምርጫ ተጭበርብሯል ውዝግብ፣ ድምጽ የሰጠ የዋህ ህዝብ የሚሞትበትና “ግድያው ተመጣጣኝ መሆኑ” የሚጣራበት----የሰቀቀን ወቅት!!
ዲሞክራሲ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብና የመደራጀት፣ ተቃዋሚ ፓርቲ አቋቁሞ መንግስትን ለስልጣን መፎካከር፣ ነጻ ሚዲያ መስርቶ ነጻ መረጃ ብቻ ሳይሆን ነጻ ሃሳብን፣ ነጻ መንፈስን፣ ለህዝቡ ማድረስ --- ማቀበል!!! ሁሉም የሰው ልጆች ተፈጥሯአዊ መብቶች በመሆናቸው ቅዱስ ናቸው፡፡ በትክክል ሲተገበሩም ትርጉም ያለው ሙሉ ህይወት ያጎናጽፋሉ፡፡ የደስታና የእርካታ ምንጭ ይሆናሉ፡፡ ለሰለጠኑ ህዝቦችና አገራት!!!
 እኛ አገር ግን አደባባይ ወጥቶ በደልን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን---- መጠየቅ በራሱ ህይወት ያስከፍላል፡፡ ዋጋው  አይቀመስም፡፡ መስዋዕትነቱ ብዙ ነው፡፡
...አትሌት ሃይሌ፤ “ዲሞክራሲ ለአፍሪካውያን ቅንጦት ነው” ብሎ ተናገረ ብለን እንደ ጉድ ስንወርድበት ነበር፡፡ ግን እውነቱን ነው፡፡ የዲሞክራሲ ዋጋው ህይወት ነው፡፡ በተለይ በጦቢያ!
 የእብድ ሃሳብ ቢመስልም፤ አንዳንዴ ለምን ቅንጥር አይልም እላለሁ - ዲሞክራሲ!!!  
(እናላችሁ ዲሞክራሲ ከ”ብላክማርኬት” እያፈላለግሁ ነው!!)
*   *   *
ሳልፈልግ ተስፋ ቆረጥኩ!!!
...በአገራችን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ዕውቅ የጦቢያ ምሁራንና አንጋፋ ፖለቲከኞች (በ93 የክፍፍሉ ወቅት ከኢህአዴግ የተባረሩ የቀድሞ ታጋዮችን ጨምሮ) እየሰጡት ያለውን የመፍትሄ ሃሳቦች ስትመለከቱ፤ ሁሉም ማለት ይቻላል መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ እንዳለበት የሚያሳስቡ ናቸው፡፡  
..ከወትሮው በተለየ የህዝቡ ተቃውሞና ዘርፈ-ብዙ የመብት ጥያቄዎች የማያፈናፍኑ መስለው ስለታዩኝ፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም፣ ለማንም ብሎ ሳይሆን ለራሱ ሲል የመፍትሄ ሃሳቦቹን ይቀበላል የሚል ጽኑ እምነትና ተስፋ ነበረኝ፡፡ (ምኞትና ቅዠት ቅልቅል ሳይሆን አይቀርም!!)
.ከዚህም በመነሳት በጣም በቅርቡ አገሪቱ በፓርቲዎች ውይይት ትጥለቀለቃለች ብዬ ቋምጬ ነበር፡፡ ለኢህአዴግም ሆነ በቀጣይ ሥልጣን ላይ ለሚወጣ ፓርቲም ችግሮችን በሃይል ሳይሆን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጀመር የአሁኑ ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን ተስፋ መሰነቄ አልቀረም፡፡
.ይሄ ሁሉ የግል ቅዠቴ መሆኑ የገባኝ የኢህአዴግን የሰሞኑን መግለጫ ስሰማ ነው፡፡
ትላንት ምሽት በኢቢሲ የሰማሁት የጠ/ሚኒስትሩ መግለጫ ግን የፍርሃት ቆፈን አስያዘኝ። በበርካታ ውይይቶች መፍትሄና እልባት ያገኛል ብዬ ያሰብኩት ፖለቲካዊ ቀውስ፣ በሃይል (ያውም በመከላከያ)  እንደሚፈታ ስሰማ ተስፋ ቆረጥኩ። በጠ/ሚኒስትሩ ወይም በኢህአዴግ አይደለም (ጦሳቸውን!)
ተስፋ የቆረጥኩት በአገሬ ነው፡፡ ተስፋ የቆረጥኩት ላለፉት 40 ዓመታት ከኋላቀርነት ድቅድቅ ጨለማ መውጣት ለተሳነው ፖለቲካችን ነው፡፡ ተስፋ የቆረጥኩት ----- ላልሰለጠነው የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡
በአመጽና በግጭት ሲታመሱ የሰነበቱ ከተሞችና ወረዳዎች ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሲባል የሚገደሉ፣ በጅምላ የሚታሰሩና የሚዋከቡ ዜጎችን ሳስብ-----የፍርሃት ቆፈን ይጨመድደኛል፡፡ ቅስሜ ይሰበራል፡፡ ጭንቀት ይውጠኛል፡፡ ወገኖቻችንን ከሞት የመታደጊያ አቅም ወይም መፍትሄ ስለሌለኝ (ን) ቁጭት ያንገበግበኛል፡፡
ግን ደግሞ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ እስከ ዛሬ የኖሩት፣ በኛ ዕውቀትና ጥበብ ሳይሆን በዓምላክ ኪነጥበብ- በእሱ ተዓምር መሆኑን አስብና ራሴን ከጭንቀት አወጣለሁ፡፡ እፎይ እላለሁ፡፡
(ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከመከራ ይጠብቃቸው!!)
*   *   *
መፍጠን አለብን፤ ጊዜ የለንም
የአገራችን አስፈሪ የፖለቲካ ቀውስ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን በእጅጉ ያሰጋል፡፡ እንደ እስከ ዛሬው እጃችንን አጣምረን ከተቀመጥን ደግሞ ከቁጥጥር ውጭ የማይሆንበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለም፡፡ መቼም ለዘመናዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንግዳ ብንሆንም እንኳን ዕድሜ ጠገብ የእርቅና ሽምግልና ባህል ሞልቶናል፡፡ ንቀን ገፍተነው እንጂ፡፡
ከገባንበት ቀውስ ለመውጣት የሚያግዙን ብዙ አማራጭ ሃሳቦች የሚያቀርቡልን ምሁራንም ችግር ያለብን አይመስለኝም፡፡ በፍረጃና ጆሮ በመንፈግ አግልለናቸው እንጂ፡፡
.ባለቤት የሌለው ህዝባዊ ተቃውሞና አመጽ ወደ እልቂት እንደሚያመራ ቀድመን ብናውቅ ኖሮም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አማርረንና አዋክበን አናዳክማቸውም ነበር፡፡
የዚህ ሁሉ ችግራችን መንስኤው አርቆ አለማሰብ ነው፡፡ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ከግምት ውስጥ አለማስገባታችን ነው፡፡ ከሥልጣንና ከጥቅም ባሻገር አገርንና ትውልድን ማሰብ አለመቻላችንም ነው፡፡
.አሁንም ቢሆን በቀረችው እንጥፍጣፊ ጊዜ የበኩላችንን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የተጋፈጥነው ችግር ኢህአዴግ እንደ ፍጥርጥሩ ይወጣው የምንለው አይደለም፡፡ ተባብረንም ከተሳካልን ዕድለኞች ነን፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦች አለን የምንል ዜጎች፤ እስክንጠየቅ ወይ እስክንጋበዝ ሳንጠብቅ፣ መፍትሄዎቻችንን  ለማጋራት ልንተጋ ይገባናል፡፡ መንግስትም የማነው፣ ከየት ነው ሳይል፣ ለመፍትሄ ሃሳቦች ልብና ጆሮውን ሰጥቶ በአፋጣኝ ወደ ተግባር መግባት ይኖርበታል፡፡ ወደ መፍትሄ!!!
ግን መፍጠን አለብን፡፡ ጊዜ የለንም፡፡ በከንቱ ያሳለፍነው ጊዜ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡
*   *   *
ጭንቀት የወለደው ----
ዝም ብዬ ሲጨንቀኝ ያወረድኩት ሃሳብ ነው፡፡ ጭራና ቀንድ ይኑረው አይኑረው አላውቅም፡፡ ማሰብ ጨርሼ አይደለም መጻፍ የጀመርኩት፡፡ ብለው ብለው አልጨበጥ፤ አልሰበሰብ አለኝ - ሃሳቡ፡፡ ግን ደግሞ ጭንቅላቴ ውስጥ ያልተያያዙ ብዙ ሃሳቦች አፍነው ያዙኝ፡፡ ስለዚህ እንደ ምንም ተንፍሼው መገላገል ፈለግሁ፡፡ ሸክሙን ለሌሎች ማከፋፈል ሳይሻል አይቀርም፡፡
አንዳንዴ ለብቻ ከመብሰክሰክ በደቦ ማሰብ ብንችል ጥሩ ነበር - እየተጋገዝን፡፡ ለማንኛውም እየጻፍኩ ማሰቤን ቀጥያለሁ፡፡ ቀጣዩ ሃሳብ የሚመጣልኝ የቀደመውን በዓረፍተ ነገር አስፍሬ፣ በአራት ነጥብ ከከረቸምኩ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ እያለሁ የጽሁፍህ ዓላማ ምንድን ነው ብትሉኝ ግን እቀየማችኋለሁ፡፡ አላውቀውማ!!!
.ውስብስብ ብሎ ያስቸገረኝ አገሬ ያለችበት የተወሳሰበ ሁኔታ ነው፡፡ ቋጠሮው የቱ ጋ እንዳለ አይታወቅም፡፡ ጭንቀቴ በዝቶ ወደ ፍርሃት ደረጃ ሲያድግ ይሰማኛል፡፡ በየቀኑ ችግሮች ሲባባሱ እንጂ ሲቃለሉ አላይም፡፡ ከዚህ በላይ ምን ሊያስጨንቀኝ ይችላል?!
*   *   *
ኢቢሲና የሉሲ አሟሟት?!
ሉሲ ከዛፍ ላይ ወድቃ መሞቷ መረጋገጡን የሚያበስረውን የኢቢሲ ዜና ሰምቼ ተገረምኩ፡፡ ያስገረመኝ እንደ ዜና መቅረቡ አይደለም፡፡ የዕለቱ የዜና መክፈቻ መሆኑ እንጂ፡፡ በየቀኑ በተቃውሞና በግጭት እየተናጠች ለምትገኝ ያልታደለች አገር፤ የሉሲ የሞት መንስኤ በምን መመዘኛ የዜና መክፈቻ ሊሆን ይችላል? በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ በሚከሰቱ ግጭቶች የሚሞቱ ሰዎች ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል እንጂ እንዴት የሉሲ አሟሟት ዋነኛ ጉዳያችን ይሆናል?
 ግን መቼ ነው ኢቢሲ ወቅታዊ ሆኖ ከወቅቱ ጋር መራመድ የሚጀምረው?! ይሄ እኮ ወቅታዊ አለመሆን ብቻ ሳይሆን እውነታውን መካድ ጭምር ነው!!! ከዚያም በላይ ግን ለህዝብ ወገንተኛ አለመሆን ነው። (ኢህአዴግም ራሱ ኢቢሲን ለህዝብ ወገንተኛ ባለመሆን ይተቸዋል እኮ!) ራሱ ኢህአዴግስ ------ ለህዝብ ወገንተኛ ነኝ ይለን ይሆን? (በጄ የሚለው ካገኘ መድፈሩ አይቀርም!)
*   *   *
እባካችሁ ነገ እንዳይጸጽተን!!!
ሰዎች አሁን ትንሽ ሰከን ብሎ ማሰብ የሚያስፈልገን ይመስለኛል፡፡ ማናቸውንም የተጓደለብንን መብቶች መጠየቅና ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ መንግስታዊ አሰራሮችን መቃወም፣ ብሎም የሥርዓት ለውጥ መጠየቅ- ማንም የማይሰጠን - ማንም የማይነሳን ህገ-መንግስታዊ መብቶቻችን ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው እኒህን የመብት ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ተከትለው ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለእስርና ለወከባ መዳረጋቸው ብቻ ነው፡፡
አሁን ደግሞ የከፋ ወሬ እየሰማን ነው፡፡ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡ የፈራነው ባልተጠበቀ ፍጥነት ደረሰ ማለት ነው!? እንኳን ድርጊቱ ሃሳቡ የሚሰቀጥጥ አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ ለዘመናት በፍቅር አብሮ ብዙ መከራና ደስታ ካሳለፈ ደግና ጨዋ ህዝብ የማይጠበቅ የሰይጣን ሥራ ነው፡፡ ለምንሳሳለት ኢትዮጵያዊነታችንና ለአኩሪ የነጻነት ባህላችን ፈጽሞ የማይመጥን አስከፊ ድርጊት ነው፡፡
መንግስታት ሃላፊዎች ናቸው፤ ዘላለም አይኖሩም፡፡ ህዝቦች ግን ሁሌም ኗሪ ናቸው፡፡  
እባካችሁ ---- ሌላው ባይሆንልን እንኳን ለአዲሱ ትውልድ ደም የተቃቡና ቂም የቋጠሩ ህዝቦች ትተንላቸው አንለፍ፡፡ በኋላ ከሚቆጨን ዛሬ - አሁን ከስሜታዊነት ወጥተን፣ ትንሽ ሰከን ብለን እናስብ። እባካችሁ አስሬ ስሟን የምንጠራትን አገራችንን ከእልቂትና ከጥፋት እናድናት!! ከአስነዋሪና ከአስከፊ ታሪክ እንታደጋት!! ልብ አድርጉ - ማንንም ከተጠያቂነት አይድንም!!
(ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይጠብቃት!!!)

Read 10029 times