Wednesday, 04 April 2012 08:11

ወሲብ ለተሳናቸው “ልዩ ህክምና” እሰጣለሁ የሚለው ድርጅት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(101 votes)

* ህክምናው  ከ3ሺ - 4ሺ ብር ክፍያ ይጠይቃል

በአብዛኛው ወደ እኛ ተቋም የሚመጡ ሰዎች ችግራቸውን የፍቅር አጋሮቻቸው እንዲያውቁባቸው አይፈልጉም፡፡ ሚስት/ባል የችግሩ ተጠቂ ሆነው ሲመጡ፣ የመጣውን አካል አሰልጥኖ የፍቅር አጋሩን እንዲረዳና ከችግራቸው እንዲላቀቁ እንዲያደርግ እንመክራለን፡፡ የባልና ሚስት ተማምኖና ተስማምቶ ወደ እኛ መምጣት የእኛንም ሥራ ያቃልልናል፡፡ ግን በአብዛኛው ይህ አይሆንም፡፡ ሁለቱም ወገኖች አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡት በየግላቸው ነው፡፡ ሚስቴ እንድታውቅብኝ አልፈልግም፤ ባሌ እንዲያውቅ አልፈቅድም ይላሉ፡፡ ስለዚህም ያው በግድ ህክምናውን ማግኘት ካለባቸው ሊያገኙ የሚችሉት በእኛ ባለሙያዎች ነው፡፡ ባለሙያዎቹ እንደአስፈላጊነቱ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡

የሰው ልጅ ከታደላቸው ተፈጥሮአዊ ፀጋዎች አንዱ የወሲብ እርካታ ነው፡፡ ማንኛውም ጤናማ ሰው ይህንን የተፈጥሮ ፀጋ ታድሏል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ተፈጥሮአዊ ፀጋ በተለያዩ ምክንያቶች ሊጓደል ወይንም ጨርሶውኑ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ይህ ችግርም “ስንፈተ ወሲብ” በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡  የዚህ ችግር ተጠቂ የሆነ ሰው ከአካላዊ ጉዳቱ ይልቅ ሥነልቡናዊ ጉዳቱ ስለሚያይል በህይወቱ ፍፁም ደስተኛ አይሆንም፡፡ በዚህ ምክንያትም ህይወቱን ጐደሎ ያደረገበትን ልዩ ደስታ ለማግኘት የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይገባበት ጉድጓድ አይኖርም፡፡ ቴክኖሎጂ ምሥጋና ይግባውና ዛሬ እነዚህን ችግሮች ለማቃለልና ለማስወገድ የሚረዱ የተለያዩ መድሃኒቶችና ህክምናዎች በዓለማችን በስፋት ይሰጣሉ፡፡ ከእነዚህ በተለየ መንገድ ወሲብ ለተሳነናቸው ሰዎች “ልዩ ህክምና” በመስጠት ከችግራቸው እንዲላቀቁና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ እየሰራሁ ነው የሚል አንድ ድርጅት መኖሩን ሰማንና ከድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ቀጠሮ ያዝን፡፡

የድርጅታችሁ መጠሪያ ምንድነው? ምንስ አገልግሎት ይሰጣል?

ድርጅቱ “ዲና የስንፈተ ወሲብ ህክምና ማዕከል” በመባል ይጠራል፡ በድርጅቱ የሚሰጠው አገልግሎትም የስንፈተ ወሲብ ችግር ላለባቸው ሰዎች በረዳት “የወሲብ ሐኪሞች” አማካኝነት እየታገዙ ከችግራቸው እንዲላቀቁ መርዳት ነው፡፡

ስንፈተ ወሲብ የብዙ ችግሮች መንስኤ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ለትዳር መፍረስና ለቤተሰብ መበተን ሁሉ ሊዳርግ ይችላል፡፡ የሚያስከትላቸው ችግሮች ውስብስብ ናቸው፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ችግራቸውን የሚረዳላቸው፣ የሚከታተላቸውና እርዳታ የሚያደርግላቸው ሰዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ማግኘት ደግሞ በቀላሉ አይቻልም፡፡ ይህ የእኛ ድርጅት ለዚህ ችግር መፍትሔ ይሰጣል፡፡

የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ችግራቸው መፍትሔ እስከሚያገኝና ከችግራቸው ተላቀው ሰላማዊ ህይወታቸውን እስከሚመሩ ድረስ የቅርብ ክትትል የሚያደርጉላቸውና የሚንከባከቧቸው ባለሙያዎች በመመደብ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡

ይህን “የህክምና ዘዴ” ለመስጠት እንዴት አሰባችሁ

(ምን አነሳሳችሁ?)

ህክምናው አዲስ አይደለም፤ የወሲብ ህክምናን በረዳት የወሲብ ሐኪም መስጠት የተጀመረው በአሜሪካ አገር ሲሆን ማስተርስና ጆንሰን የተባሉ ሁለት ባለሙያዎች በ1957 ዓ.ም የጀመሩት የህክምና ጥበብ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የወሲብ ችግሮች በስነልቡና ህክምና ብቻ ሊወገዱ አለመቻላቸውን በመገንዘባቸው፣ የተሻለ የህክምና ጥበብ መጠቀም ጀመሩ፡፡ ይህም ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ማስቻሉን ሲረዱ ሥራውን በስፋት ተያያዙት፡፡ እዚህ በአገራችንም የስንፈተ ወሲብ ችግር ለበርካታ ትዳሮች መፍረስ ምክንያት ሆኗል፡፡

በየክልሎች እየተዘዋወርኩ አንዳንድ ጥናቶችን ለማድረግ በሞከርኩባቸው ጊዜያትም ያየሁት ይህንኑ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሥነልቡና ህክምናና በባህላዊ መድሀኒቶች ውጤት ባለማግኘታቸው፣ ከዚህ ከተለመደው የወሲብ ህክምና ለየት ባለ መንገድ እርዳታ የሚያገኙበት መንገድን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ በሁለቱ አሜሪካውያን የሚሰጠው አገልግሎት የተሻለ ውጤት እንዳለው በመረዳቴም “ህክምናውን” በአገራችን ለመጀመር ወሰንኩ፡፡

“ህክምናው” ምን ዓይነት ህክምና ነው?

ይህ በወሲባዊ ችግሮች ዙሪያ የሚሰጠው ህክምና እንደ ችግሩ ዓይነት እየተለየ የሚሰጥ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የስንፈተ ወሲብ ችግር ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉት፡፡ እነሱም፡- አካላዊና ስነልቡናዊ ችግሮች ናቸው፡፡ አካላዊ የሚባሉት በወሲብ መፈፀሚያ አካላት ላይ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ምክንያቶች በሚደርሱ ጉድለቶች የሚከሰት ችግር ሲሆን፤ ሥነ ልቡናዊ የሚባለው ደግሞ ከልጅነት አስተዳደግ ጀምሮ ለተቃራኒ ፆታ ባለ አመለካከት፣ ከፍርሃት፣ ራስን አሳንሶ ከማየት፣ በመሳሰሉ ምክንያቶች የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ የእኛ ድርጅት አካላዊ የጤና ችግሮች ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት አይችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ችግሮቻቸው በህክምና ዘዴ ሊስተካከል ወደሚችልበት የህክምና ተቋም እንልካቸዋለን፡፡

ወደተቋማችን የሚመጡትን አገልግሎት ፈላጊዎች በመጀመሪያ የምናደርገውም ይህንኑ ነው ችግሩ አካላዊ ነው ስነልቡናዊ የሚለውን መለየት ማለት ነው፡፡ የሰውየው/የሴትየዋ ችግር ሥነልቡናዊ መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ሙሉ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ እናደርጋለን፡፡

ምን ዓይነት የጤና ምራመራ ነው የሚደረገው?

በእኛ የህክምና ተቋም ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት የሚችሉት ሙሉ ጤናማ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ተላላፊ የሆኑና የማይተላለፉ በሽታዎች መኖር ያለመኖራቸው በህክምና እንዲረጋገጥ ያደርጋል፡፡

በሽታ ቢኖርባቸውስ?

ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ማለትም ኤችአይቪን ጨምሮ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ካሉ በእኛ ተቋም አገልግሎት አያገኙም፡፡ የማይተላለፉ በሽታዎች ላይ ግን ያሉበትን ደረጃዎችና የሰውየውን ሁኔታ በማየት አገልግሎቱን እንዲያገኝ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡

የእናንተ ሠራተኞችስ የጤና ምርመራ ያደርጋሉ?

አዎ በየሶስት ወሩ ተከታታይ የጤና ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡

ቀጣዩ ሂደትስ ምንድነው?

ታካሚው የጤና ምርመራውን ሲያጠናቅቅ ስለ ህክምናው ሙሉ ገለፃ ይደረግለታል፡፡

ህክምናው ምን ምንን እንደሚያካትት ከእሱ የሚጠበቀው ምን እንደሆነ ይነገረዋል፡፡ በዚህ ከተስማማና ህክምናውን ለመቀጠል ከፈለገ፣ ለዚሁ ሥራ ከተመደበችለት ባለሙያ ጋር እንዲገናኝ ይደረግና ህክምናውን ይጀምራል፡፡

ህክምናው ምን ምን ደረጃዎች አሉት?

ወደ ስምንት የሚደርሱ ደረጃዎች አሉት፡፡ እነዚህን የህክምና ደረጃዎች ባለሙያዋ ከታካሚው ጋር በመስማማትና በፍላጐት ይፈጽሙታል፡፡ የህክምና ደረጃዎቹ በትክክለኛው መንገድና በቅደም ተከተል መከወን ይኖርባቸዋል፡፡ እያንዳንዳቸው የተለየ ስሜትና አፀፋዊ ምላሽ አላቸው፡፡ ከዚህ የህክምና ደረጃ ቀዳሚው የእጅ ዳሰሳ የተሰኘው ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እጅ ከተለመደው ሥራ ውጪ ሌላ አገልግሎት አለው ብለው አያስቡም፡፡ እጅ ግን ትልቅ የስሜት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የሰውነታችን አካል ነው፡፡

ከዚያ በመቀጠል የፊት ዳሰሳ፣ የሰውነት ዳሰሳ፣ የውስጥ እግር እሽታ፣ ገላን መቃኘት በእምብርት ዙሪያ የሚደረግ እሽታ፣ በጀርባ አከርካሪ በኩል የሚደረግ እሽታ አሉ፡፡

እነዚህ እሽታዎች በተለያዩና ለዚሁ ተግባር በተዘጋጁ የቅባት አይነቶች ይከወናሉ፡፡ እነዚህን ሰባት የእሽታ ደረጃዎችን በአግባቡ ያጠናቀቀ ታካሚ የመጨረሻውንና መዳኑ የሚረጋገጥበትን የወሲብ ተግባር ይፈጽማል፡፡ በዚህ የህክምና ጥበብ ከ70% - 80% ታካሚው ከነበረበት ችግር ይላቀቃል የሚል እምነት አለን፡፡

ታካሚው ባለትዳር/ፍቅረኛ ያለው ከሆነ ህክምናውን ካገኘ በኋላ የመጨረሻውን ደረጃ ከራሱ አጋር ጋር እንዲፈጽም የምታደርጉበት መንገድ የለም?

ይህ እንዲሆን እናበረታታለን፡፡ ግን በአብዛኛው ወደ እኛ ተቋም የሚመጡ ሰዎች ችግራቸውን የፍቅር አጋሮቻቸው እንዲያውቁባቸው አይፈልጉም፡፡ ሚስት/ባል የችግሩ ተጠቂ ሆነው ሲመጡ፣ የመጣውን አካል አሰልጥኖ የፍቅር አጋሩን እንዲረዳና ከችግራቸው እንዲላቀቁ እንዲያደርግ እንመክራለን፡፡ የባልና ሚስት ተማምኖና ተስማምቶ ወደ እኛ መምጣት የእኛንም ሥራ ያቃልልናል፡፡ ግን በአብዛኛው ይህ አይሆንም፡፡

ሁለቱም ወገኖች አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡት በየግላቸው ነው፡፡ ሚስቴ እንድታውቅብኝ አልፈልግም፤ ባሌ እንዲያውቅ አልፈቅድም ይላሉ፡፡ ስለዚህም ያው በግድ ህክምናውን ማግኘት ካለባቸው ሊያገኙ የሚችሉት በእኛ ባለሙያዎች ነው፡፡ ባለሙያዎቹ እንደአስፈላጊነቱ አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ የሰውየው መዳን እስከተፈለገ ድረስ፣ ባለሙያዋ ወሲብ መፈፀምንም ጨምሮ ሁሉንም አይነት የህክምና ጥበብ በመጠቀም ታካሚው ከችግሩ እንዲላቀቅ ታደርገዋለች፡፡

ወደተቋማችሁ የሚመጡ ሴት አገልግሎት ፈላጊዎች አሉ?

አዎ አሉ፡፡ የስንፈተ ወሲብ ችግር ቀደም ሲል የወንዱ ችግር እንደሆነ ብቻ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ያ አስተሳሰብ ቀርቷል፡፡ ሴቶችም ህክምናውን ለማግኘት ወደ እኛ ይመጣሉ፡፡ ስለ ሕክምና አሰጣጡ ስንነግራቸው አንዳንዶቹ እንዲህ አይነት ህክምና መውሰድ አንፈልግም ብለው የሚሄዱ አሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ የምክር አገልግሎት ተሰጥቶአቸው ስለችግራቸው ከባለሙያ ጋር ተመካክረውና መፍትሔ የሚሆን ነገር አግኝተው ይመለሳሉ፡፡

ይህ “የህክምና ጥበብ” ባለትዳሮች ከትዳራቸው ውጪ ወሲብ እንዲፈጽሙ በማድረግ ዝሙትን የማስፋፋት ሥራ በይፋ እየሰራ ነው ለማለት አያስችለንም?

በፍፁም እንደዛ ማለት አንችልም፡፡ ቀድሞውንም ታካሚው ወደተቋማችን ሲመጣ የጀርባ ታሪኩን በደንብ አጥንተን ባለትዳር ከሆነ ወይም ፍቅረኛ ካለው ከፍቅር አጋሩ ጋር  እንዲመጣ ተገቢ ምክር እንሰጠዋለን፡፡ ለዚህ ፍቃደኛ ሳይሆን ከቀረ ግን ታካሚው ከያዘው ችግር መላቀቅ ይገባዋል ብለን ስለምናምን ህክምናውን እንዲያገኝ እናደርገዋለን፡፡

ህክምናው ከባህልና ከሥነምግባር አንፃርስ ምን ያህል ተቀባይነት አለው ብለህ ታምናለህ? ወደተቋማችሁ የሚመጡ ታካሚዎችስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ስሜት አላቸው?

ማህበረሰቡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ለመቀበል ከዚህ ቀደም እምብዛም ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ አሁን አሁን ግን ትልቅ ለውጥ አለ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የተሳሳተ እምነትና አመለካከት ይዘው ወደተቋማችን የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ገና እንደመጡ ቀበቶአችንን እንፍታ የሚሉ አይነት ማለት ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ችግር ኖሮበት ሲመጣ፣ ለችግሩ ቋሚ መፍትሔ አግኝቶ ከችግሩ ተላቆ መሄድ ስላለበት ትእግስትና ፍቃደኝነት ይጠበቅበታል፡፡

በአንድ ጉዳይ ላይ መተማመን አለብን፡፡ ማንኛውም ሰው የወሲባዊ ችግር ካለበት ማንኛውንም አይነት መፍትሔ ከመወሰድ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ወግ፣ ባህል፣ ሥነምግባር ስለሚባሉ ጉዳዮችም ብዙ አይጨነቅም፡፡

ምክንያቱም ወሲብ የህይወቱ ትልቅ ምዕራፍ ሆኖ እያለ፣ ይህንን ነገር በአግባቡ መፈፀም ሳይችል ሲቀር ጤናማ የሆነ ህይወት ይኖረዋል ብሎ ማሰቡ ይከብዳል፡፡ ሆኖም በአንድ ጊዜ ይቀበለዋል ወይንም ሙሉ በሙሉ ተቀብሎታል ማለትም አይቻልም፡፡

አገልግሎቱን የሚሰጡ ምን ያህል “ባለሙያዎች” አሉ? የተመረጡበት መስፈርትስ ምንድነው? ክፍያቸውስ? የዕድሜ መጠናቸውስ ምን ያህል ነው?

በአሁኑ ወቅት በህክምና ተቋማችን ይህንን የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ አራት የሴትና ሁለት የወንድ ባለሙያዎች አሉን፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ከተመረጡባቸው መስፈርቶች ዋንኛውና የመጀመሪያው የሰዎችን የወሲብ ችግር ለመረዳትና ከችግራቸው ለማውጣት ታላቅ ፍላጐትና ቁርጠኝነት መኖር ነው፡፡ ጤናማ የሆነና የተስተካከለ ቁመናና ገጽታም ከመስፈርቶቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ ጥሩ ባህርይ ያላቸው፣ ተግባቢ የሆኑ፣ ሰዎችን የመቀበል፣ የማክበርና ከሰዎች ጋር የመግባባት ባህርያቸው ጥሩ የሆነ ልጆችን እንመርጣለን፡፡ ዕድሜያቸውን በተመለከተ ከ24 እስከ 30 የሚደርሱ ወጣቶች ናቸው፡፡ በነርስ ሙያ የተመረቁ፣ በማሳጅ ቴራ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም አሉበት፡፡ እነዚህ ቋሟ ባለሙያዎቻችን በወር 1700 ብር ደመወዝ ይከፈላቸዋል፡፡ አገልግሎቱን በሚሰጡበት ወቅት ደግሞ የሚሰጣቸው የኮሚሽን ክፍያ አለ፡፡

አገልግሎቱን የምትሰጡት በምን አይነት ቤቶች ነው?

ለዚሁ አገልግሎት የተዘጋጁ ቤቶች አሉን፡፡ ታካሚው ህክምናውን ሲከታተል ልክ በቤቱ ውስጥ እንዳለ እንዲሰማውና የእንግድነት ስሜቱን ለማስወገድ ሲባል የሚዘጋጁለት ነገሮች አሉ፡፡ ግን በይፋ የወሲባዊ ችግር ህክምና ተቋም ብለን የምንሰራው ሥራ የለም፤  ምክንያቱም ሰዎች ሳይሸማቀቁ ወደ እኛ መጥተው እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው፡፡

የአገልግሎቱን ፈላጊዎች ከየት ታገኟቸዋላችሁ?

በተለያዩ መንገዶች እናገኛቸዋለን፡፡

ከችግሩ ተጠቂዎች እርስበርስ ውይይት ስለጉዳዩ ሰምተው፣ ወደ እኛ የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎችና ትላልቅ ክሊኒኮችም ወደ እኛ የሚላኩ ሰዎች አሉ፡፡

በእናንተ ተቋም ሕክምና አግኝተው ከችግራቸው ተላቀው ከሄዱ በኋላ ችግሩ ተመልሶ የመጣባቸው ሰዎች የሉም? ችግሩ ዳግመኛ የመመለስ ባህርይ የለውም?

ችግሩ የመመላለስ ባህርይ የለውም፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ የነበረ ሰው፣ ከችግሩ ሲላቀቅ ችግሩ ዳግመኛ እንዳይገጥመው በማድረጉ በኩል የእሱም ሃላፊነት አለበት፡፡ ካለበት ችግር መውጣት እንዳለበት ራሱን ማሳመን ይኖርበታል፡፡

ታካሚው ለዚህ አገልግሎት ምን ያህል ይከፍላል? የሚፈጅበትስ ጊዜ ምን ያህል ነው?

ክፍያው ችግሩ እንደሚወስደው የጊዜ መጠን ይወሰናል፡፡ በአጭር ጊዜ ከችግሩ ለመላቀቅ የቻለ ሰው እስከ 3 ሺህ ብር የሚደርስ ክፍያ የሚከፍል ሲሆን ህክምናው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ ከ4ሺህ ብር በላይ ሊከፍል የሚችልበት ሁኔታም አለ፡፡

አጭር ጊዜ ስንል ምን ያህል ነው? ረጅሙስ?

አጭር ጊዜ ስንል በአንድ ወር ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ የሚሻሻል ሲሆን ረጅሙ እስከ ሶስት ወር የሚደርስ ነው፡፡

ለስንፈተ ወሲብ ችግሮች የሚሰጡ መድሃኒቶች በአነስተኛ ዋጋ እንደልብ በሚገኙበት በዚህ ዘመን የናንተ ክፍያ ተወደደ የሚሉ አልገጠሟችሁም?

በእርግጥ ቪያግራንና ሌሎች ለስንፈተ ወሲብ የሚረዱ መድሀኒቶችን በአነስተኛ ዋጋ እንደልብ ለማግኘት ይቻላል፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች በሰውየው ላይ የሚያስከትሉት የጐንዮሽ ችግርና የሥነ ልቡና ችግሮች እንዳሉ ሆነው የሚሰጡትም መፍትሔ ጊዜያዊ ነው፡፡ ይህ ከእኛ ሕክምና ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም፡፡ የእኛ መፍትሔ ዘላቂነት ያለው፣ የጐንዮሽ ጉዳት የሌለውና በጥንቃቄ ከተከወነም ሙሉ በሙሉ ከችግሩ የሚያላቅቅ መፍትሔ ነው፡፡

አገልግሎታችሁ በመንግስታዊ ተቋማትና ድርጅቶች ይታወቃል?

አሁን እነሱን ነገሮች እያከናወንን ነው ያለነው፡፡ ስለአገልግሎታችን በስፋት ለማስታወቅና ከመንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አገልግሎታችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች መዳረስ አለበት የሚል እምነት ስላለንም በዚህ ጉዳይ ላይ ድጋፍ የሚያደርግልን አካል በማፈላለግ ወደየክልሎችም የመሄድ እቅድ አለን፡፡

እስከዛሬ የአገልግሎታችሁ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ምን ያህል ናቸው?

አገልግሎታችንን አግኝተውና ከያዛቸው ችግር ሙሉ በሙሉ ተላቀው የሄዱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ አሁንም አገልግሎቱ እየተሰጣቸው ያሉ ሰዎች አሉ፡፡

 

 

 

Read 38172 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:45