Saturday, 25 March 2017 12:38

የክብር ዶክትሬት ጥያቄ?!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  አንድ ባለጸጋ በአካባቢያቸው ወደሚገኝ አንድ ኮሌጅ ጎራ ይሉና ለተቋሙ 1ሚ.ብር ለመለገስ እንደሚሹ ይናገራሉ፡፡ “ነገር ግን በአንድ ቅድመ-ሁኔታ ነው÷ ይኸውም የክብር ዶክትሬት የሚሰጠኝ ከሆነ ነው” ይላሉ፡፡
የኮሌጁ ፕሬዚዳንትም፤ “ታዲያ ምን ችግር አለ፤ ይሰጥዎታላ” ይላቸዋል፡፡
 “የክብር ዶክትሬቱ ግን ለአህያዬ ነው” አሉ፤ ባለጸጋው፡፡
ፕሬዚዳንቱ በድንጋጤና በአግራሞት መሃል ሆኖ፤ “ለአህያዬ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
ባለጸጋውም፤ “አዎ--- አህያዬ ለብዙ ዓመታት እኔን ተሸክማ ከቦታ ቦታ በመውሰድ ከባድ ውለታ አድርጋልኛለች፡፡ ለዚህም የትራንስፖርት የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣት እሻለሁ; በማለት ኮስተር ብለው አስረዱ፡፡
“ግን እኮ---- ኮሌጃችን ለአህያ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶ አያውቅም” አለ ፕሬዚዳንቱ፡፡
“እንግዲያውስ ገንዘቡን ለሌላ ተቋም እለግሰዋለሁ” አሉና ከመቀመጫቸው ተነሱ-ባለሃብቱ፡፡
ዓይኔ እያየ 1ሚ.ብር ሊያመልጠኝ ነው ብሎ ያሰበው ፕሬዚዳንት፤ “ቆይ እስቲ ከኮሌጁ ቦርድ ጋር ልማከርበት” ሲል ጥቂት ጊዜ እንዲሰጡት ይጠይቃል፡፡
ባለጸጋው፤ “በል በቶሎ አሳውቀኝ” ብለውት ይሄዳሉ፡፡
(በልባቸው “ብትማከር ነው የሚሻልህ” ሳይሉት አይቀሩም!)
ፕሬዚዳንቱ፤ ወዲያው የኮሌጁን ቦርድ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራና በጉዳዩ ላይ ውይይት ይጀምራሉ፡፡ ብዙዎቹ አባላት የገንዘቡ መጠን የፈለገውን ያህል ብዙ ቢሆን፣ ለአህያ የክብር ዶክትሬት አንሰጥም ብለው ተፈጠሙ፡፡
አንድ በኮሌጁ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ብልህ አዛውንት ግን ለፕሬዚዳንቱ የተለየ ሃሳብ አቀረቡ፡፡
“ገንዘቡን ተቀበልና ለአህያዋ የክብር ዶክትሬቱን ስጥ ባክህ; አሉት፡፡
ፕሬዚዳንቱም ደንገጥ ብሎ፤ “ይሄን ማድረግ ለኮሌጃችን ውርደት አይሆንም?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“በፍጹም አይሆንም; አሉ አዛውንቱ፤ “እንደውም ክብር ነው፤ ለምሉዕ አህያ የክብር ዶክትሬት ስንሰጥ በኮሌጁ ታሪክ የመጀመሪያችን ይሆናል!!”
(እስከዛሬ ድረስ ከአህያ ለማይሻሉ ሰዎች ስንሰጥ ከርመናል ማለታቸው ነው!!)

Read 1196 times