Monday, 27 March 2017 00:00

የትም እንደማላደርሳቸው ባውቅም እስላለሁ - ሰዓሊ እስራኤል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “ባለቤቴ ስዕል ሳልስል እንድውል፣ ተስፋ እንድቆርጥ በጭራሽ አትፈልግም

              ተወልዶ ያደገው መሀል ፒያሳ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ፊት ለፊት በሚገኘው አካባቢ ነው፡፡ አባቱ ነጋዴ የነበሩ ሲሆን የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ ጥሩ እንክብካቤ እየተደረገለት ማደጉን ይናገራል፡፡ የመዋዕለ ህፃናት ጊዜውን ባሳለፈበት ሊሴ ገ/ማሪያም ት/ቤት ስለተለያዩ ቀለማትና ስለ ስዕል ያለው እውቀትና ዝንባሌ መፈጠሩን ይገልፃል፤ሰዓሊ እስራኤል ወ/ሚካኤል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ስዕሎችን በመሳል ሀሳቡን፣ ስሜቱንና
ፍላጎቱን ይገልጻል፡፡ ሆኖም ከጊዜ በኋላ ባጋጠመው የአካል ጉዳት የተነሳ፣ ስዕሎቹ በቤት ውስጥ ተወስነው ተመልካች ሳያገኙ በዝናብና በአቧራ ለብልሽት መዳረጋቸው ያሳዝነዋል፡፡ የትም እንደማላደርሳቸው ባውቅም እስላለሁ - ይላል ሰዓሊ እስራኤል፡፡ ሰዓሊው እንዴት ለአካል ጉዳት ተዳረገ? አሁን ያለበት የኑሮ ሁኔታ ምን ይመስላል? ሳሎኑንና መኝታ ቤቱን የሞሉት አስደማሚ ስዕሎቹ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? በቀጣይስ ህልሙ ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በሰዓሊው መኖሪያ ቤት ተገኝታ አነጋግራዋለች፡፡

       እስቲ ስለ ልጅነት ህይወትህ በጥቂቱ ንገረኝ?
የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም እዚሁ ፒያሳ አሁን የምንገኝበት ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ለአባቴ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ከእኔ በታች ሶስት እህቶች አሉኝ፡፡ የልጅነት ጊዜዬ በጣም አሪፍና በእንክብካቤ የተሞላ ነው፡፡ የመዋዕለ ህፃናት ጊዜዬን በሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት ነው ያሳለፍኩት፡፡ የተለያዩ ቀለማትንና የስዕልን ጉዳይ ያወቅሁትና ወደ ስዕል ያዘነበልኩትም በዚሁ ት/ቤት ነው፡፡
ከሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት ለምን ወጣህ?
ከሊሴ የወጣሁት ጥሩና አስደሳች የነበረው ኑሯችን ከላይ ወደ ታች በማሽቆልቆሉ ነው::
በምን ምክንያት ነው የኑሮ ቁልቁለት ውስጥ የገባችሁት?
አባቴ ነጋዴና ጥሩ ባለሀብት ነበር፤ የተለያዩ ድርጅቶችም ነበሩት፡፡ ውጭ ተምሮ ነው የመጣው። የጃንሆይ መንግስት ወድቆ ደርግ ሲመጣ የግል ድርጅቶች ይወረሱ ስለነበረ አባቴ እነዚህ ድርጅቶች ከሚወረሱ ሰራተኞቹ እንደራሳቸው አድርገው እንዲሰሩ አድርጎ፣ እሱ ጎዴ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ውስጥ በወቅቱ ከፍተኛ በሚባል ደሞዝ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ፡፡
አባትህ በውጭ አገር ምን ነበር ተምረው የተመለሱት?
ምህንድስና (ኢንጂነሪንግ) ነው የተማረው፡፡ የታወቀ ኢንጂነር ነበር፡፡
ከዚያስ ምን ተፈጠረ ? …
እዛው ጎዴ እየሰራ እያለ የሶማሌ ጦርነት ተነሳና በግርግር ታፍሶ ታሰረ፡፡ ለ11 ዓመታት ያለምንም ጥያቄና ክስ እስር ቤት ቆየ፡፡ በዚያ ጊዜ እኛ አባታችንን አናውቀውም ነበር፡፡ እናታችን ነበረች ውጣ ውረዱን ችላ፣ እንደ አባትም ጭምር ሆና ያሳደገችን፡፡ በዚህ መሀል እናታችን ብዙ መከራና ችግር አሳልፋለች። እኛ በወቅቱ ልጆች ሆነን መኪናችን በ500 ብር ሲሸጥ፣ እቃችን ከቤት ሲወጣ አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ሁሉ በደል ሲደርስ እናቴን የሚደግፋት ስላልነበረ መቋቋም አልቻለችም፡፡ ከዚያ እኔና ታናሽ እህቴ ሌላ ቦታ እንድናድግ ለዘመድ ተሰጠን፡፡
የትና ለማን ነበር የተሰጣችሁት?
እዚሁ አዲስ አበባ ከመነን ከፍ ብሎ ባለ ሰፈር አጎቴ ቤት ነው ያደግነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሊሴ ገ/ማርያም ወደ ቄስ ት/ቤት፣ ከቄስ ት/ቤት ወጥቼ ደግሞ በፀሐይ ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ጀመርኩኝ ማለት ነው፡፡ ከፀሐይ ጮራ በኋላ ደግሞ የካቲት 12 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት (መነን) ገባሁና የሀይስኩል ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፡፡
ከ12ኛ ክፍል በኋላ ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የመማር ዕድል አልገጠመህም?
አልተማርኩም፤ ምክንያቱም ውጤት አልመጣልኝም ነበር፡፡ ሆኖም ሊሴ ገ/ማርያም እማር በነበረበት ወቅት ስለ ስዕል፣ ስለ ቀለም በደንብ የማወቅ እድል በማግኘቴ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በስዕል የመግፋቱ ነገር በውስጤ ነበር፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እያለሁ በስዕል ጥሩ ውጤት ነበረኝ። ለእናቴ በስዕል ስራ መግፋት እፈልጋለሁ ስላት፣ አላበረታታችኝም፤ እድልም አልሰጠችኝም ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ከኔ ጋር ስዕል ይሰሩ የነበሩ ልጆች አሁን እውቅ ሰዓሊያን ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ሰዓሊ ሮቤል ብርሃኔን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡
አሁን አንተ ስዕል የምትስለው በልምድ ብቻ ነው ማለት ነው?
እንደነገርኩሽ 12ኛ ክፍልን እንደጨረስኩ ስራም አልነበረኝም፤ ውጤትም ስላልመጣልኝ መቀጠል አልቻልኩም ነበር፡፡ የዕለት ወጪ ለመሸፈን ትንንሽ ስራዎችን እየሰራሁ ገንዘብ አገኝ ነበር፤ ግን በቂ ስላልነበረ ስደት ሄድኩኝ፡፡ የተለያዩ አገሮችን በስደት እረግጫለሁ፡፡ ለምሳሌ ድሬደዋ በመሄድ ነው ስደትን “ሀ” ብዬ የጀመርኩት፡፡ ከዚያ ወደ ጅቡቲ ሄድኩኝ፤ እዛም አልተሳካልኝም፡፡ ገንዘብ መያዝ አልቻልኩም። ጓደኞቼ ኬንያ እንሂድ የሚል ሀሳብ አመጡ፡፡ እሱን ተቀብዬ ኬንያ ገባሁ። እዛም የመለወጥና የመስራት ዕድል ባለማግኘቴ ተመልሼ ወደ አገሬና ቤተሰቤ መጣሁና ትንሽ ጊዜ እንደተቀመጥኩ፣ የአቢሲኒያ የስነ - ጥበብ ትምህርት ቤትን ማስታወቂያ አየሁኝ። ከዚያ መማር እፈልጋለሁ አልኩኝ፡፡ እናቴ በ1996 ዓ.ም እንደ ህፃን ልጅ ይዛኝ ሄዳ፣ አስመዘገበችኝ። የስዕል ትምህርቴን እዛ ተምሬ ተመርቄያለሁ፡፡ ከዚያም ስዕል እየሳልኩ፣ የእንጨት የብረታ ብረትና ሌሎች ስራዎችን ተቀጥሬ ስሰራ ነበር የኖርኩት፡፡
የአካል ጉዳት ያጋጠመህ እንዴት ነው?
የአካል ጉዳት ካጋጠመኝ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጉዳቱ በአንዴ የመጣ ሳይሆን ከወገቤ በታች እግሬ ቀስ በቀስ እየታመመና ቅርፁን እየቀየረ መጣ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና እከታተል ነበር፤ ብዙ መድኃኒት ይሰጡኛል ግን ምንም መፍትሄ ሊመጣ አልቻለም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መጣ፤ ቆሜ እየሄድኩ እግሬ ይከዳኛል፡፡ ብድግ እልና እግሬን ማዘዝ አቅቶኝ ተመልሼ እቀመጣለሁ፤ እየሄድኩ አስፋልት ላይ እየተጋጨሁ መውደቅ ጀመርኩኝ፡፡ ቀስ በቀስ በራሴ መሄድ ተስኖኝ በክራንች መሄድ ጀመርኩኝ፡፡ ፊዚዮ ቴራፒ ታዘዘ፤ ምንም ለውጥ የለም፡፡ በቃ ቤት ውስጥ ቀረሁ ማለት ነው፡፡ ከአቢሲኒያ ት/ቤት እንደተመረቅሁ ነው ቤት የዋልኩት፡፡
የተሻለ ህክምና ለማግኘትና የችግሩን መንስኤ ለማወቅ አልሞከርክም?
በቅርቡ በሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ አማካኝነት “ኪዩር” ሆስፒታል ህክምና ጀምሬ ነበር፡፡ ኪዩር ሆስፒታል ብሩክ የሺጥላን መራመድ እንዲችል ያደረገ ተዓምረኛ ሆስፒታል ነው፡፡ እነሱ ባደረጉት ምርመራ፤ የወገብ አከርካሪ (ስፓይናል ኮርድ) መጎዳት መሆኑን ደርሰውበታል፡፡
ታዲያ እንዴት በህክምና ሊረዱህ አልቻሉም?
አዎ ሊረዱኝ ሊያክሙኝ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ሆስፒታሉ ሲከፈት ህፃናትን ለማከም ስለነበረ አሁን አዋቂዎችን እንዳያክሙ ተከልክለዋል፡፡ እነሱም ይህንን በግልፅ ነግረውኛል፤ ኃላፊነት የሚወስድ ሰው ቢኖር ወይም ቢፈቀድላቸው ሊያክሙኝ ይችሉ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡
በአሁኑ ሰዓት መተዳደሪያ ገቢህ ምንድን ነው?
እንደምታይኝ ከስዕል ውጭ ምንም አልሰራም። ስዕልም ስሜቴ ስለሆነ ማቆም ስለማልችል እንጂ ተሰርቶ ከመቀመጥ ውጭ ለገበያም ሆነ ለእይታ የማቀርብበት መድረክ አላገኘሁም፡፡ የምተዳደረው በባለቤቴ ድጋፍ ነው፡፡ እሷ ተሯሩጣ ፅዳት ሰርታ፣ ቀለቤም የምስልበት ቀለሜም እንዳይጎድል ታደርጋለች፡፡ የምኖረው በምታይው በቆርቆሮ የተጠጋገነ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ያደግንበትን ቤት እህቴ ትዳር ይዛ እየኖረችበት ነው፡፡ ስዕል የምስለው የምኖረው በምታይው ጎስቋላ ቤት ነው፡፡ ከ150 በላይ የደከምኩባቸው ስዕሎች፣ በዝናብ፣ በአቧራና ቦታ በማጣት ለብልሽት እየተዳረጉ ነው፡፡ የትም እንደማላደርሳቸው ባውቅም እስላለሁ፡፡ ለዚህ ብርታት ደግሞ ባለቤቴ ትልቁን ድርሻ ትይዛለች። ስዕል ሳልስል እንድውል፣ ተስፋ እንድቆርጥ በጭራሽ አትፈልግም፡፡ ባለቤቴ ሜሮን ብርሃኑ ከፅዳት ባሻገር ጥልፍ እየጠለፈች በመሸጥ እኔ ምንም ነገር እንዳይጎድልብኝ ያላትን አቅም ሁሉ ትጠቀማለች። እሷ ባትኖር ምን ልሆን እንደምችል ሳስብ በጣም ይከብደኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ እሷን በማግኘቴ እድለኛ መሆኔን ለመግለፅና ለማመስገን እፈልጋለሁ።
ግቢው በጣም ቆንጆ ነው፤ ትልልቅ ቤቶችም አሉበት፤ አንተ የምትኖርበት ደሳሳ ቤት የማን ነው? ተከራይተህ ነው?
ግቢው የኪራይ ቤቶች ነው፡፡ ተወልጄ ያደግሁበት ነው፤ እናቴ ይሄኛውን ቤት ሰጥታኝ ነው። ትልቁንና ዋናውን ቤት እህቴ እየኖረችበት ነው፡፡ የትም መውደቂያ ስለሌለኝ ለማዕድ ቤትነት እንኳን በማይመጥን ቤት እየኖርኩኝ ነው፡፡ መኝታ ቤቴን … ስቱዲዮዬን እያቸው (ባለቤቱ ሜሮን እንድታሳየኝ እየነገራት) ክረምት ሲሆን ከጀርባችን ያለው ቤት ከፍታ ቦታ ላይ ያለ ስለሆነ የጣሪያውም ሆነ ሌላው ጎርፍ ተመልሶ የኛ ግድግዳ ላይ ነው የሚያርፈው፡፡ በዚህ ምክንያት ከቤት እቃችን በተጨማሪ ስዕሎቼ ይበሰብሳሉ ይሸራረፋሉ፡፡ እንደምታያቸው እርስ በእርስ ተደራርበውና ተዛዝለው ነው ያሉት፡፡ ቤቱን ባለቤቴ ጠጋግና ለፍታ አስተካከለችው፡፡ ይሄ አሁን የምታይው ቤት በጣም ተለፍቶበት እንጂ ቤት አይመስልም ነበር፡፡
እዚህ ቤት ከመግባትህ በፊት የት ነበር የምትኖረው?
በፊት ከእናቴ ጋር ነበር የምኖረው፡፡ ትልቅ ከሆንኩ በኋላ ለብቻዬ አንድ ክፍል ተሰጥቶኝ (ከዋናው ቤት ጋር የተያያዘ ነው) እኖር ነበር፡፡ ባለቤቴ አብረን ለመኖር ፍቃደኛ ስትሆንና አንዳንድ እቃዎችን ስናሟላ፣ ቤቱ ጠበበን፡፡ እናቴ እንደምንም ብላችሁ ይህን ቤት አስተካክላችሁ ኑሩ ብላ ሰጠችን። ይሄው እዚህ ቤት ለማለት በሚከብድ ቤት ውስጥ ከስዕሎቼ ጋር ተጣብቀን እየኖርን ነው፡፡
ሀይስኩል አብሮህ ይማር የነበረውን ሮቤልን ጨምሮ በርካታ ሰዓሊያን አሉ፡፡ ብሩክ የሺጥላም የቅርብህ ሰው ነው፡፡ ታዲያ በምታውቃቸው ሰዓሊያን በኩል ስዕሎችህ ለእይታና ለገበያ እንዲቀርቡ ያልተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው?
ያን ያህል ብዙ ሰው አላውቅም፡፡ የሚያውቁኝና አቅም አላቸው ብዬ የማስባቸውም ሰዎች ምክንያታቸው ባይታወቅም የምጠብቀውን ያል ድጋፍ አላደረጉልኝም፡፡ በእርግጥ ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ በቅርቡ 20 ያህል ስራዎቼን በኤግዚቢሽን ላይ እንዳቀርብ አድርጎ ሁለት ስዕሎቼን ለመሸጥ በቅቻለሁ፡፡ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፡፡ ከገንዘቡ በላይ ስዕሎቼ ለሰው አይን በቅተው፣ ከዚያ አልፈው ለሽያጭ ሲበቁ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል አስቢው … ተደጋጋሚ እድል ቢያገኙ ደግሞ ምን ያህል እንደሚያወጡ መገመት ይቻላል፡፡ ስዕሎቹን ስስላቸው ቆንጆ ይሆኑና እዚህ እርስ በእርስ ሲደራረቡ፣ ፍሳሽና አቧሯ ሲነካቸው ይበላሻሉ፡፡ አንድ ቀን ተስፋ አለኝ፤ ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡    
ስዕሎቹ ምን ያህል ተሸጡ?
ለእኔ ትልቅ ብር ነው ማለት እችላለሁ፡፡፡ ብሩክ የሺጥላ ዋጋውን ተደራድሮ፣ ለመንግስት ታክስ ከፍሎ ነው የሸጠልኝ፡፡ አንዱ 6 ሺህ ብር፣ አንዱ ደግሞ 1ሺህ አምስት መቶ ብር ተሸጦ ተቀብያለሁ፡፡ ሌላው ኢሳያስ ግዛው የሚባል ታዋቂ ሰዓሊ አለ፤ ሀይስኩል አብረን ነው የተማርነው፡፡ ብዙ ሊረዳኝ ፈልጎ ብዙ ጥሯል፡፡ ባለፈው ጣይቱ ሆቴል የተቃጠለ ጊዜ ለቤቱ ድጋፍ ተብሎ ኢሳያስ ባዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ስራዬን አቅርቤያለሁ፡፡ በእርግጥ ኤግዚቢሽኑን ኢሳያስ ሊያቀርብልኝ፣ መፅሄት ሊያሳትምልኝ የነበረው ከጣይቱ መቃጠል በፊት ነበር፡፡ በዚህ መሀል ቃጠሎው ሲከሰት የእኔም ኤግዚቢሽን ሳይቀርብ ቀረ፡፡ ኢሳያስ ግን ሊረዳኝ ጥረት አድርጓል፤ ጥረቱን አደንቃለሁ አመሰግነዋለሁ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሆቴል ውስጥ አምስት ስዕሎቼን ለእይታ አብቅቼ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ አሁን ባለኝ የጤና እክል ተንቀሳቅሼ ስዕሎቼን በተከታታይና በጥሩ ሁኔታ ለእይታ ለማብቃት አልቻልኩም፡፡ አሁን ሁሉም ነገር በሰው ነው የሚሆነው፡፡ እኔ ለዚህ የሚያበቃ ሰው የለኝም፡፡ ባለቤቴም እንደምታያት የቤቱንም የውጭውንም ሰርታ ደክማ ነው የምታኖረኝ፡፡
ስዕል ትስላለህ ይቀመጣል፤ መቀመጡ ገቢ አለማምጣቱ ተስፋ አያስቆርጥህም?
 እኔ ገቢውን ብዙም አላስበውም፡፡ ሰዎች ቢያዩትና አስተያየት ቢሰጡኝ ነው የምመርጠው። ያንንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ እየሳልኩ አስቀምጣለሁ፡፡ አንድ ቀን እንደነገርኩሽ ሁሉም ነገር ጥሩ ይሆናል፤ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ ቆርጬ አላውቅም፤ ምክንያቱም ተስፋ የሆነች ሚስት ፈጣሪ ሰጥቶኛል፡፡ እቃ ስትገዛ እንኳን ከእኔ የስዕል ቀለሞች ነው የምትጀምረው፡፡ ተስፋ መቁረጥ የጀመረ ሰው እየሞተ ነው ማለት ነው፡፡
በፊት በርካታ ጓደኞች እንደነበሩህ ነገረኸኛል --- አሁን ይጠይቁሃል?
ይሄ ግልፅ ነው … በአንድ ወቅት አንቺን ከበው መዋል የሚፈልጉ፣ ጓደኝነትሽን አጥብቀው የሚፈልጉ የነበሩ ሰዎች፣ ቀን ሲከዳሽ አብረውሽ አይሆኑም። እኔም የዚህ ሰለባ ነኝ፡፡ ከሚስቴና ከአንዳንድ የቤተሰቤ አባላት በስተቀር ድሮ የነበሩኝ ሁሉ ትተውኛል፤ አልፈርድባቸውም፡፡ ጊዜው ለሁሉም ነገር አመቺ አይመስለኝም፡፡
ባለቤትህን የምታውቃት የአካል ጉዳት ከመከሰቱ በኋላ ነው በፊት?
ጤነኛ እያለሁ ነው የተገናኘነው፡፡ እሷ ጤነኛ እያለሁ ከነበራት ፍቅርና እንክብካቤ በላይ ነው አሁን እየተንከባከበችኝ ያለው፡፡ በእርግጥ ልጅ አልወለድንም፤ ከላይ አልተሰጠንም፤ በፍቅርና በሰላም እየኖርን ነው፡፡ በችግርም በመከራም በደስታም ጊዜ አብራኝ ልትሆን በጋብቻችን ቀን የገባችውን ቃል ከሚገባው በላይ እየጠበቀች ነው። በጣም አመሰግናታለሁ፡፡
በመጨረሻ የምትለው ካለ …
 የጥበብ ሰው ነኝ ግን ጤናዬ አሳሳቢ ነው፤ የምስለው የማድረው የምውለው ለጤናዬ ምቹ ባልሆነ ቤት ውስጥ ነው፡፡ የጥበብ ማህበረሰብ፣ መንግስትና በጎ ፍቃደኞች የጥበብ ሞያዬንና ህልሜን እውን አድርግ ዘንድ የተሻለ ቤት ውስጥ መኖር እንድችል እንዲረዱኝ እማፀናለሁ፡፡ እስካሁን እኔን ለመደገፍ የሚችሉትን ያህል ሲደክሙ ለነበሩ ለብሩክ የሺጥላ፣ ለባለቤቴ ሜሮን ብርሀኑ፣ ለኢሳያስ ግዛው፣ ለጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔና ለሌሎችም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

Read 1208 times