Saturday, 25 March 2017 12:55

ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ለ3ኛ ጊዜ “የፍቅር ሳምንት” ያከብራል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት በሞት ያጡ ህፃናትን፣ በልመና የሚተዳደሩና በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው የነበሩ እናቶችን ከነልጆቻቸው ሰብስቦ ድጋፍ እያደረገ ያለው ሙዳይ የበጎ አድራጎት ማኅበር፤ ለ3ኛ ጊዜ ከመጋቢት 17 እስከ 24 ቀን 2009 በልዩ ልዩ ዝግጅቶች “የፍቅር ሳምንት” እንደሚያከብር አስታውቋል፡፡
የማኅበሩን የበጎ ተግባር እንቅስቃሴ ከመገናኛ ብዙኃን ከሰሙ በኋላ አንዳንድ ትውልድ ወዳድ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ድርጅቶች “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በማለት የቻሉትን ድጋፍ ከሚያደርጉት በስተቀር ምንም ቋሚ በጀት የሌለው ይህ ማኅበር፣ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ እናቶችና ህፃናትን እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ከ900 በላይ ችግረኛ ወገኖችን ከነበሩበት አሳዛኝ ህይወት በማላቀቅ ቤት በመከራየት፤ የምግብ፣ የልብስና የህክምና ወጪያቸውን በመሸፈን፤ ልጆቹ ትምህርት እንዲማሩ፣ ወላጆቻቸው ሙያ ተምረው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉ ስለ ፍቅር ሳምንት መግለጫ በተሰጠበት ወቅት የማኅበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ገልጻለች፡፡
ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሕፃናት በተለያየ ምክንያት እናት አባታቸውን ያጡ፣ ወይም ምንም ደጋፊ የሌላቸው ወይም ምንም ገቢ ከሌላት ከነጠላ ቤተሰብ ጋር ከእናቶች፣ ከአያቶች ወይም ከአክስቶች ጋር የሚኖሩ፣ ህፃናት እንደሆኑ የጠቀሰችው ወ/ሮ ሙዳይ፤ በግቢው ድጋፍ የሚደረግላቸው ህፃናትና አዋቂዎች በቀን ሶስት ጊዜ ቁርስ ምሳና እራት ይመገባሉ ብላለች፡፡
“የፍቅር ሳምንት” ዓላማ የህፃናቱ ምግብ፣ መጠለያ፣ ሕክምና፣ ትምህርት፣ … ማግኘት ብቻውን በቂ አይደለም፤ የሚጎድላቸው ነገር አለ፤ የቤተሰብና የወላጆች ፍቅር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ የአገር ተረካቢ፣ የነገ አገር መሪ፣ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚ/ር፣ ሳይንቲስት … የሚሆኑ ህፃናት በጥሩ ሁኔታ መማር፣ ፍቅር አግኝተው ማደግ … ሙሉ ስብዕና የተጎናፀፉ ዜጎች ለመሆን እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ስለዚህ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ህዝብ ቤተሰቡንና ልጆቹን ይዞ በሙዳይ በጎ አድራጎት በመገኘት ፍቅር እንዲለግሳቸው ለ3ኛ ጊዜ በ“ፍቅር ሳምንት” የተገኘውና የሙዳይ አምባሳደር የሆነው አርቲስት ፀሐዬ ዮሐንስ ጠይቋል፡፡
መግለጫው በተሰጠበት ወቅት የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር እስካሁን ስላደረገው እንቅስቃሴ የተገለጸ ሲሆን፣ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በብሬል እየታገዙ 500 ተማሪዎች ከ1ኛ - 8ኛ ክፍል እያስተማረ ሲሆን ማዕከሉ ስላልበቃ 120 ልጆችን ከ200 እስከ 600 ብር በመክፈል በየሰፈሩ ቤት ተከራይቶ ሲያኖር፣ ለዋናው ግቢና ከጎን ላለበት ኪራይ በየወሩ 162 ሺህ ብር፣ ለሰራተኞችና መምህራን ደመወዝ በየወሩ 120 ሺህ ብር ለምግብና ለተለያዩ ወጪዎች በየወሩ 300 ሺህ ብር ወጪ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለ450 ሴቶችና ልጆቻቸውን ለብቻ ለሚያሳድጉ እናቶች ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን፣ 1000 ሴቶች ስልጠና ወስደው አመለካከታቸው እንዲለወጥ ተደርጎ ወደ መደበኛ ህይወት ገብተዋል፡፡ 15 ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ራሳቸውን መቻላቸውን፣ ከየመኖሪያ አካባቢያቸው ተሰደው ወደ ማዕከሉ የገቡ 1,500 ሰዎች ወደየመጡበት ቀዬ እንዲመለሱ መደረጉም ታውቋል፡፡
ወ/ሮ ሙዳይ ይህን ሁሉ ድጋፍ የምታደርገው አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚያደርጉላት ድጋፍና ብድር ነው፡፡ ብድር አትፈራም፡፡ ደግሞም ጥሩ ከፋይ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት 5 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲለባት ገልጻለች፡፡ ለግቢው ተጠቃሚዎች በየቀኑ 300 እንጀራ የሚጋገር ሲሆን ለገቢ እንደደጉማት በማለት በቀን 300 እንጀራ በሦስት ደረጃ 3.50፣ 4.00፣ 500 ብር እየጋገረች ለራስ አምባ ሆቴልና ለኮተቤ መምህራን ማኅበር ታቀርባለች፡፡ ንፁህ ጤፍ ገዝታ ግቢው ውስጥ በተተከለ ወፍጮ አስፈጭታ እዚያው አቡክታ የምትጋግረውን እንጀራ የሚወስድላት ድርጅት፣ ሆቴልና ሱፐር ማርኬት ብታገኝ በቀን 10,000 እንጀራ የመጋገር አቅም እንዳላት ገልጻለች፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በጣም አስከፊና አሳዛኝ አደጋ መከሰቱን ያስታወሰው በበጎ ፍቃደኝነት መድረክ ሲመራ የነበረው ታየ ወርቁ፤ እነዚህ ሰዎች ለዚህ አደጋ ሊጋለጡ የቻሉት በድህነታቸው ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ሄደው ቤት ሰርተው ወይም መሬት ገዝተው የሚኖሩት፣ ርካሽ ስለሆነና ሌላ ቦታ የሚጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ስለማይችሉ ነው፡፡
በመቶ ሺህ የሚገመት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው በድርጅትና በግለሰብ ደረጃ ከቤቱ ነቅሎ ወጥቶ ድጋፍና ዕርዳታ ሲያደርግ የነበረው፡፡ በዚህ ጋ ዳይፐር፣ በዚህ ጋ ስኳር፣ በዚህ ጋ ሞዴስ፣ በዚህ ጋ ውሃው፣ በዚህ ጋ ለስላሳው፣ በዚህ ጋ ጁሱ፣ … ተጭኖ ሲመጣ ነበር፡፡
ለምንድነው ለመርዳትና ለመደገፍ ሞት እስኪመጣ የምንጠብቀው? ለምንድነው እነ ሙዳይን፣ እነ መሰረትን፣ እነ መቄዶንያን አግዘንና የበለጠ አጠንክረን ሞትን ከአገራችን የማናጠፋውበት ምክንያት? በአንድ ጊዜ ለዕርዳታ የቀረበው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ነው። 5 ሚሊዮን ብር ለሙዳይ ቢሰጣት ግን ተአምር ትሰራበት ነበር። አደጋ ሲፈጠር “እኛም አለን” ከሚሉ ባለሀብቶች አንዱ ቤት ቢሰራላት፣ አሁን የምትረዳቸውን 900 ልጆች 1,500 ወይም 2000 ማድረስ ትችላለች፡፡
በዚህ ዓይነት ከጎዳና ላይ ህፃናትን እናነሳለን፡፡ እነዚህ ህፃናት ደግሞ ከተማሩ ይለወጣሉ፡፡ ሙዳይ የሚረዳት ካጣች አሁን የምትደግፋቸው ህፃናት ዕጣ ፈንታቸው መበተን ነው፡፡ ከተበተኑ ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ (ሕይወት) ወዳለበት ወደ ቆሼ ነው የሚሄዱት። ወደዚያ ሳያመሩ እዚሁ እያሉ ብንረዳቸው ምን አለበት፡፡ ሰው ከሞተ በኋላ የሚደረገው ዕርዳታና ድጋፍ እውነተኛ አይመስለኝም፤ ለታይታ ነው … በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ 

Read 525 times