Saturday, 25 March 2017 12:56

ባለ 5 ኮከቡ “ሳፋየር አዲስ” ሆቴል ለዳግማይ ትንሳኤ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

ግንባታው ከስድስት ዓመት በፊት ተጀምሮ በቅርቡ የተጠናቀቀውና ከ“ሁለት ሺህ ሀበሻ የባህል ምግብ አዳራሽ” አለፍ ብሎ የሚገኘው “ሳፋየር አዲስ” ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ለዳግማይ ትንሳኤ ተከፍቶ ስራ ይጀምራል ተብሏል፡፡
ሆቴሉ ከዘመናዊ ብልጭልጭነት የፀዳና በቀደመው የኪነ - ህንፃ ጥበብ በተጠረበ ድንጋይ መገንባቱን የሆቴሉ ባለቤት አቶ ፍስሀ አባይ ገልፀዋል፡፡
130 ያህል የተለያየ ደረጃ ያላቸው የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሆቴሉ፤ 1 ሺህ 500፣ 700 እና 150 ሰዎችን የሚይዙ 3 አዳራሾች፣ የአገር ውስጥና አለም አቀፍ ምግቦችን የሚያስተናግዱ 3 ሬስቶራንቶች፣ ጂምና ስፓ እንዲሁም የጤናና የውበት መጠበቂያና ሌሎች አገልግሎቶችንም ያሟላ ነው ተብሏል፡፡ ለ200 ሰዎችም የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ባለቤቱ ተናግረዋል፡፡
የሆቴሉ ባለቤት በወርቅ ጌጣጌጥ ስራ ለ30 ዓመት መስራታቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ሰዓት እያደገ በመጣው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለጎብኚዎችም ሆነ ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠትና የአገር ገፅታን ለመገንባት ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
የሆቴሉ ግንባታ ምን ያህል እንደፈጀ የተጠየቁት አቶ ፍስሃ፤ አሁንም ወጪ እየተደረገበት በመሆኑ ስራው እስኪያልቅ ወጪውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበታል ብለዋል፡፡

Read 4000 times