Print this page
Sunday, 26 March 2017 00:00

ሰሜን ኮርያ “የአሜሪካን ዛቻ ከቁብ አልቆጥረውም” አለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሰሜን ኮርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልወስድ እችላለሁ  በሚል በይፋ ማስጠንቀቋ፣ አገራቸውን ፍርሃት ውስጥ እንደማይከታትና የኒውክሌርና የሚሳየል ፕሮግራሞቿን ከማካሄድ እንደማይገታት ማስታወቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ባለፈው አርብ በሰጡት መግለጫ፣ አገራቸው በሰሜን ኮርያ ላይ ጠበቅ ያለ ማዕቀብ እንደምትጥልና ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስጠንቀቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የሰሜን ኮርያው ቃል አቀባይ በበኩላቸው ለአገራቸው የዜና ወኪል በኩል በሰጡት ምላሽ፣ አገራቸው በአሜሪካ ዛቻ እንደማትደናገጥ መግለጻቸውን አስታውቋል፡፡
የሰሜን ኮርያ ኒውክሌር አገሪቱንና ህዝቦቿን ከጥፋት የሚታደግ ሁነኛ መሳሪያ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ሰሜን ኮርያ ከአሜሪካ ሊቃጣባት የሚችልን ወታደራዊ ጥቃት በብቃት ለመመከት በሚያስችል ሁኔታ ኒውክሌር የታጠቀች አገር መሆኗን መሪዎቿ ሊገነዘቡ ይገባል ማለታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
ከንግድ ወደ ፖለቲካ ፊታቸውን ያዞሩት የአሜሪካ ባለስልጣናት፣ ሰሜን ኮርያን በዛቻና በማስፈራሪያ ትሸማቀቃለች ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል፤ መሳሳታቸውንም በቅርቡ ይገነዘባሉ ሲሉም አክለዋል፡፡
ምንም አይነት የኒውክሌርም ሆነ የሚሳኤል ሙከራ እንዳታደርግ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ክልከላ የተደረገባትና በኒውክሌር ፕሮግራሟ ሳቢያ ከአሜሪካ ጋር ግጭት ውስጥ የገባቺው ሰሜን ኮርያ፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ ለሁለት ጊዚያት የኒውክሌር ሙከራ ፍንዳታዎችን፣ ለ24 ጊዚያት ያህል ደግሞ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጓን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 6316 times
Administrator

Latest from Administrator