Monday, 27 March 2017 00:00

ቢል ጌትስ ዘንድሮም የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

    በ12 ወራት 1 ቢ. ዶላር የከሰሩት ትራምፕ፣ ከአምናው ደረጃቸው በ220 ዝቅ

       ላለፉት ሶስት አመታት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ሆነው የዘለቁት አሜሪካዊው የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ፣ ዘንድሮም የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ መሆናቸውን ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረገው የ2016 የፈረንጆች አመት የአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር አስታውቋል፡፡
አምና በ75 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት የአለማችን ቀዳሚው ቢሊየነር የነበሩት ቢል ጌትስ፣ በአንድ አመት ውስጥ የሃብት መጠናቸው በ11 ቢሊዮን ዶላር በማደግ 86 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ዘንድሮም በመሪነታቸው መቀጠላቸውን ያስታወቀው ፎርብስ፤ ቢል ጌትስ ካለፉት 23 አመታት በ18ቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር መሆን መቻላቸውንም አስታውሷል፡፡
አሜሪካዊው ዋረን ቡፌት በ75.6 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛው የአለማችን ባለጸጋ ሆነዋል ያለው መጽሄቱ፤ በአመቱ ከአለማችን ቢሊየነሮች ከፍተኛው የተባለለትን የ27.6 ቢሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሪ በማስመዝገብ አጠቃላይ ሃብታቸው 72.8 ቢሊዮን ዶላር የደረሰላቸው የአማዞን ኩባንያ መስራች ጄፍ ቤዞስ ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አስረድቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፖለቲካው የተጎናጸፉትን ድል በቢዝነሱ ለመድገም አልቻሉም ያለው ፎርብስ፤ ትራምፕ በአመቱ የሃብት መጠናቸው በ1 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቶ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በመድረሱ፣ አምና ከነበሩበት ደረጃ በ220 በማሽቆልቆል 554ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ገልጧል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ በድምሩ 1 ትሪሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያላቸው 183 የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለጸጎች የተካተቱ ሲሆን፣ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 11.4 ቢሊዮን ዶላር በማፍራት የሃብቱን መጠን 56 ቢሊዮን ዶላር ያደረሰው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የአለማችን ቢሊየነሮች ብዛት አምና ከነበረበት የ13 በመቶ እድገት በማሳየት፣ 2 ሺህ 43 መድረሱን ያስታወቀው ፎርብስ፤አሜሪካ 565 ቢሊየነሮችን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት ቀዳሚነቱን መያዟን፣ ቻይና በበኩሏ 319 ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ገልጧል፡፡
የሴት ቢሊየነሮች ቁጥር አምና ከነበረበት 202 ወደ 227 ማደጉ የተነገረ ሲሆን 39.5 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያላት ፈረንሳዊቷ ሌላኔ ቤቴንኮርት እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም የአለማችን ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር ሆናለች፡፡
በአመቱ ወደ ፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር የገቡ አዳዲስ ባለጸጎች ቁጥር 195 ሲሆን፣ አብዛኞቹ ቻይናውያን መሆናቸው ተነግሯል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፣ የሃብት መጠናቸው በማሽቆልቆሉና ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ሳቢያ ከዝርዝሩ ውስጥ የተወገዱ ባለጸጎች ቁጥር 78 ነው ተብሏል፡፡
በዘንድሮው  የአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 2 ሺህ 43 ቢሊየነሮች አጠቃላይ ድምር የተጣራ ሃብት 7.67 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ፎርብስ መጽሄት ሰኞ ዕለት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

Read 4436 times