Monday, 27 March 2017 00:00

ከሉሲዎቹ አንዷ ኢየሩሳሌም ነጋሽ ለአስቸኳይ ህክምና ርብርብ ትፈልጋለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ኢየሩሳሌም ነጋሽ ትውልዷ እና እድገቷ  ለገሃር ባቡር ጣቢያ አካባቢ በሚገኘው አበበች ቀበሌ ነው። ከቤታቸው ፊት ለፊት በነበረችው ትንሽ ሜዳ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ስትከታተል  ከእግር ኳስ ጋር ተዋወቀች፡፡  ከሜዳው ዳር ቆማ ኳስ በመከታተል፤ አንዳንዴም ኳስ በማቀበል  እግር ኳስን ተላመደችው።  በዚያች ትንሽ ሜዳ ላይ ጋሽ አለማየሁ የሚባሉ ሰው እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ቡና፤ ፖሊስ እና ሌሎችን ክለቦችን በሚወክሉ ታዳጊ ቡድኖች  ውድድሮችን ያዘጋጁ ነበር። ገና በስምንት አመቷ ጊዮርጊስን በወከለ ቡድን የምትጫወትበት እድል ተፈጠረላት፡፡ እግር ኳስን ገና በታዳጊ እድሜዋ እንድትወድ ያደረጓት የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ በተለይ ግን በትንሿ የሰፈራቸው ሜዳ ውድድሮች ያዘጋጅ የነበረው ጋሽ አለማየሁ ቤቱ ተቀምጦ ምናባዊ ጨዋታዎችን  እንደ ኮሜንታተር በማስተላለፍ በቴፕ ቀርፆ ያሰማቸው ነበር፡፡ ‹‹አንዳንዴ  ካሴቱን ተውሰን በየቤታችን እየወሰድን እንሰማ ነበር፡፡ ስሜን እየጠራ ሲያስተላልፍ ደስ ይለኝ ነበር ›› በማለት ኢየሩሳሌም ታስታውሳለች፡፡
ያኔ በሰፈራቸው ትንሿ ሜዳ ኳስን መጫወት ስትጀምር ‹‹ሚጡ›› በሚል ቅፅል ስሟ ትጠራ ነበር። ዛሬ በአሜሪካ በምትኖረው ፍሬወይኒ የተባለች ሴት አማካኝነት ተመልምላ በጋሽ ኢተፋ ገ/ሚካኤል ይንቀሳቀስ የሴቶች እግር ኳስ ፕሮጀክትን ተቀላቀለች። ይህ ፕሮጀክትም በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ፈርቀዳጅ የሚባል ነው፡፡ በጋሽ ኢተፋ ፕሮጀክት ስር የመጀመርያውን ዓመት የተጨዋችነት ዘመኗን ካሳለፈች በኋላ አዲስ ኮከብ ወደ ተባለ ሌላ ቡድንን ገባች፡፡ ለ2 ተከታታይ ዓመታት በአዲስ ኮከብ ክለብ ስትጫወት ቆይታ ለአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ለመመረጥ በቃች። ከአዲስ አበባው ምርጥ ቡድን ጋርም በአዳማ ከተማ በተካሄደ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና  ላይ ተሳተፈች፡፡ በዚህ ሻምፒዩና ምርጥ ብቃቷን በማሳየቷ ለመጀመርያ ጊዜ በ1993 ዓ.ም ለተመሰረተው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተመርጠች፡፡ እየሩሳሌም ለስፖርት አድማስ እንዳወጋችው መስቀል አደባባይ አካባቢ በጋሽ ኢተፋ ፕሮጀክት ስትሰራ በነበረበት ወቅት የብሄራዊ ቡድን ቱታ የለበሱ አትሌቶች ስትመለከት በታዳጊ አዕምሮዋ ብዙ ጉጉት ቢፈጠርባትም፤ በልቧ ግን በእግር ኳስ አንድ ቀን ይህን የብሄራዊ ቡድን ቱታ መልበሷ እንደማይቀር እምነት እንደነበራት ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ለመጀመርያ ጊዜ የተቀላቀለችው ብሔራዊ ቡድን ከእነ ‹‹እቱ መላምቺ›› ዘመን በኋላ ለኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስና ሉሲዎች በሚል ስያሜው ለሚታወቀው ብሄራዊ ቡድን መሰረት የነበረ ቢሆንም ብዙም እንዳልተወራለት  ኢየሩሳሌም ነጋሽ ትናገራለች፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ16 ዓመቷ በመሰለፍ ያደረገችው ጨዋታ ከጅቡቲ ጋር የተደረገ ሲሆን 11ለ0 ሲሆን ሰፊ ውጤት ያሸነፉበት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ1994 ዓ.ም  ሉሲዎቹ በሚል ስያሜ እየታወቀ የመጣው የሴቶች ብሔራዊ ቡድኑ በተጨዋቾች ስብስብ ተጠናክሮ ከተገነባ በኋላ በ3ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በሚደረግ የማጣርያ ውድድር ሲሳተፍ ኢየሩሳሌም ከቋሚ ተሰላፊዎቹ አንዷ ሆነች፡፡ በቅድመ ማጣርያው  የመጀመርያ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ከስዋዚላንድ አቻቸው ጋር ተደልድሎ የነበረ ቢሆንም ፎርፌ አግኝቶ  ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ተሸጋገረ፡፡ ይህም ለሁለተኛው የማጣርያ ጨዋታ በቂ ዝግጅት የማድረግ ዕድል የፈጠረ እንደነበር ኢየሩሳሌም ነጋሽ ለስፖርት አድማስ አስታውሳ ያኔ ስለነበረው የሴቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴ ስትገልፅ ‹‹ከ12 እና ከ13 ዓመታት በፊት በሴቶች እግር ኳስ በክለብና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በቂ እንቅስቃሴዎች አልነበሩም፡፡ ምርጥ ብቃት እና ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች በቂ ስልጠና  ሊያገኙ የሚችሉት በብሔራዊ ቡድኑ ሲያዙ እና ጨዋታዎች ሲኖሯቸው ነበር፡፡›› ብላለች
ለ3ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በሚደረግ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር ገብቶ የነበረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድኑን የሚያሰለጥኑት በሙገር ክለብ አሰልጣኝ ሆነው የሰሩት አዳነ ገ/የስ እና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት አሸናፊ በቀለ ናቸው፡፡ እቱ መላምቺ በተባለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዘመን ተጨዋች ሆነው ያሳለፉት በለጥሽ ገ/ማርያምም የቡድኑ አባል ነበሩ፡፡ እነዚህ 3 የእግር ኳስ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ  መሰረት የጣሉ ናቸው የምትለው ኢየሩሳሌም፤ በ3ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ሁለተኛ  ዙር ማጣርያ ሉሲዎቹን በዋና አምበልነት እንድትመራ ስትሾም ገና 17  ዓመቷ እንደነበር ታስታውሳለች። ከኡጋንዳ ጋር ተገናኝተው 4ለ2 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት አሸነፉ እና በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻሉበትን ታሪክ አስመዘገቡ። 3ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ያዘጋጀችው ናይጄርያ ነበረች፡፡ ከዚሁ የሉሲዎቹ 3ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ ኢየሩሳሌም ለብሄራዊ ቡድን መጫወቷን ስትቀጥል የተሳተፈችበት ውድድር የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ነበር፡፡
በ1996 ዓ.ም ከብሔራዊ ቡድኑ አገልግሎት ወደ ክለብ እግር ኳስ ስትመለስ “ኪውንስ” ወደ ተባለ ክለብ ነበር የገባችው፡፡ በወቅቱ የክለቡ  የተጨዋቾች ስብስብ ባግባቡ ያልተደራጀ እና ልምድ ያነሰው በመሆኑ ብዙም አልተሳካላትም ነበር፡፡ ስለሆነም ሌላ ክለብ ስታፈላልግ ቆይታ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቡና የሴቶች ቡድንን ተቀላቀለች፡፡ በ250 ብር ወርሃዊ ደሞዝ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ቡና የሴቶች ቡድን ገና ከጅምሩ ጥሩ ተቀባይነት በማግኘቷ ብዙ ኃላፊነቶች ነበሯት። ከተጨዋችነቷ ባሻገር ዋና አምበል ፤የቡድን መሪ፣ ምክትል አሰልጣኝ ሆና የመጀመርያውን አንድ ዓመት በቢሮ ለከፍተኛ ደረጃ ስታገለግል ቆየች፡፡
አሳዛኙ የጉዳት አጋጣሚና አስቸጋሪው የኳስ ማቆም ውሳኔ
ኢየሩሳሌም ነጋሽ በኢትዮጵያ ቡና የሴቶች ቡድን መጫወት ከጀመረች በኋላ በ1996 ዓ.ም የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ያልጠበቀችው አሳዛኝ ጉዳት አጋጥሟታል፡፡ በልምምድ ሜዳ ላይ  ከቡድን አጋሮቿ ጋር መሃል ባልገባ ሲጫወቱ በቀኝ ጉልበቷ አካባቢ የደረሰባት የጅማት መበጠስ ነው፡፡  በወቅቱ ለደረሰባት ይህን አይነት ጉዳት በፍጥነት ህክምና አግኝታ ልታገግም የምትችልበት ሁኔታ አልነበረም ለ1 ዓመት ተኩል ያህል የፊዚዮቴራፒ ህክምና ስትከታተል ነበር የቆየችው፡፡
ያኔ በነበረው የእግር ኳስ እንቅስቃሴ የተሟላ የክለብ አደረጃጀት ባለመገኘቱ እንዲሁም ብቁ የህክምና ባለሙያና ተቋም ባለመኖሩ ግን በቶሎ ታክማ እና ከጉዳትዋ አገግማ ወደ ጨዋታ ለመመለስ አልቻለችም፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ አመራሮች ትኩረት ሰጥተው ባሳለፉት ውሳኔ ጉዳቱ ከደረሰባት ከ2 ዓመት ከመንፈቅ በኋላ በ1999 ዓ.ም ላይ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ተጉዛ እንድትታከም አደረጉ፡፡ እስከ 55 ሺ ብር ወጭ በተደረገበት በዚህ ህክምና ከጉዳቷ በፍጥነት በማገገም መጫወት እንደምትችል ተስፋ አድርጋ ነበር፡፡
ስለሆነም ህክምናውን ካገኘች ከ6 ወራት በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ሞከረች፡፡ አልሆነላትም። ጉዳቱ ወዲያው ነው ያገረሸባት፡፡ በሳውዲ አረቢያ የወሰደችው ህክምና ወቅቱን የጠበቀ እና የተሟላ ባለመሆኑ በ2000 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እግር ኳስን ለማቆም በመወሰን ጫማዋን ሰቀለች፡፡ ‹‹ ገና ብዙ መጫወት በምችልበት የወጣትነት እድሜዬ ኳስን  ለማቆም ስገደድ በጣም አስቸጋሪ ውሳኔ ሆኖብኝ ነበር። ጫማዎቼን ከሰቀልኩ በኋላ ለ6 ዓመታት በቤተሰብ ህይወት በመቆየት አስቸጋሪውን ዘመን ማሳለፍ ነበረብኝ፡፡››
ስትል ለስፖርት አድማስ ተናግራለች፡፡
ከተጨዋችነት ጉዳት ማግስት ወደ አሰልጣኝነት
ኢየሩሳሌም ነጋሽ በተጨዋችነት ዘመኗ ካጋጠማት ጉዳት በኋላ ወደ እግር ኳስ ስፖርት ለመመለስ የወሰነችው በ2007 ዓ.ም ላይ ሲሆን ለመጫወት አልነበረም፡፡ በአሰልጣኝነት ለመስራት ነበር፡፡ ስለዚህም የአሰልጣኝነት ኮርሶች መውሰድ ጀመረች። በ2008 ዓ.ም ላይ በአሰልጣኝነት የ “ሲ” ላይሰንስ አገኘች፡፡ ወዲያውኑም በኢትዮጵያ ቡና የሴቶች ክለብ ዋና ረዳት ሆና በአሰልጣኝነት መስራት ጀመረች፡፡  2009 ዓ.ም ሲገባ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆና ተሾመች፡፡ በተመሳሳይ ወቅትም በኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የስልጠና ቡድን የመሳተፍ ዕድል ተፈጠረላት፡፡   ለመጀመሪያ ጊዜ  በተካሄደው የሴካፋ የሴቶች ሻምፒዮና ላይ ሉሲዎቹ በተሳተፉበት ወቅት ሲሆን የዋና አሰልጣኝ  መሰረት ማኔ ረዳት ሆና በምክትል አሰልጣኝነት በመስራት 3ኛ ደረጃ ማግኘት ችለዋል፡፡
ስለ ተጨዋችነት ዘመኗ አስታውሳ ኢየሩሳሌም ለስፖርት አድማስ ስትናገር  “በእኛ ጊዜ የነበረው የሴቶች ኳስ ማራኪና ውበት ያለው ነበር፡፡ ለሉሲዎቹ   መሰረት የጣልንበት ዘመን ነው፡፡ ተጫዋቾች ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ነበራቸው፡፡ በየቡድኑ የነበረው አንድነትና ፍቅር ለአሁኑ ትውልድ ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ ኳስን የተጫወትነው የገቢ ጥቅም ሳይኖረን በሙያ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ኳስን ስለምንወዳት ጥበብ በሜዳ ላይ እናሳይ ነበር፡፡ ከበረኛ እስከ አጥቂ ሁላችንም ምርጥ ነበርን፡፡ ይህ ሁሉ በቂ ክፍያ በማይገኝበት፤ በቂ ህክምና ባልነበረበት ብዙ ክለቦች እና ውድድሮች በሌሉበት ነው፡፡” ትላለች፡፡ “ዛሬ በሴቶች እግር ኳስ ብዙ ብር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ብዙ ተጫዋቾች ተፈጥረዋል፡፡
 በቂ በጀት ያላቸው እና ለስፖርቱ ትኩረት የሚሰጡ ክለቦች አሉ፡፡ ግን የተጫዋቾች ችሎታ እና ተሰጥኦ እንደ ድሮው አልሆነም፡፡ ዛሬ በአስተዳደር እና ለህክምና ተጫዋቾች የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት ዘመን ላይ ነው፡፡ በህክምና በተለይ ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ  በጉልበቴ ላይ የደረሰው ጉዳት በአሁኑ ወቅት ቢሆን ኖሮ ወዲያውኑ ህክምና አግኝቼ መጫወቴን በቀጠልኩ ነበር፡፡
አሰልጣኝነቷን እንዳትቀጥል
የተፈታተናት ጉዳት
በቀኝ ጉልበቷ አካባቢ ለደረሰባት የጅማት መበጠስ ከ10 ዓመት በፊት በሳኡዲ አረቢያ አድርጋ የነበረው የመጀመሪያ ህክምናው ስኬታማ ስላልነበር፤ ለኢየሩሳሌም ኳስን መጫወት ካቆመች በኋላ ማሰልጠኑንም ስትጀምር   እግሯ ጤነኛ ሆኖ አያውቅም፡፡ መንገድ ላይ ስሄድ እግሯ ይወልቃል። በተለይ ለበርካታ ዓመታት መኝታ ላይ ስትቸገር እና ህመሙን በየቀኑ ስትጋፈጥ ነው የኖረችው። ወደ አሰልጣኝነት ከገባች በኋላ በቀን ሁለቴ ከቡድን ጋር እየተገናኘች ስለምትሰራ በየጊዜው ህመሙ የሚያገረሽባት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ። በየስልጠናው በማደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ድንገት ጉዳቱ ይቀሰቀስባል፡፡ መሮጥ አትችልም፤ ኳስ መምታት አትችልም፡፡
የጉዳት ማገርሸቱ ነገር በተደጋጋሚ ሲያጋጥማት አሳሰባትና በመጀመሪያ ወደ ያሬድ ሆስፒታል ሄደች። ዶክተሩን ያነጋገረችው ኳስ ለመጫወት ስለምፈልግ በህክምና እንደምድን ተስፋ ማድረግ እችላለሁ በሚል ጥያቄ ነበር፡፡  የጉልበት ላይ ጉዳት ሲቆይ ይድናል ሲባል ስትሰማ ስለነበር ነው በዚያ ተበረታትታ ዶክተሩን ያማከረችው በዛ ላይ በእሷ ዕድሜ ያሉ ተጫዋቾች በተለያዩ ክለቦች ስለሚጫወቱ ወደ ሜዳ መመለስን ተስፋ ብታደርግ አይደንቅም ነበር፡፡ የያሬድ ሆስፒታል ዶክተር ግን ምርመራውን ካደረገላት በኋላ በተጫዋችነት  ለመቀጠል እንደማትችል ቁርጡን ነገራት፡፡ መስራት  የሞትችይው አሰልጣኝነቱን ብቻ ነው አላት፡፡
በያሬድ ሆስፒታል ካደረገችው ምርመራ በኋላ በቀን ሁለትና ሶስት ጊዜ ጉልበቷ የወለቀ ያሰቃያት ጀመር፡፡ ታፋዋ፤ የውስጥ እግሯ፣ ጀርባዋ አካባቢ ህመሞች ተጨማሪ ህመመሞች እየተሰሟት ሰነበተች። ስለሆነም በድጋሚ “ኪዮር” ወደ ተባለ ሆስፒታል ለምርመራ ሄደች፡፡
የኪዩር ሆስፒታል ዲያሬክተር ራጅ እንድተነሳ ከነገራት በኋላ ያን አድርጋ ለራጁ የምርመራ ውጤት ሲገለፅ ግን ምላሹ አስደንጋጭ ነበር፡፡ የኪውር ሆስፒታል ዲያሬክተር ምርመራውን ካደረገ በኋላ በሰጣት ልዩ ምክር በጉልበቷ ላይ ላጋጠማት የጅማት መበጠስ በሳኡዲ አረቢያ ያደረገችው የመጀመርያው ህክምና የተሳካ ስላልነበር አሁን ካለሽበት ጉዳት ለማገገም እና ሙሉ በሙሉ ለመዳን ዘመናዊ ህክምና በውጭ አገር በአስቸኳይ ማግኘት ይኖርባታል፡፡  ትክክለኛውን ህክምና ማግኘት የምትችለው ደግሞ በእንግሊዝ፤ በአሜሪካ ወይም በአውስትራሊያ ነው፡፡
‹‹ቶሎ ህክምናን ካገኘሁ ጉዳቱ ወደ የተባባሰ ደረጃ አያደርሰኝም በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረችው ኢየሩሳሌም ‹‹ ዋና ፍላጎቷ ወደ እግር ኳስ ተመልሳ የአሰልጣኝነት ህልሟን እውን ማድረግ፤ በሴቶች እግር ኳስ ለውጥ መፍጠር፤ ዋና የሴቶች ብሄራዊ ቡድኑን ማሰልጠን.. በስፖርቱ የሴቶችን የአመራርነት ሚና በሚያሳድጉ አቅጣጫዎች መስራት ነው›› ብላለች፡፡

Read 2575 times