Monday, 03 April 2017 00:00

በኦሮሚያ ግዙፍ የቤቨሬጅ ኩባንያ ዛሬ ይቋቋማል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

*አርሶ አደሮችን ጨምሮ 1 ሚሊዮን ገደማ ባለአክሲዮኖች ይሣተፉበታል
*የኩባንያው ካፒታል 5.7 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቷል
አጠቃላይ ካፒታሉ 5.7 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን የተገመተው "ኬኛ ቤቨሬጅስ" የተባለ ግዙፍ ኩባንያ በዛሬው እለት በኦሮሚያ በይፋ ይመሰረታል፡፡ የኦሮሚያ "የኢኮኖሚ አብዮት" በሚል በክልሉ የተጀመረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አካል የሆነው ይኸው የቤቨሬጅ ኩባንያ፤የተለያዩ ከአልኮል ነፃ የሆኑ መጠጦችን እንደሚያመርት የተገለጸ ሲሆን 310 ሺህ ያህል ወጣቶች፣ 400 ሺህ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች አክሲዮን በመግዛት ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኩባንያው ከአልኮል ነፃ የማልት መጠጦችን፣ የማዕድን ውሃ፣ ለስላሳ መጠጦችና ጭማቂዎችን የሚያመርት ሲሆን የጠርሙስ ፋብሪካ፣ የፕላስቲክና ፓኬጂንግ እንዲሁም የስፖርትና ኢንተርቴይንመንት ንዑስ ዘርፎችን ያቀፈ ግዙፍ የቢዝነስ ተቋም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ገብስ አምራች አርሶ አደሮችም ከዚህ ኩባንያ ጋር የገበያ ትስስር እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡ የኩባንያው የአዋጭነት ጥናት ልምድ ባላቸው አማካሪ ድርጅቶች በዝርዝር ተጠንቶ እንደተጠናቀቀና የፋብሪካዎቹን ማዕከል በጥናት የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን የኩባንያው ፋብሪካዎች ማዕከል ምዕራብ ሸዋ ዞን እንዲሆን መመረጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 4722 times