Monday, 03 April 2017 00:00

ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠው የጋምቤላ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ታቦት የደረሰበት ጠፋ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ጽላቱን የሚያውቁ ካህናት በምርመራው መካተት እንዳለባቸው ተጠቁሟል
• “ጥያቄውን ለሀገረ ስብከቱ እንዳናቀርብ ሥራ አስኪያጁ ያሳስሩናል” /ምእመናኑ

በጋምቤላና ደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የምትገኘው፣ የሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ዕድሜ ጠገብ ታቦት፣ የደረሰበት አለመታወቁን የከተማው ምእመናን የተናገሩ ሲሆን፤ በአቋራጭ መክበር በሚፈልጉ ስግብግቦች እጅ ሳይገባ አፋጣኝ ማጣራትና ምርመራ እንዲካሔድላቸው መንበረ ፓትርያርኩን ጠየቁ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ በ1941 ዓ.ም. መታነጿንና ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠ የኪዳነ ምሕረት ታቦትም እንዲገባ ካስደረጉ በኋላ፣ ሥርዓተ እምነታቸውን ሲፈጽሙባትና ሲማፀኑባት እንደኖሩ ምእመናኑ ጠቅሰው፤ ከየካቲት 24 ቀን ጀምሮ ግን ታቦቱ በመንበሩ ላይ እንደሌለ ከካቴድራሉ ካህናት መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
የታቦቱ/ጽላቱ/ በመንበሩ ላይ አለመኖር በመጀመሪያ ያረጋገጡት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ እንደነበሩና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ቄሰ ገበዙን እንደጠየቋቸው ያወሱት ምእመናኑ፣ ቄሰ ገበዙ፥ “እኔን ለምን ትጠይቁኛላችሁ? ሥራ አስኪያጁን ጠይቁ፤” የሚል ምላሽ በመስጠታቸው፣ “ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎብናል፤” ብለዋል፡፡ በቀጥታ ለጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዳያቀርቡ፣ “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ተጠቅመው ያሳስሩናል፤” ብለው እንደሚሰጉና ሁከት እንዳይቀሰቀስ ፍርሃት እንዳደረባቸው ምእመናኑ አልሸሸጉም፡፡
“ለምነን ያላፈርንባት፤ ችግራችንን ፈጥና የምትሰማን የኪዳነ ምሕረት ታቦት ጠፍታ እንዴት ዝም እንላለን፤ ብለን በአንድ ቦታ ተሰብስበን ከተመካከርን በኋላ በትዕግሥትና በሥርዓት ለሚመለከተው የበላይ አካል ማመልከትን መርጠናል፤” ያሉት ምእመናኑ፣ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ባለፈው መጋቢት 13 እና 14 ቀን፣ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሠራው ታቦት፣ የሀገርም ቅርስ መሆኑን ምእመናኑ ጠቁመው፣ በአቋራጭ የመክበር ምኞት በተጠናወታቸው ስግብግቦች እጅ ሳይገባ፣ በመንበረ ፓትርያርኩ መሪነት አስቸኳይ ማጣራትና ምርምራ እንዲካሔድላቸው ተማፅነዋል፤ ጽላቱ የሚቀመጥበት መንበር ባዶ መኾኑን የሚያሳይ በወቅቱ የተቀረፀ የቪዲዮ ምስል በአባሪነት ማቅረባቸውን ገልጸው፣ ጽላቱ በመንበሩ ላይ ተገኘ ቢባል እንኳ፣ ዕድሜ ጠገቡ ጽላት መሆኑን ለይተው በሚያውቁ ካህናት ታይቶ መረጋገጥ እንደሚኖርበት ጨምረው አሳስበዋል፡፡
አህጉረ ስብከቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፣ በክልሉ ተመድበው በሠሩበት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ 17 ብቻ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ወደ 53 ማደጉንና በደቡብ ሱዳን ጭምር መታነፃቸው ተገልጧል፡፡ ይህም የዋና ሥራ አስኪያጁን ሐዋርያዊ ትጋት ያመለክታል ቢባልም፣ በአገልግሎታቸው ቀጣይነትና አያያዝ ረገድ፣ ከአገልጋዮችና ምእመናን በርካታ ጥያቄዎች እየተነሡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ፣ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ በእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡



Read 6761 times