Monday, 03 April 2017 00:00

ኢህአዴግ "አደራዳሪ" አያስፈልግም በሚል አቋሙ ፀንቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

*"ሰማያዊ" ያለ አደራዳሪ በሚደረግ ድርድር ውስጥ ላለመሳተፍ መወሰኑን አስታወቀ    
*መኢአድ በድርድሩ መቀጠል አለመቀጠሉን በነገ ስብሰባ እወስናለሁ ብሏል  
*ገዢው ፓርቲ ለምን አደራዳሪ እንደማያስፈልግ ምክንያቶቹን አስቀምጧል  
*"ገለልተኛ የሚባል አካል የለም፤ወይ ኢህአዴግን ወይ ተቃዋሚን ይደግፋል"


በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል የሚደረገውን ድርድር “ማን ይምራው” በሚለው ጉዳይ ኢህአዴግ “በዙር እንምራው” የሚል አቋሙን እንደማይለውጥ የገለጸ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ያለ አደራዳሪ በሚደረግ ድርድር ውስጥ ላለመሳተፍ መወሰኑን ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ መኢአድን ጨምሮ 5ቱ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ሃሳብ ፈፅሞ እንደማይስማሙ የገለጹ ሲሆን ከየፓርቲ ሥራ አስፈጻሚዎቻቸው ጋር መክረው በድርድሩ እንቀጥላለን ወይም አንቀጥልም የሚለውን እንደሚወስኑ ጠቁመዋል፡፡   
ከድርድሩ አስቀድሞ ራሱን ያገለለው መድረክ በበኩሉ፤ዶ/ር መረራ ጉዲና እና በቀለ ገርባን የመሳሰሉ የመድረክ አመራሮችና ሌሎች ጋዜጠኞች ተፈተው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ተነስቶ ኢህአዴግ ከሌሎች ጋር ከሚያደርገው ድርድር ጎን ለጎን ከመድረኩ ጋርም እንዲደራደር የጠየቀ ሲሆን በገለልተኛ አካል መደራደር እንደሚፈልግም አስታውቋል፡፡  
ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 20 ፓርቲዎቹ በነበራቸው የድርድር ቀጠሮ ላይ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ "በዙር እየመራን እንደራደር" የሚለውን አቋሙን ቀይሮ ይመጣል የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም ገዢው ፓርቲ ግን "በዙር እየመራን እንደራደር" በሚለው ሃሳብ መጽናቱን አስታውቋል፡፡ ቀደም ሲል "ድርድሩ በዙር ይመራ" የሚል አቋም ሲያራምዱ የነበሩና በኋላ “ድርድር ያለ አደራዳሪ እንዴት ይሆናል” በማለት ሲከራከሩ የቆዩት ቅንጅት፣ አትፓ፣ ኢዲህንና መኢብን ጨምሮ 13 ፓርቲዎች፣ ሀሳባቸውን በመቀየር "ድርድሩ በዙር ይመራ" ወደሚለው የቀድሞ አቋማቸው ተመልሰዋል፡፡   
ኢህአዴግም "በዙር ይመራ" ከሚሉት ፓርቲዎች ጋር ድርድሩን ለመቀጠል የወሰነ ሲሆን "በገለልተኛ አደራዳሪ" የሚል አቋም የያዙ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን ከለወጡ ወደ ድርድሩ መመለስ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡ በተናጠል ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር የሚፈልጉ ፓርቲዎችን በተመለከተ፣ የተጀመረው ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን የጠቆመው ገዥው ፓርቲ፤ እሱም ቢሆን በመሃል "ገለልተኛ አደራዳሪ" የሚባል ነገር ከሌለ ነው ብሏል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ኢህአዴግ "ገለልተኛ አደራዳሪ" አያስፈልግም ያለባቸውን ምክንያቶች የገለጸ  ሲሆን አንደኛው ምክንያቱ፤"ገለልተኛ የሚባል ወገን የለም፤ ወይ ኢህአዴግን ወይ ተቃዋሚን ይደግፋል" የሚል ሲሆን ሌላኛው ምክንያቱ፤"ከዚህ ቀደም 4 መሰል ድርድሮች ያለ አደራዳሪ ተደርገው የምርጫ ህጉን በውጤታማ መልኩ ማሻሻል ተችሏል" የሚል ነው፡፡ ኢህአዴግ ሌላም ያቀረበው ምክንያት አለ፡፡ "ድርድሩ ሁለት ፀበኞችን ለማስታረቅ ሳይሆን ለፖለቲካው ምህዳር መስፋት ታስቦ የሚደረግ እንደመሆኑ መሃል ገቢ አሸማጋይ አያስፈልግም" ሲል አብራርቷል፡፡  
ለዚህ ምላሽ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፤“ኢህአዴግ የሚታመን ድርጅት አይደለም፤አናምነውም፤ስለዚህ አደራዳሪ የግዴታ ያስፈልገናል" ብለዋል፡፡ የመኢአድ ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ሀብተወልድ በበኩላቸው፤በአለማቀፍ ደረጃ የተደረጉ ድርድሮችን ተመክሮ በመጥቀስ የአደራዳሪ አስፈላጊነትን አስረድተዋል፡፡ አደራዳሪ መኖሩ መተማመን እንዲፈጠርና ድርድሩ ቀጣይነት እንዲኖረው እንደሚያደርግ በመግለፅም ኢህአዴግ የአደራዳሪን አስፈላጊነት እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡
የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ፤ፓርቲያቸው በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ቆይታው፣ የጋራ ምክር ቤቱን ስብሰባዎች በዙር የመምራት ሂደት ምንም ፋይዳ እንዳላመጣና መፍትሄ አመንጪ ሀሳብም ቀርቦበት እንደማያውቅ በመግለፅ፣ይሄም ድርድር ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው አደራዳሪ ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡  
"በዙር መድረክ እየመራን እንደራደር" የሚለው አቋሙ የማይለወጥ መሆኑን በድጋሚ ያስታወቀው ኢህአዴግ በበኩሉ፤ተቃዋሚዎች በድርድሩ ቢገፉበትም ባይገፉበትም የጀመረውን ተሃድሶ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ድርድሩንም ለመጀመር ያሰበው ከፍራቻ በመነጨ ሳይሆን ለሀገር ይበጃል ከሚል መሆኑን በመግለጽ፣ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ፤"ድርድሩን የጀመርኩት ከፍራቻ አይደለም" ለሚለው የኢህአዴግ ማብራሪያ፤“ይሄ በህዝብ ትግል የመጣ ድርድር ነው፤አራት ነጥብ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  
"ድርድር ያለ አደራዳሪ አይሆንም" በሚል አቋማቸው የፀኑት 6ቱ ፓርቲዎች፤ የሁለት ደቂቃ የምክክር ጊዜ ከተፈቀደላቸው በኋላ አቋማቸውን ያሳወቁ ሲሆን "በዚህ አካሄድ ድርድሩ ይሳካል የሚል እምነት የለንም፤ያለ አደራዳሪ የሚደረግ ድርድር ውጤት የለውም፤ የሚል አቋም ይዘን እንወጣለን፣በድርድሩ መቀጠል አለመቀጠላችንን ከየፓርቲያችን ስራ አስፈፃሚ ጋር  ተወያይተን በቀጣዩ ቀጠሮ እናሳውቃለን" ብለዋል፡፡
ቀጣዩ የፓርቲዎቹ የቀጠሮ ቀንም ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ሰሞኑን  አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤የፓርቲያቸው ሥራ አስፈፃሚ ነገ እሁድ ተሰብስቦ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ አቋም እንደሚይዝ የገለጹ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ድርድር ያለ አደራዳሪ በፍፁም የማይታሰብ በመሆኑ፣ በዙር መድረክ እየተመራ በሚደረግ ድርድር ውስጥ ላለመሳተፍ የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
ኢህአዴግ ሃሳቡን ለውጦ በገለልተኛ አደራዳሪ ለመደራደር ፍቃደኛ ከሆነ፣ ፓርቲው ወደ ድርድር መድረኩ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ጠቁሞ፣ካልሆነም ሌሎች ተደራድረው ሲጨርሱ አሁንም በአደራዳሪ ተራውን ጠብቆ ለመደራደር ዕቅድ እንዳለው ጠቁሟል፡፡     
 

Read 5217 times