Print this page
Monday, 03 April 2017 00:00

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም - ለተቃዋሚዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“በፓርቲያችንእንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ይፈጥርብናል”
አቶ አበበ አካሉ
(የ”ሰማያዊ” የውጭ ግንኙነት ኃላፊ)

የፓርቲ ስብሰባ ላይ ሆነን ነው የመረጃ ቋቶቻችንን ከፍተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለ4 ወራት መራዘሙን ያየነው፡፡ በጣም ነበር ያዘነው፡፡ መንግስት በሀገሪቱ ምንም አይነት ችግር የለም እያለ በሚዲያዎች እየነገረን፣ አዋጁን በድጋሚ ለ4 ወር ማራዘሙ ሀገሪቱ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ያሳያል፡፡ ሁሉም ነገር ተረጋግቷል፤ሰላም አለ፤በተባለበት ሰአት አዋጁን ማራዘም ለሀገሪቱም አይጠቅምም፤የፖለቲካ ምህዳሩንም ያጠባል፡፡ ለወደፊት የሚታሰሩ ሰዎችም ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ሰላም ሰፍኗል እያሉ አዋጁን የማራዘም ጉዳይ እንዴት እንዳዩት እኛ አናውቅም፡፡ ሰላም ነው ከተባለ ማራዘሙ ተገቢ አይደለም፡፡
የአዋጁ መራዘም በፓርቲያችን እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋትና ስጋት ይፈጥርብናል፡፡ በየክልሉ ተንቀሳቅሰን የፓርቲውን ስራ መስራት አለብን፣ ከህዝብ ዘንድ መድረስ አለብን፡፡ ይሄን ለማድረግ እንዴት ፍቃድ እናገኛለን፡፡ ይሄ በጣም ይከብዳል። በጣም ያሳስበናል፡፡ ፓርቲያችን በዚህ ጉዳይ ተሰብስቦና መክሮበት አቋሙን በመግለጫ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡

=================================

“የአዋጁ መራዘም ለኔ አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው”

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ ሊቀመንበር)

የአዋጁ መራዘም ለኔ አስደንጋጭ ነው፡፡ የስጋታችንን ደረጃ የበለጠ እያጠለቀው ነው፡፡ እነሱ ተሃድሶአችንን እያጠለቅን ነው እንደሚሉት ሁሉ የኛም ስጋት እንዲሁ ደረጃው እየጠለቀ ነው ያለው፡፡ ይሄ አዋጅ መፍትሄ አይሆንም፡፡ እነሱ ህዝብን አስገድዶ እየገዙ መኖር የሚለውን የቻይናዎች ፍልስፍና ነው እየተከተሉ ያሉት፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ያላቸው ህዝቦችን በምታስተናግድ ሀገር ላይ የዚህ ዓይነት አካሄድ በብሶት ላይ ብሶት፣ በምሬት ላይ ምሬት ይፈጥራል። ህዝቡን ለማስከፋት ምክንያት መጨመር ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ በዚህ ሀገር በጣም አሳዛኙ አጋጣሚ ነው፡፡ የዚህ አይነቱ እርምጃ ለኛ አይነቱ ሀገር የሚሆን አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ራዕይ እንዳጡና ምን ያህል ፍርሃት ውስጥ እንዳሉ ነው የሚያሳየው፡፡
4 ወር እኮ አሁንም ያልቃል፡፡ ከዛ ምን ይፈጠራል? 6 ወር ምንም ሳይሰራ አይደለም እንዴ ያለቀው፡፡ መፍትሄው ይሄ አይደለም፤ ዝም ብሎ ድብብቆሽ እንደሚጫወቱ ህፃናት መሆን ነው፡፡ እኔ ብዙም የፖለቲካ ጥበብ አላየሁበትም። ህዝቡ በነፃ ሃሳቡን ገልፆ መንቀሳቀስ ሲችል እኮ ነው መንግስት የህዝብን ሀሳብ መረዳት የሚችለው፡፡ በሀዘንና በምሬት አንገቱን ደፍቶ ውስጡ እየፋመ መኖሩ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ታምቆ የከረመ ነገር ፈንድቶ ሲወጣ ጉዳቱ ኃይለኛ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በብሶት ላይ ብሶት እየጨመሩ መሄድ የበለጠ ነገር ከማወሳሰብ ውጪ በሀገሪቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። የተወሰደውም እርምጃ አግባብ አይደለም፡፡ ህዝባችንም ትዕግስቱን አሳይቷል፡፡ ህገ መንግስቱ የሰጣቸው 4 ወር ጊዜ ካለቀ በኋላ ደግሞ ምን እንደሚፈበርኩ ለማየት የዚያ ሰው ያድርገን ነው የምንለው፡፡
በዚህ መሀል  የአባላቶቻችን መታሰር፣ የሰብአዊ መብት መጣስ ስጋታችን ያይላል ማለት ነው። ምን ተፈጥሮ ነው የሚያራዝሙት? ምን ስጋት ታያቸው? ከተፈለገም ችግር ባለባቸው ቦታዎች ብቻ ማራዘም ይቻል ነበር፡፡ አሁን አዲስ አበባ ምን ችግር ታየ? በሌሎች አካባቢዎችስ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤”80 ከመቶ በላይ ህዝብ እንዲራዘም ፈልጓል” ብለው ሲናገሩ፣ እንደ ሀገር መሪ ጥንቃቄ ማድረግ የለባቸውም እንዴ? የትኛው ድርጅት ነው ይሄን ያጠናው? ምናልባት ኢህአዴግ ካድሬዎቹን አነጋግሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ማን ጠያቂ አለብኝ እየተባለ ነው ሁሉም ነገር የሚደረገው፡፡ እንግዲህ ሁላችንም ተስፋ ቆርጠን … ቆርጠን የዚህች ሀገር ነገር ምን እንደሚሆን ያስጨንቃል፡፡  

===================================


“አሁንም ቢሆን
የሚያስፈልገው የፖለቲካ መፍትሄ ነው”

ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

አዋጁን ማራዘም ባለፉት 6 ወራት ታይቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ውድቀት በድፍረት ማስቀጠል ነው፡፡ አጠቃላይ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ ወድቋል፡፡ ከእድገት አንፃር፣ ከGTP 2 አንፃር፣ ከጤናና ከትምህርት አንፃር-----በሌሎችም ዘርፎች ታስቦ የነበረው የእድገት እቅድ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር የማይቀየርበት ጊዜ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ አዋጁ ተራዘመ ማለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በነበሩበት ደካማ አካሄድ ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ ሌሎች  መንግስትም ባለሀብቶችም የሚያካሂዷቸው ኢንቨስትመንቶች በሙሉ እየተጎዱ ነው የሚሄዱት፡፡
አሁንም ፖለቲካዊ መፍትሄ እስካልመጣ ድረስ 4 ወር ቢራዘም ምንም አይነት ለውጥ የሚያመጣ መስሎ አይታየኝም፡፡ ህዝቡ እስካሁን የጠየቃቸው ጥያቄዎች እየተመለሱለት አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶ ተብሎ እስከ ታች የወረደውን አካሄድ ለማየት ሞክረን ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋወሩ እንጂ የማያሰሩ ደንቦችና ህጎች ሪፎርም አልተደረጉም፡፡ ክፍተቶቹ እንዳሉ ናቸው፤አሁንም አልተዘጉም፡፡ ስለዚህ አዋጁ ለውጥ አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ለ4 ወር ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ አንድ ዓመት ራሱ በዚህ መንገድ ከቀጠለ ህዝቡ የበለጠ ወደ ሌላ አማራጭ እንዲያመራ በር እየከፈተ ነው የሚሄደው፡፡
 አሁን እንደምናየው በየመንደሩ ሚሊሻና ካድሬ የተለየ አስተሳሰብ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል እያሰረ ነው ያለው፡፡ ባለፉት ጊዜያት አንድም አባል ታስሮብን የማናውቅ ፓርቲ፣ አሁን በየወረዳዎቹ አባሎቻችን ታስረውብን ነው ያሉት፡፡ ይሄ የበለጠ ጥላቻን፣ ቅራኔንና ቂምን እየቋጠረ ነው የሚሄደው፡፡ ህብረተሰቡ አሁን ባለው አኳሃን የተሻለ አስተሳሰብ ይይዛል ብለን አናስብም፡፡ አሁንም ቢሆን የሚያስፈልገው የፖለቲካ መፍትሄ ነው፡፡ ውይይት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ውይይቱን ራሱ እናድርግ ስንል እንኳ ምን ያህል እየገፋን እንደሆነ እየታየ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እንዳለበት፣ የታሰሩ ሰዎች መፈታት እንዳለባቸው በአጀንዳ መልክ እንወያይበታለን ያልነው ሁሉ ዘግተውብናል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት ያለፉበትን የፖለቲካ ሂደት መገምገም አይከብደንም፡፡ በአጠቃላይ ስጋት እየጫሩ ነው ያሉት፡፡ እነሱም ይሰጋሉ፡፡ እንዳያሻሽሉ ግራ ገብቷቸዋል፡፡ እንዳያሳትፉን ደግሞ በመሃል ብዙ ሚስጥሮች ይወጣሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ለነሡ ስጋት ሆነው ነው የሚቀጥሉት፡፡
እንደሚታወቀው በሃገሪቱ ላይ የውጭ ምንዛሬ ጠፍቷል፡፡ ምንዛሬ ጠፋ ማለት ወጪ ገቢ ንግድ መስራት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ትላልቅ ባለሃብቶች በምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሠራተኛ እየቀነሱ ነው ያሉት፡፡ ምርት እየቀነሱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን ተብለው የተቋቋሙ ማዕከላት በገንዘብ እጥረትና በአዋጁ ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ  አገሪቱ በኢኮኖሚ ምን ያህል እየተጎዳች እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ይሄን ሁሉ ባለማሰባቸው አዋጁ መራዘሙ እስካሁን ከነበረው እጅግ የበለጠ እየጎዳን ነው የሚሄደው፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት የሚቻለው አዋጁን በማስቀጠልና በመዋሸት አይደለም፡፡ አንድ ታላቅ የሃገር መሪ የሆነ ሰው፤”82 በመቶ ህዝብ እንዲቀጥል ደግፎናል” ብሎ የሚናገርበት የውሸት አለም ላይ ነው ያለነው፡፡ መቼ ሄደው መረጃ ሰብስበው ነው? መቼ ህዝብ የሚናገረውን አደመጡ?... እንዲህ ያለ ሃሰተኛ መረጃ በአደባባይ መናገር እጅግ ያሳዝናል። መቼም አሁን ባለንበት ደረጃ አንቀርም፡፡ ተተኪው ትውልድም ቢሆን የለውጥ ጥያቄ አንግቦ ጥያቄ የሚያቀርብበት ጊዜ ሩቅ ይሆናል ብለን አናስብም፡፡
============================


‹‹አዋጁ መራዘሙ ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም››
ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት


በሌላው አለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ችግር ያለበት ቦታ ላይ ብቻ ተለይቶ ነው የሚታወጀው፡፡  እንደኛ ሃገር እንደዚህ የተራዘመ አዋጅ አይጣልም፡፡ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማራዘም ይልቅ “ለምንድን ነው ህዝቡ በየክልሉ ብሶቱን የገለፀብኝ ?”፣ “ምንድን ነው የጠየቀው?” የሚለውን አጢኖ፣መልስ ለመስጠት ቢሞክር ነበር የሚያዋጣው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ ተገቢ ነው ብዬ አልገምትም፡፡ መንግስት እንደ መንግስትነቱ ለህዝቡ ብሶት መልስ መስጠት እንጂ በጉልበትና በሃይል ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፡፡
ይሄ መንግስት ሁሉም እንደሚያውቀው ሠላም፣ እድገት እያለ ይናገራል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ሠላምም እድገትም ይፈልጋል፤ግን ሠላምና እድገት ሊመጣ የሚችለው ዝም ብሎ በምኞት ሳይሆን ህዝቡ ለሚጠይቀው ጥያቄ መንግስት ተገቢውን መልስ መስጠት ሲችል ብቻ ነው፡፡ በኔ እምነት አዋጁ መራዘሙ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል ብዬ አልገምትም፡፡
በአሁኑ ጊዜ የፓርቲያችን አባላትና አመራሮች ይታሰራሉ ይፈታሉ፡፡ እርግጥ ነው ለኮማንድ ፖስቱ አመልክተን የተፈቱልን አባላት አሉ፡፡ ግን በአጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴያችንን ገድቦታል። አባሎቻችን እንደ ልባቸው ተሰብስበው ውይይት ለማድረግ ተቸግረዋል፡፡

Read 2371 times
Administrator

Latest from Administrator