Monday, 03 April 2017 00:00

“አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ምስጋና ይግባው!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ዘንድሮ ለምንድነው ነገሮች እንደ አጀማመራቸው መቀጠል የሚያቅታቸው!
የሆነ ምግብ ቤት ትገቡና ምን የመሰለ ፍርፍር ታዛላችሁ፡፡ “ፍርፍር እንዲህ ዶሮ ወጥን የምታስንቅ ትሆናለች!” ምናምን እያላችሁ ትመገባላችሁ፡፡ “እሰይ የፍርፍር አምሮቴን የምወጣበት ግሩም ቤት አገኘሁ…” ትሉና አንድ ሁለት ቀን ትመላለሳላችሁ፡፡ ከዛ አንድ ሦስት ሳምንት ከረም ትሉና ትሄዳላችሁ።
“እስቲ ያቺን ጉደኛ ፍርፍር አቅርቡልኝ…” ትላላችሁ፡፡ ‘ጉደኛ ፍርፍር’ ትቀርብላችኋለች። ‘ጉደኛነቷ’ ግን እናንተ ባሰባችሁት መንገድ አይደለም፡፡ ምን አለፋችሁ…ፍርፍሩ የሆነ ለልማት የናዱት ቤት ፍርስራሽ አይነት ይመስላል፡፡ “ውስጡ የሆነ ኮረት የሚመስል ነገር ሁሉ ነበረው…” ብላችሁ ልትምሉ ሁሉ ትችላላችሁ፡፡ ያ ‘ጣት ያስቆረጥማል’ የተባለለት ምግብስ! ብዙ ጊዜ እንዲህ የሚሆነው የአብሳይ መለዋወጥ ምናምን ሳይሆን ቸልተኝነት ነው፡፡
“ምነው… የዛሬው ፍርፍር የለመድኩት አይነት አይደለም፣” ትላላችሁ፡፡
“ምን ሆነ?”  
አንደኛ ጣእም የለውም፣ ሁለተኛ ውስጡ ሰጋቱራ የሚመስል ነገር ሁሉ አለው፡፡”
“እንደውም እርሶ ደንበኛ ስለሆኑ በስፔሻል ነው የተሠራው፡፡” ስፔሻል! “‘ስፔሻል’ የተባለው እንዲህ ከሆነ ‘ኖርማሉ’ ምን እንደሚመስል አንድዬ ይወቀው…” ብላችሁ ሦስቴም ሳትጎርሱ ሂሳቧን ቁጭ አድርጋችሁ ትወጣላችሁ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የዘንድሮ ኮሚክ ነገር ምን መሰላችሁ… በሆነ ነገር ላይ ቅን አስተያየት መስጠት ‘ጉንጭ ማልፋት’ አይነት እየሆነ ነው፡፡ “ምግቡ እንደ በፊቱ አይደለም…” ከተባለ…አለ አይደል… “ምን ጎደለው?” “ምን እናስተካክል?” ምናምን ይባላል እንጂ  ጭራሽ… “ለእርሶ ተብሎ ስፔሻል ነው የተሠራው…” ምናምን አይነት ክርከር… የምር ቀሺም ነው፡፡
የሆድ ነገር ‘ምሳሌነቱ ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) አነሳነው እንጂ ሁሉም ነገር ላይ እንዲሁ ነው፡፡ መጀመሪያ ያያችሁት መልካም የሚባልና ያጨበጨባችሁለት ነገር ከጥቂት ወራት በሁዋላ ድራሹ ይጠፋል፡፡
“አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ምስጋና ይግባው!” ለማለት ያብቃንማ!
አንድ ጊዜ አንድ ‘የሹሮ አድናቂ’ ወዳጃችን፣ የሆነ ምግብ ቤት አሪፍ ሹሮ ይመገባል፡፡ ከዛም ምልልስ፡፡ ከዛም ጠፋ ይልና ከተወሰኑ ሳምንታት በሁዋላ ይመለሳል፤ ምን ቢያቀርቡለት ጥሩ ነው… ‘ትራንስፓረንት’ ሹሮ! “ብታዩት ሳህኑ ስር የተፋቀችው ቦታ ሁሉ ቁልጭ ብላ ትታያለች…” ነው ያለው፡፡ የምር ግን ‘ትራንስፓረንት’ ሹሮ መሥራት የቻለች ‘ሼፍ’ ዓለም አቀፍ የአእምሮ ብቃት ጥበቃ ማረጋገጫ ሊሰጣት ይገባል፡፡
ስሙኝማ…የዘንድሮ ጓደኝነት እንኳን መላው ጠፍቷል ነው የሚባለው፡፡ በመጀመሪያ ወራት ጓደኝነቱ ኤል ኒኖ እንኳን ሊተረትረው የማይችል  ይሆናል፡፡ አለ አይደል…አንዱ ከጎደለ ሌላኛው መተንፈስ የሚያቆም ይመስላል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ… አንደኛው ደንቀፍ ባደረገው ቁጥር… አለ አይደል…ሌላኛው፣
“እኔን ይድፋኝ!…” ይላል፡፡ በአንድ እጅ ብቻ ቀና ማድረግ የሚቻለውን በሁለት እጅ እቅፍ ይደረጋል።
አንደኛው ትን ባለው ቁጥር…ሌላኛው፣
“እኔን ትን ይበለኝ!...” ይላል፡፡
እናላችሁ…ሦስት ወር ከአንድ ሳምንት ሲሆን ይህ ነው በማይባል ምክንያት፣ አንዱ ሌላኛውን የሚወቅስብት ምንም ነገር ሳይኖረው ሁሉ ነገር ይለወጣል፡፡ ታዲያማ…አንዱ ደንቀፍ ባደረገው ቁጥር…ሌላኛው፣
“እያየህ አትሄድም… ምንድነው የሚያንሻፍፍህ!” ይላል፡፡  
አንዱ ትን ባለው ቁጥር…ሌላኛው፣
“እየመጠንክ አትጎርስም እንዴ!…ምንድነው እንደ ቡልዶዘር እየዛቁ መጎስጎስ!“ ይላል፡፡ (ጥያቄ አለን… በሁለት ጉንጭ ማኘክ ጎጂ ልማድ የሆነበት ምክንያት ይብረራልንማ!  አሀ…ምግብ ላይ ሲሆን አምስት ተጨማሪ ጉንጭ የሚያበቅሉ ሰዎች ስለበዙብን… አለ አይደል…ሁለት ጉንጭን ከኮነንን ባለ ሰባቶቹን ምን እንደምንላቸው ግራ ገብቶናላ!)
እናላችሁ…ለነገሩ የዘመኑ የጓደኝነት ነገር… አለ አይደል…
    ከሌለህ ማን አለ ደጅህ
    ኪስህ ነው የልብ ወዳጅህ
ስለሆነ ከሚፈርሱ ጓደኝነቶች ይልቅ የሚያስገርሙት የሚከርሙት ሆነዋል፡፡
“አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ምስጋና ይግባው!” ለማለት ያብቃንማ!
እናላችሁ …ነገሮች ሁሉ እንዳጀማመራቸው አልቀጥል እያሉ ተቸግረናል፡፡
እሱዬው ተሹሞ ይመጣና የትውውቅ ስብሰባ ይጠራል፡፡
“ምንም እንኳን በአለቅነት ብቀመጥም እንደ አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ ብታዩኝ እወዳለሁ። እዚህ የመጣሁት አናት ላይ ቁጭ ብዬ ትእዛዝ ለማስተላለፍ ሳይሆን ከእናንተ ጋር እጅና ጓንት ሆኜ ይህን ድርጅት ለማሳደግ ነው፡፡ ሁላችሁም እንደ ወንድማችሁ ብታዩኝ እወዳለሁ…” ምናምን እያለ ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንኳን የሚበዛ ዲስኩር ያደርጋል፡፡ በተከታዮቹ ቀናትም ትንሽ፣ ትልቅ ሳይል ለሁሉም ሰላምታ ይሰጣል፣ ስለ ሥራ ይጠይቃል፡፡  
ከዛም ከአንድ ወር በኋላ ላይኛው ቆዳ ይገፈፍና እውነተኛው ከውስጥ ብቅ ይላል፡፡ እንኳን ሰላም ሊል በዓይኑ ሙሉ ማየት እንኳን ይተዋል፡፡ መሬት ሊስሙ ደርሰው ሰላም ሲሉት፣ ጀርባውን ማዞር ይጀምራል፡፡ ለጸሀፊዋም ቀጭን ትእዛዝ ይተላለፋል።
“ማንም ሠራተኛ እኔ ቢሮ ቢመጣ እንዳታስገቢ፡፡ ጉዳይ ካላቸው እዛው ከአስተዳደሩ ጋር ይጨርሱ…” ምናምን ይባላል፡፡
እኔ የምለው…ያ ለተባበሩት ጠቅላላ ጉባኤ እንኳን ይበዛል ያልነው ዲስኩርስ! እንደ ወንድማችሁ ብታዩኝ እወዳለሁ ምናምን የተባለውስ!
“አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ምስጋና ይግባው!” ለማለት ያብቃንማ!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ... ይሄ መንግሥት መሥሪያ ቤት ሰኔ ላይ አሥራ አምስት ‘ሶፍት፣’ አሥራ አራት ሳሙና ምናምን ይሰጥ የነበረው… ቀረ እንዴ! ለነገሩ በተወደደ ጤፍ ለአንድ ወር አሥራ ምናምን ‘ሶፍት’ አሽሙር ሊመስል ይችላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…ብዙ ነገሮች እንደ ጅምራቸው አልዘልቅ እያሉ ተቸግረናል፡፡
አልኮል እየጠጡ በሚነዱ ላይ ቁጥጥር ነገር ተጀምሯል መሰለኝ፡፡ እስከ ምን እንደሚቀጥል ለማየት ያብቃን እንጂ ነገሩ አሪፍ ነገር ነው፡፡
እናማ…እነ እንትና ‘ሲፕ’ እያደረጉ መኪናን ‘በአውራ ጣት’ ብቻ ለመንዳት መሞከር ዕዳ ሊያመጣ ነው፡፡ “አቦ፣ ይሄ ቤት አልሰለቻችሁም! እንትና ቤት ሄደን ለምን አፕሬቲቭ አንጠጣም…” የሚል ሸላይ አሽከርካሪ… … አለ አይደል… ‘ዋሌቱ’ በቅጣት አፕሬቲቭ ሊሆንለት ነዋ!
“እኔ እኰ አይደለም አራት ደብል… የውስኪውን ጠርሙስ ግማሹን ብገለብጠው አንድ ብርጭቆ ውሀ የጠጣሁ አይመስለኝም…” ብሎ ፉከራ ወንዝ አያሻግር ይሆናል፡፡
“እሱ እኮ ሲጠጣ ቢያነጋ አንዴ መኪናው ውስጥ አስገብተህ ካስቀመጥከው ቀጥ ብሎ እቤቱ ድረስ ይነዳል…” አይነት አድናቆት እንደ ወንዝ አሳስቆ ይወስድ ይሆናል፡፡ ነገሮች እንደ ጅምራቸው እንዲቀጥሉ እንመኛለን፡፡
“አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ምስጋና ይግባው!” ለማለት ያብቃንማ!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እግረ መንገዴን… የሆነ ቦታ በፈረንጅ አፍ ተጽፋ ያነበብኳትን እዩልኝማ…
“ፖለቲከኞችና ዳይፐሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁለቱም በየጊዜው ለተመሳሳይ ምክንያት መለወጥ አለባቸው፡፡” ቂ…ቂ…ቂ… ትረምፕ ይሄን ቢያዩ ትዊተርን ይቀውጡት ነበር፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2737 times