Monday, 03 April 2017 00:00

ደንጋዮች የሰገዱላቸው የጎንጂ መነኩሴ

Written by  ታደለ ገድሌ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

    የደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም የታላላቅ ባለቅኔዎችና ፈላስፋዎች የትውልድ ቦታ  ብቻ ሳይሆን የቅዱሳን አባቶች  ሀገርና ማረፊያ ጭምር መሆኑን  ታሪክ ያበሥረናል፡፡ ደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም፣ ከጎንጂ ቆለላ የወረዳ ከተማ 1.5 ኪሎ ሜትር ወደ ቆላው ወረድ ሲሉ ይገኛል፡፡ አካባቢው በዛፍና በልዩ ልዩ ዕፀዋት የተከበበ በመሆኑ ወደ ገዳሙ ሲወርዱ የዛፎቹና የአበቦቹ መዓዛ ነፍስን ይመስጣል፡፡ ባለቅኔው ተዋነይ የዕፀዋት ጥበበኛ ሊሆን የቻለውም ከዚሁ የተነሣ  ነው ብሎ ለመገመት ያስችላል፡፡ ጎንጂ ቆለላ የሚገኘው በምዕራብ ጎጃም ዞን  ውስጥ ሲሆን በጊዜው አወቃቀር የዞኑ ዋና ከተማ ፍኖተ ሰላም ነው፡፡ ምንም እንኳን ጎንጂ ቆላላ ለባሕርዳርና ለአዴት ቅርብ ቢሆንም በአወቃቀር በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ ተካትቷል፡፡
ለሥራ ጉዳይ  ወደ ቦታው ሔጀ በነበረበት ወቅት የገዳሙ  አስተዳዳሪ ቄስ መልካም በዜ  ስለገዳሙ አመሠራረት በቃለ መጠይቅና በጽሑፍ ጭምር ማስረጃዎችን ሠጥተውኛል፡፡ በማስረጃዎቹ መሠረት፤ የደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም የተመሠረተው በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ መሥራቹም ንቡረ ዕድ አዛርያስ ነው፡፡ አዛርያስ በዘመኑ እንደ ጳጳስ ይታይ ነበር፡፡ የቀዳማዊ ምኒልክ እናት ንግሥት አዜብ /ሳባ/ 31 ዓመተ ዓለም ገዝታ፣ ሥልጣንዋን ከእሥራኤል ንጉሥ - ሰሎሞን ለወለደቺው ልጅ ለቀዳማዊ ምኒልክ አስረክባለች፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክም ኢትዮጵያን ለ25 ዓመት /ዓመተ ዓለም/ ገዝቷል፡፡ ንቡረ ዕዱ አዛርያስ ታቦተ ጽዮንን ከወንድሙ ጋር ካመጣ በኋላ በዚያው በትግራይ ክልል ውስጥ ገሊላ ከምትባለው ጎጥ ድላሎ የሚል ስም ሰይመው አስቀምጠው ነበር፡፡ በመቀጠል ሸዋ ላይ አንኮበር፤ ጎንጂ ጽላሎ፤ ምሥራቅ ጎጃም ግንደበረት ላይ እንዲሁ ጎንጂ ጽላሎ የሚል ስያሜ ሰጥተዋል፡፡ ቀጥለው ቆለላ ላይ ጎንጂ ጽላሎ ሲደርሱ የነበረውን ሁኔታ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ወአዕረፉ በምድረ ቆለላ ሲል ይገኛል፡፡ ይኸ ደብረ ገሊላ ጥንትም ሊቃውንት ቅኔ ሲቀኙበት ነበር፡፡ ጽሑፉ ወአዕረፉ በምድረ ቆለላ ቢለው  ጎንጂ አፋፍ ላይ በሚገኘው ጎጥ ካባ ለብሶ  ከተባለው ቦታ ሊቀ ካህናቱ አዛርያስና ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ሚካኤልን አስገብተዋል፡፡ ይኸውም ታቦተ ሕጉ የተቀመጠው /በመጀመሪያ ጊዜ/ በድንኳን ውስጥ ነበር፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በምኩራብ ከአስቀመጡ በኋላ ምሥዋዕተ ኦሪት እንዲሰጥበት አድርገዋል። ይኸውም ደብሩ የተቆረቆረበት ዘመን በ4018 ዓመተ ዓለም ነው፡፡ ቦታው ገሊላ ወይንም ካባ ለበስ ከተባለው ቦታ ላይ ሲሆን ከ218 ዓ. ምሕረት ድረስ የክርስትናው እምነት አስተምህሮ  ውስጥ ለውስጥ ሲካሄድበት ቆይቷል፡፡
ከ317 ዓ.ም በኋላ በደጋጎቹ ነገሥታት በአብርሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥትና በአቡነ ሰላማ የጵጵስና ዘመን ቦታው ከምኩራብነት ወደ ቤተክርስቲያንነት ተዛወረ፡፡ ቀጥሎ በዓፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት የገዳምነት ክብሩን አገኘ። ለዚህ በዓፄ ይኩኖ አምላክ እውቅና ለአገኘው ገዳም ራሳቸው /ንጉሡ/ ሁለት የወርቅ ሥዕል፤ አንድ የወርቅ መስቀል ከሙሉ አልባሳት ጋር አበርክተው  ገዳምነቱን አጽድቀዋል፡፡ ከአበረከቱት የወርቅ መስቀል ላይም “ዘወሀቦ ዓፄ ይኩኖ አምላክ” የሚል ጽሑፍ ይገኝበታል፡፡ ከዓፄ ይኩኖ አምላክ እስከ ዓፄ ሠይፈ አርእድ ድረስ ካባ ለብሶ ከተባለው ቦታ ላይ ቆየ፡፡ ከዚህ በኋላ የዓፄ ሠይፈ እርእድ የልጅ ልጅ አቡነ ግርማ ሥሉስ የተባሉ መምህርና አበምኔት ታቦቱን ከካባ ለብሶ አውርደው አሁን ከአለበት ገዳም ወርዶ እንዲተከል አድርገዋል፡፡ ይህም የተፈጸመው መንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ነው፡፡
አቡነ ግርማ ሥሉስ የደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስን ታቦተ ሕግ አሁን ታቦቱ ከአለበት ቦታ ላይ ከአሠፈሩ በኋላ በምዕራብ አቅጣጫ ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን በመጨመር የታቦታቱን ቁጥር ሁለት አድርገውታል፡፡ የገዳሙንም ትልቅነት በማየት ቀደም ሲል  ታቦቱ ከነበረበት ቦታ ትንሽ ወደ ምሥራቅ እንዲስፋፋ ተደርጎ ስለተገነባ፣ በነገሥታትና ጳጳሳት ዘንድ ክብሩ ከፍ እያለ መጣ፡፡ በመሆኑም በዓፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት ለደብሩ ሁለት ቅጽር ያለው ሆኖ በኖራ እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ ደብሩ ከዕድሜ ብዛት በተጎዳ ጊዜም  እስከ ዛሬ ድረስ በኖራ እየታደሰ አሁን እስከ አለንበት ዘመን /2009/ ድረስ ደርሷል፡፡
ቄስ በዜ መልካሙ የደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም አስተዳዳሪ በደብሩ ውስጥ ከሚገኝ የጽሑፍ ማስረጃ ጋር እያጣቀሱ እንደገለጹልኝ፤ የዚህ ጽሑፍ ርእሰ ጉዳይ የሆኑትና ከትሩፋት ሥራቸው የተነሣ ደንጋዮች ሰግደውላቸዋል የተባሉትና ፈዋሴ ዱያን መሆናቸው የሚነገርላቸው የአቡነ ግርማ ሥሉስ ዐፅምም ያረፈው  በዚያው  ገዳም ውስጥ ነው። ድንግል የነበሩት አቡነ ግርማ ሥሉስ የተወለዱት እዚያው ጎንጂ ቴዎድሮስ ነው። አባታቸው ነገደ ኢየሱስ፤ እናታቸው ትኩና ለጽዮን  ይባላሉ። ነገደ ኢየሱስ የተባለው ግለሰብ ሀብታም ስለሆነ ከሀብቱ ብዛት የተነሣ ጉልበት ተሰምቶት ነበር። በዚህ ዓይነት ዓፄ ሠይፈ አርእድ ሠራዊታቸውን አስከትለው ከጎንደር ወደ ሸዋ ሲሄዱ ጎንጂ እሙይት ከተባለችው ቦታ ልዩ ስሙ ጉመር ከተባለው ጎጥ ሳር ውሀ ላይ ሠፈሩ፡፡ በሠፈሩበት ቦታ ላይ ለአንድ ወር ቆዩ። በዚያ ወቅት ሁሉም ሰው ወጥቶ ንጉሡን እጅ መንሣት እንዳለበት አዋጅ ተነገረ፡፡ ነገደ ኢየሱስ የተባለው ከሀብቱ ብዛት የተነሣ “እኔ ለንጉሥ አልሰግድም” ብሎ ንጉሡን እጅ ስለአልነሣ፣ የንጉሡ ሠይፈ አርእድ ወታደሮች አስገድደው በመውሰድ ወደ ንጉሡ ያቀርቡታል፡፡
ንጉሡም “ለምን እጅ አልነሣኸኝም” ብለው ይጠይቁታል፡፡ በመልሱ በመናደዳቸውም ሁለት ዓይኑን ያወጡታል፡፡ ከዚህም የግፍ ሥራ የተነሣ ፀሐይ ለሦስት ቀን ሙሉ ብርሃኗን ትሠውራለች። ንጉሡ የፀሐይ መጥፋቷ ምክንያት ምንድን ነው ብለው ቢጠይቁ፣ መልስ ስለአጡ ሱባዔ ይገባሉ፡፡ ሱባዔ እንደገቡም፤ “እግዚአብሔር ሆይ ምን በድየህ ነው የፀሐይ ብርሃንን የጋረድክብኝ” ብለው ጸለዩ። ጌታም በመንፈስ ቅዱስ ተገለጠላቸው፡፡ “ፀሐይ ብርሃኗን እንዳትሰጥህ የከለከልኳት የነገደ ኢየሱስን ዓይን በማጥፋትህ ነው” የሚል መልስ ሰጣቸው። በዚሀ ጊዜ ነገደ ኢየሱስን አስጠርተው፤” ረዳትህና ካሳህም  ትሆን ዘንድ ልጄን ልዕልት ትኩና ለጽዮንን  ሰጥቼሃለሁ” ብለው ለነገደ ኢየሱስ አጋቡት፡፡ ነገደ ኢየሱስም ትኩና ለጽዮንን “ተኩልኝ” ብሎ ሰየማት። ከእርስዋም አቡነ ግርማ ሥሉስንና ዐሰበ ክርስቶስን ዘልያን፣ ጽጌ ማርያምን፣ ማዕዶትን ወለደ፡፡
ግርማ ሥሉስ የተወለዱት በጾታ አካላቸው ላይ ማተብ አድርገው፤ በእጃቸው መስቀል ይዘው ተገዝረው ነው። ስለዚህ አቡነ ግርማ ሥሉስ ድንግል ናቸው፡፡ ለአካለ መጠን እንደደረሱ በአበምኔትነት ከቆዩ በኋላ በብቃት እሙይት ከተባለው ባሕር ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ አድረዋል፡፡ በኋላ ወደነበሩበት ቦታ ሲመለሱ አዕባን /ደንጋዮች/ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አቡነ ግርማ ሥሉስ” እያሉ ከእሙይት ባሕር እስከ ጎንጂ ድረስ ተከተሏቸው። ከዚያም ወደ ገዳሙ ሊወርዱ ሲሉ አብዛኛው ደንጋይ በምክር ከአፋፍ በላይ ሲቀር፣ ሦስቱ ደንጋዮች ግን “ከወደቁበት እንወድቃለን” ብለው ተከትለዋቸው ሲወርዱ፣ “አይሆንም ተመለሱ” ብለው ገዘቱዋቸው። ደንጋዮችም ከአሉበት ቦታ ላይ በመቅረታቸው “ግዝት ድንጊያ /ደንጋዮች/” ተብለው እስከ ዛሬ ድረስ ይጠራሉ። (የተገዘቱ ድንጋዮችን ፎቶግራፍ ስለአነሳኋቸው መመልከት ይቻላል፡፡) ስለተገዘቱ እንጂ የቆሙበት ቦታ’ኮ ከፍተኛ ቁልቁለት ነው፡፡ በቦታው ላይ ደንጋይ ቀርቶ ስንጥር እንጨት ሊቆም አይችልም፡፡
በማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 21፣ ቁጥር 21  ላይ፡- ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ  “እውነት እላችኋለሁ  እምነት ቢኖራችሁ፤ ባትጠራጠሩም ---ይህን ተራራ እንኳ ተነቅለህ  ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል” ቢልም ደንጋዮች  አቡነ ግርማ ስሉስን የተከተሏቸው  በራሳቸው ፈቃድ እንጂ በእርሳቸው ትእዛዝ አይደለም፡፡
ከአፋፍ በላይ የቀሩት ደንጋዮች በአሁኑ ጊዜ ከጎንጂ ቆለላ ከተማ ከገበያው መሃል ይገኛሉ፡፡ ቦታው ከጊዜ በኋላ ገበያ እንደሚቆምበት የታያቸው ሥሉስ፤ ከባሕር ውስጥ ወጥተው “ቅዱስ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ የተከተሏቸውን ደንጋዮች ባሉበት ቦታ ላይ እንዲቆሙ የመከሯቸው እንዲህ ብለው ነው፡-
“ከጊዜ በኋላ ከዚህ ቦታ ላይ ገበያ ሊቆም ስለሚችል የደጋውና የቆላው ወገኔ ለገበያ በሚገናኙበት ጊዜ ማረፊያና የሸቀጣሸቀጡ መቀመጫ ትሆናላችሁ” ስለአሉዋቸው በአሁኑ  ጊዜ በቁጥር ከ60 በላይ የሚሆኑ ደንጋዮች በየቦታው  በመደዳ ተሰድረው ለገበያተኛው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ መስከረም 10 ቀን በታላቅ ድምቀት በዓላቸው ይከበራል፡፡ ለገዳሙም ገቢ ያስገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከደብረ ጥበብ ገዳም ከፍ ብሎ በግርማ ሥሉስ ስም የተሰየመ ጸበል ፈልቆ ሕሙማን በየጊዜው ይፈወሱበታል፡፡ እስከ አንድ ሺህ ሕሙማን ይፈወሳሉ፡፡  ግርማ ሥሉስ ዘመናቸውን በምንኩስና የገፉ ሲሆን ገዳሙን ለዐርባ ዘመን በመምህርነት አገልግለዋል፡፡
የገዳሙ ታሪክ ሲወሳ የአቡነ ክርስቶደሉም ስም አብሮ ይጠቀሳል፡፡ አቡነ ክርስቶደሉ የዓፄ ሱስንዮስ ጳጳስ ናቸው፡፡ ያስመጡዋቸውም ከኢየሩሳሌም ነው ይባላል። ጳጳሱ መንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ትንቢት በመናገር ዴንሳ ውስጥ ግንብ በተባለ ቦታ ሲኖሩ ዕለተ ሞታቸው ደረሰ፡፡ አንድ ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ “ረፍቴ ደርሶአልና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ስብሐተ እግዚአብሔር ከማይታጎልበት ገዳም ጎንጂ ውሰዱና ቅበሩኝ” ብለው በዙሪያቸው ለሚገኙ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
ሰዎችም፤ “አባታችን አሁን ዕርበተ ፀሐይ ሆኖአል እኮ” ቢሏቸው፣ “ፀሐይን ገዝቻታለሁ” ብለው ባለችበት ላይ አቆሟት፡፡ ሰዎችም ይዘዋቸውና አስከሬናቸው ጎንጂ ደርሶ ከተቀበሩ በኋላ ኀዘንተኛው ወደ ዴንሳ እስኪመለስ ድረስ ፀሐይ ብርሃኗ አልጠፋም ነበር፡፡ ከዴንሳ እስከ ጎንጂ ያንድ ቀን መንገድ ያህል እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ የአቡነ ክርስቶደሉ መቃብር መፈወስ ደዌ ሆኖ በደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
Read 830 times